ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ መሻሻሎች እንዳሳየች “ፍሪደም ሃውስ” አስታወቀ

0
1091

“አገሪቱ አይታ በማታውቀው የዲሞክራሲ ለውጥ ውስጥ ገብታለች”

         ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መምራት ከጀመሩበት ሚያዚያ 2010 ዓ.ም ወዲህ ሃገሪቱ የዲሞክራሲ መሻሻሎችን እንዳሳየች ያስታወቀው ፍሪደም ሐውስ፤ አሁንም ዲሞክራሲውን እውነተኛ ለማድረግና ነፃ ህዝብ ለመፍጠር ሃገሪቱ ብዙ ሥራዎች ይቀራታል ብሏል፡፡ 
የዓለም ሃገራትን የዲሞክራሲ ይዞታ በየዓመቱ እየገመገመ ይፋ የሚያደርገው ፍሪደም ሃውስ፤ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሃገሪቱ በተፈጠረ ህዝባዊ አመፅና የዲሞክራሲ ጥያቄ ምክንያት ስልጣንን ለብቻው ጠቅሎ ይዞ የነበረው ኃይል ተፈረካክሷል፣ አሁን ሃገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር የለውጥ ኃይል ናቸው ብሏል፡፡ 
ለውጥን የሚያራምዱት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ነፃ የፖለቲካ ውይይት መስፋፋቱን፣ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውን፣ ለመገናኛ ብዙኃን ነፃነት መሰጠቱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ነገር ግን አሁንም የሃገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መቶ በመቶ በአንድ የፖለቲካ ኃይል መያዙን አስታውቋል፡፡ 
የፓርላማ ውክልና በተመለከተ ኢትዮጵያ ከ12 በተያዘው የመለኪያ ነጥብ 1 ብቻ ማግኘቷንም አስታውቋል፡፡ ይህ የህዝብ ውክልና በቀጣይ እውነተኛ ሆኖ ሊረጋገጥ ይገባል ያለው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያ ወደ ተጨባጭ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተሸጋገረች ማለት የሚቻለው ይህ ሲፈፀም ነው ብሏል፡፡ 
ከዲሞክራሲያዊ ዕድገት ጎን ለጎን ዜጎች በፈለጉት የሃገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመኖርና የመስራት መብትን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚባም ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡ 
ሃገሪቱ አይታ በማታውቀው ዓይነት የዲሞክራሲ ለውጥ ውስጥ ገብታለች ያለው ሪፖርቱ፤ “ይህን ለውጥ ይበልጥ ተቋማዊ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ዲሞክራሲው መሬት መያዙን ሊያረጋግጥ የሚችለው ደግሞ ቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ ነው” ብሏል፡፡