የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን አጸደቀ

0
447

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮርቤቲ የኃይል ግዢ ስምምነት እና ረቂቅ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ እንዲሁም ሁለተኛውን የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አጸደቀ።ምክር ቤቱ ዛሬ ጠዋት ባካሄደው ስብሰባ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኮርቤቲና ከቱሉሞዬ የጂኦተርማል ኃይል የግል አመንጭ ኩባንዎች ጋር የተደረጉ የኃይል ግዥ እና የማስፈጸሚያ ስምምነቶች ለምክር ቤቱ አቅርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ስምምነቶቹ በምክር ቤቱ ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ከኮርቤቲ ጋር የሚደረገው የኃይል ግዢ ስምምነት መንግሥት ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማካሄድ ረዥም ዓመታትን የጠየቁ ሥራዎችን ካከናወነ በኋላ መጠናቀቁ ተገልጿል።በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል የሚከወንን የጥምረት ሥራ፣ የውጪ አካላት በቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የሚችሉበትን የእንፋሎት ሃይል እና የኢነርጂ አዋጆችን፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማካሄድ የሚችልባቸውን ሁኔታዎችን በአግባቡ በማጥናት ማጽደቅ የዚሁ ሥራ አንድ አካል መሆኑንም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስታውቀዋል።የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር በአንድ በኩል እንዲሁም የኮርቤቲ እና ቱሉ ሞዬ ኩባንያዎች ደግሞ በሌላ በኩል በመሆን፥ በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል የሚካሄደውን ጥምረት በመከወን በአጠቃላይ 300 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ኃይል እንደሚያመነጩም ጠቅሰዋል።የኢትዮጵያ እንፋሎት ኃይል ዘርፍ እና ተያያዥ ክህሎቶች፣ የኢትዮጵያን የኃይል ዐቅም፣ ዋስትና እንዲሁም አስተማማኝነት በሚያረጋግጥ መልኩ አረንጓዴ፣ ንጹሕ እና ታዳሽ የኃይል ምንጭ በጥቅም ላይ ያውላሉም ነው ያሉት።ምክር ቤቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ተወያይቷል፡፡የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ዋና አላማ ሀገሪቱ አለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ አማራጭ መንገዶችን እና ስልቶችን ማመላከት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚሰጠውን የእድገት አማራጭ አሟጦ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ረቂቅ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ መንግሥት የፈጠራ ሥራዎች እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት ሁሉን አካታች ዕድገት ለማምጣት የሚያከናውነው ሥራ ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል።ቀበሌዎች ከወረዳዎች ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከርም ዲጂታል ዕውቀትን ለማሳደግ፣ ለቱሪዝም ዘርፉ ድጋፍ ለማድረግ እና በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለማዳበር የታለመ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ያስታወቁት።በተጨማሪም ዲጂታል ኢኮኖሚውን በፍጥነት ለማሳደግ እና በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የንግድ አሠራር ለማዘመን በሚያስችል መንገድ፥ የመንግሥት አካላት ዲጂታል አገልግሎቶችን በውጤታማነት እንዲያቀርቡ ያግዛልም ብለዋል።ይህም መንግሥት የንግድ ሥራዎች በተቀላጠፈ መንገድ እንዲካሄዱ የተገበራቸው ተከታታይ ማሻሻያዎች አንድ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።ምክር ቤቱም በስትራቴጂው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንግድ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡የኢኮኖሚ ዕድገትን እና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለንግድ ሥራ ጽኑ የሕግ መሠረት መጣል የግድ ይላል ያለው ምክር ቤቱ በ1952 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ከወጣበት ዘመን አንጻር ከጊዜው የቀደመ ነበር ማለት የሚቻል ቢሆንም ባለፉት ስልሳ ዓመታት በርካታ የንግድ ጉዳዮች መለዋወጣቸውን ተመልክቷል፡፡ዛሬ ላይ ለአፈጻጸም የማይመቹ እና ለተለያዩ ትርጉሞች የተጋለጡ ብዙ ድንጋጌዎች እንዳሉበትም በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች አረጋግጠዋል ነው ያለው፡፡በመሆኑም ለመጪዎቹ ዓስርት አመታት የአገራችንን የንግድ እንቅስቃሴ ለመምራት ቀርቶ ዛሬ ኢትዮጵያ ለደረሰችበት የኢኮኖሚ እንቅስቀሴ ደረጃም ቢሆን ሕጉ የተሟላ እና በቂ ሆኖ ስላልተገኘ የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንግድ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡አዲሱ የንግድ ህግ መንግስት የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመገንባት ያለውን ፍላጎት ባማከለ መልኩ የፈጠራ እና የንግድ ሥራዎች ክንውንን የሚያነሳሳ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት አንስተዋል።

Source: FBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here