የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአለም አቀፍ የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የአለም አቀፍ የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማሺዲሶ ሬቤካ ሞኤቲን በጽ/ቤታቸው አነጋግረዋል።የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት፣ የጤናና የሰላም ጥብቅ ቁርኝት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና፣ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
ወ/ሮ ሙፈሪያት በትግራይ የጤና አገልግሎትን ጨምሮ እየተከናወነ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍና ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሂደት ላይ ገለጻ አድርገዋል። ሚኒስትሯ፣ የአለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች አጋር የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ በአጠቃላይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ አዳጋች ሁኔታዎች በገጠማት ጊዜ ሁሉ ለሚያደርጉት እገዛ ከልብ አመስግነዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን የመሰረታዊ ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ሽፋን ለበርካታ አመታት ሲከታተሉት የቆየ ጉዳይ መሆኑንና በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለ ዘርፍ መሆኑ ለሌሎች ሀገሮች መልካም ምሳሌ እንደሆነ መናገራቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
Source: EBC