Friday, March 29, 2024
Google search engine
HomeBAWZA NEWSEthiopia | የትንሳዔ በዓል ሲከበር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን የሃማኖት መሪዎች ጥሪ...

Ethiopia | የትንሳዔ በዓል ሲከበር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን የሃማኖት መሪዎች ጥሪ አቀረቡ

የትንሳዔ በዓል ሲከበር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን የሃማኖት መሪዎች ጥሪ አቀረቡ

ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከበር በሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ እንዲሆን የሃማኖት መሪዎች ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በነገው ዕለት የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል አስመልክተው ለህዝበ ክርስቲያኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልእክታቸው የትንሳኤ በዓልን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል።በተለይ በየአካባቢው በሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው የሚገኙ ወገኖችን በመመገብ፣ በማጠጣት እና በማልበስ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠር የሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግር ውስጥ በመሆናቸው ሁላችንም ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።በመሆኑም በዓሉን ሁሉም በደስታ እንዲያሳልፍ ለማድረግ የተፈናቀሉትን ማስብና መደገፍ አለብን ብለዋል። የሀገሪቷን ሰላም ለማስጠበቅ ዘብ የቆሙ ኃይሎችም ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፣ “ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከበር የተቸገሩና አስታዋሽ ያጡትን በማሰብና በመርዳት መሆን ይኖርበታል” ብለዋል።በአሉ ሲከበር እየተስፋፋ የመጣውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የተላለፈውን ምክረ ሀሳብ በመተግበር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም ሰው ክፋትን ከልቡ በማስወገድ በክርስትና ህይወቱ ውስጥ ክርስቶስን መምሰል አለበት ብለዋል።ከተበላሸ ህይወት በመጽዳት የፈጣሪን አብነት መከተልና የሰላም መሳሪያ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።በዓሉን በመተሳሰብና በፍቅር ማክበር እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው።

ከፈጣሪ የተቀበልነውን ወንጌል ከቃል ባለፈ በመተግበር እርስ በርስ ተከባብሮ በፍቅርና በሰላም መኖር ይገባል ብለዋል።”እኛ ታርቀን ሌሎችን ማስታረቅ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል” ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።መላው የወንጌል አማኞች ምዕመናን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጾምና ፀሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ህዝበ ከርስቲያኑ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችን በማሰብና ድጋፍ በማድርግ ከጎናቸው እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የትንሳኤ በዓል በነገው እለት በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ ይውላል።

ሚያዝያ 23/2013 (ዋልታ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments