ቀዳሚው የሙዚቃ አሳታሚ አረፈ
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በሀገሪቱ የነበረው የሙዚቃ ውጤቶችን የሚያቀርብ አንድ የጣልያን ድርጅት ነበር። ይህ ድርጅት በበቂ ደረጃ የህዝብን ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉ ከልጅነቱ ጀምሮ በሙዚቃ ፍቅር የተነደፈው ታዳጊው አምሀ እሸቴ በግሉ የተለያዩ ሀገራትን ሙዚቃዎችን እያስመጣ በመሸጥ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንደስትሪ ተቀላቀለ።
በአጭር ጊዜ ውስጥም ለምን የራሳችንን ሙዚቃ ራሳችን አሳትመን በራሳችን ለገበያ አናቀርብም በሚል እልህና ቁጭት ተነሳስቶ በ1961 አ.ም የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴን ሙዚቃ በማሳተም በሀገር ውስጥ የመጀመርያው የሸክላ አሳታሚ በመሆን ጉዞውን ጀመረ።ስድስት አመታትን ባስቆጠረው አምሀ ሪከርድስ በተሰኘ የሸክላ ህትመት ጊዜያት 103 የሚጠጉ በነጠላ የወጡ ዜማዎችንና 14 የሽክላ አልበሞችን ለማሳተም በቅቷል።
አንጋፋው የሙዚቃ አሳታሚና የአምሀ ሪከርድስ ባለቤት አምሀ እሸቴ ከአሳታሚነቱ በተጨማሪ የዋልያስ የሙዚቃ ባንድ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሰሜን አሜሪካ አቅንቶ የሙዚቃ ዝግጅቱን ሲያቀርብ ድርሻ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ነው።
አንጋፋው የሙዚቃ ሸክላ አሳታሚ አምሀ እሸቴ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።ለመላ ቤተሰቡ፣ወዳጅና አድናቂዎቹ መፅናናትን እየተመኘሁ የሟችን ነፍስ ይማርሚያዝያ 22 ቀን 2013
ተወልደ በየነ (ተቦርነ)