በምዕራብ ጎጃም ዞን የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች በወለጋ፣ በመተከል፣በሸዋ አጣዬ፣ካራቆሬና በሌሎችም አካባቢዎች በአማራ ላይ የሚፈፀመው የዘር ፍጅት ይቁም በሚል ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፤ ሰልፉን ተከትሎም በሰልፈኞች እንዲሁም በፀጥታ አካላት ላይ ጭምር ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ገልፀዋል።
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋበመቶዎች የሚቆጠሩ በምዕራብ ጎጃም ዞን የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።
በሰላማዊ ሰልፉም በወለጋ፣ በመተከል፣በሸዋ አጣዬ፣ካራቆሬና በሌሎችም አካባቢዎች በመንግስት አካላት ጭምር በመታገዝ በአማራ ላይ እየተፈፀመ ያለው የለየለት የዘር ፍጅት እንዲቆም ተጠይቋል።
በወለጋ በኦሮሚያ የልዩ ኃይል አባላት ጭምር በመታገዝ እየተፈፀመ ያለው ግድያ፣ዝርፊያና መፈናቀልን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኃላፊነቱን በመወጣት ጥቃቱን እንዲያስቆም፤ በሸዋ አጣዬ፣ካራቆሬና አካባቢው በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ፍጅት በማውገዝ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግለትም በፍኖተ ሰላም ወጣቶች ተጠይቋል።
ይሁን እንጅ ነዋሪዎች እንደሚሉት ሰላማዊ ሰልፉን ለማስቆምና ለማረጋጋት ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ፖሊሶች መካከል በአንደኛው ላይ ካልታወቀ አካል በተተከሰበት ጥይት ተመቶ ሕይወቱ አልፏል።
ሰላማዊ ሰልፈኞችም አንድም ተተኳሽ ነገር ይዘው እንዳልነበር ነው የዐይን እማኞች የተናገሩት።በመቀጠልም ከሰልፈኞች መካከል ሁለት ወጣቶች ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት ቆስለዋል።
አንደኛው ወጣት ጉንጩ ላይ የተመታ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እግሩን ነው በጥይት የተመታው።አንድ የአድማ በታኝ አባል ደግሞ በድንጋይ ጭንቅላቱ ላይ ተመቶ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ተገልጧል።ይህ ዜና ሲጠናቀር ሰላማዊ ሰልፉ ተበትኗል፤ ተኩስ መቆሙም ታውቋል፤ መንገዶች እየተዘጋጉ መሆኑም ተጠቁሟል፤ አሁን ላይ የፀጥታ አካላት በፓትሮል እየዞሩ አካባቢውን እየቃኙ ነው የሚል መረጃ ደርሶናል።
SOURCE:AMC