በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ
በዚህም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን መከላከያ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በመግለጫውም የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ትግራይ ክልል ውጤታማ ህግ የማስከበር ተልእኮውን በጀግንነት በመፈጸም ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛል ብሏል፡፡
ይህ ሆን ተብሎ የሰራዊቱን ህገ መንግስታዊ ተልእኮ ለማስተጓጎል ታስቦ የተሰሩ የጥፋት ሴራዎች በሰላም ወዳዱ ህዝባችን እና በመከላከያ ሰራዊታችን የተቀናጀ ስራ ሊከሽፍ ችሏል ነው ያለው።1ኛ በመተማ መስመር ለዘመናት አብረው በኖሩ የቅማንት እና የአማራ ተወላጆች መካከል የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች ከህብረተሰቡ እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ስራ በመስራት የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል ፡፡
በወለጋ ቡሬ መስመር በጊዳ አያና አንገር ጉቴ አዋሳኝ አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብሮ በኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአካባቢው ህብረተሰብ ትብብር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል ብሏል መግለጫው።እንደዚሁም የኢትዮጵያን የገቢ እና ወጪ የንግድ እንቅስቀቃሴን ለመገደብ በማሰብ በሱማሌ እና የአፋር ኢሳ ህዝቦችን ለማጋጨት የተሰራው ሴራ በሰላም ወዳዱ ህዝባችን የተቀናጀ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ለመዋል ተችሏልም ነው ያለው፡፡ሌላው ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም በዚህ ሁለት ሶስት ቀን በአጣዬ ከተማ እና በአካባቢው በታጠቁ ሃይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ይመኛል ብሏል፡፡በዚህ የጸጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና መሳርያ ይዘው በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ የሰራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ጸረ ሰላም ሃይሎች ላይ ሰራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየገለጽን÷ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የህብረሰተቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሚኒስቴሩ በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳልም ብሏል መግለጫው፡፡በዚህም መሰረት በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ሚኒስቴሩ አመላክቷል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራን ይሰራልም ነው ያለው፡፡በዚህም መሰረት የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል፡፡1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪ/ሜ ውስጥ የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግስት ተቋማትን የግለሰብ መኖርያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጥልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለህብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት የመንግስት መዋቅር እና በድኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን መታወቅ አለበት ብሏል፡፡በመጨረሻም መላው ህብረተሰባችን እንደወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ ለገሀራችን ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን ፡፡
የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር