አብን ከባሕር ዳር ከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ተወያየ

0
207

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ ከሰዓት በኋላ በባሕር ዳር ከተማ በባሕር ዳርና አካባቢዋ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በንቅናቄው የማኅበራዊ ገጽ አጠቃቀም፣ በአማራ ሕዝብ አንድነት፣ ምሁራንን መጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ ንቅናቄው አካታች እንዲሆን፣ ከክልሉ ውጭ የሚገኙ አማራዎችን መብት ስለማስከበርና ከሌሎች ክልሎች ጋር መልካም ግንኙነት ስለመፍጠር ጥያቄዎችንና አስተያዬቶችን አንስተዋል፡፡

አብን የአባላቱን ደኅንነት ስለማስጠበቁ፣ መታወቂያና መሰል መገለጫዎችን ስለማዘጋጀቱና እስከ ገጠር አካባቢዎች እየወረደ መዋቅሩን እንዲያጠናክር በውይይቱ ተነስቷል፡፡

የአብን መሪዎች በመድረኩ ላይ በሰጡት ማብራሪያም ንቅናቄው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እንደሚያከብር፣ አመራርና አባላቱን አቅም የማጎልበት ሥራ እንደሚሠራና አሁን የሕልውና ትግል ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በምርጫ ለማሸነፍ ሀገሪቱ ሠላሟ መረጋገጥ እንዳለበት ያስገነዘቡት አወያዮቹ ለቀጣዩ ምርጫ ከወዲሁ ፀጥታውን አስተማማኝ የማድረግ ሥራ በመንግሥት እንዲከናወንም አሳስበዋል፡፡

የአብን ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በለጠ ሞላ የአማራ ሕዝብ ትልቁ ችግር የመዋቅር መሆኑን አንስተዋል፡፡ እስከ ታች ድረስ ወርዶ መዋቅርን ለመዘርጋት ፈተናዎች መኖራውን ያስገነዘቡት አቶ በለጠ ‹‹ለመከበር ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ይኖርብናል›› በማለት ተናግረዋል። ደጋፊዎች ወደ አብን እንዲቀርቡና እገዛ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል፡፡(አብመድ)