አዲሱ የንጉሱ ሃውልትና የቀራፂ በቀለ መኮንን ስህተት

0
1486

የ“ስካልፕቸር” (የቅርፅ) ጥበብ በመባል የሚታወቀው የሥነ-ጥበብ ዘርፍ በአራት መሠረታዊ ዘዴዎች ይከወናል፡፡ እነዚህም፥ “ሞዴሊንግ” ወይም በልጅነታችን እናደርግ እንደነበረው ጭቃን፣ የሸክላ አፈርን ወይም መሰል ነገሮችን በማቡካትና ጥበበኛው ቅርፆችን እየለዋወጠ፣ የሸክላ ጭቃውን እየጨመረና እንደፈለገው እያድቦለቦለ የሚሠራበት ዘዴ ነው፤ “ካስቲንግ” ወይም በከፍተኛ ሙቀት ቀላጭ የሆኑ የብረት ዓይነቶችን (ባብዛኛው ነሃስ) ቀደም ተብሎ በተዘጋጀ የተፈላጊውን የቅርፅ ውጤት ይዘት ባለው (ከብዙ ድካምና ማሰብ በኋላ) መያዣ ውስጥ በማፍሰስና ቀዝቅዞ ሲደርቅ ከላይ የነበረውን በአብዛኛው ሸክላ በማፍረስ፣ ተፈላጊውን ቅርፅ የያዘው ብረት ብቻውን እንዲቀር በማድረግ የሚከወን፤ ”አሴምብሊንግ“ ወይም የተለያዩ ነገሮችን በመገጣጠም ወይም በመበያየድ የሚሰራና በ”ካርቪንግ“ ወይም በመፈልፈል ድንጋይ ወይም እንጨትን ጠርቦ የሚፈለገውን ቅርፅ በማውጣት የሚሠራበት ዘዴ ነው።
ሞዴሊንግና አሴምብሊንግ የሚባሉት ዘዴዎች የመጨመር ዘዴዎች ናቸው፤ ምክንያቱም መጀመሪያ የነበረን ሸክላ ወይም የሚገጣጠሙ ነገሮችን ሌላ የሚበየድ ብረት ወይም የሚገጣጠም ነገር እየተጨመረ ስለሚሰራ ነው። ካርቪንግ የሚባለው ዘዴ ግን የቅነሳ ዘዴ ነው፤ ምክንያቱም ቅርፅ አልባ የነበረን ድንጋይ፣ እምነበረድ ወይም እንጨት ከላዩ ላይ በመጥረብና በመፈልፈል፣ ቀራፂው የሚፈልገውን ቅርፅ በማውጣት የሚሰራበት ዘዴ ነው። 
ካስቲንግ ወደሚባለው ዘዴ ስንመለስ፣ ቀራፂው ሥራውን የሚጀምረው ከምንም ወይም ከባዶ በመነሳት ነው። ይህም ሥራውን ከባድ፣ ድካም የሚጠይቅና ተደራራቢ እንዲሁም አደገኛ ያደርገዋል። ያ ለማሰብ በሚከብድ የሙቀት መጠን (እስከ 950 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለነሃስ (ብሮንዝ)) የቀለጠ ብረት ፈሳሽ ፍንጣሪ፣ አያድርገውና የቀራፂው አካል ላይ ቢያርፍ፣ ምን እንደሚያስከትል አለማሰብ  ነው። ለዚህም ከጥበብ ሥራው ያልተናነሰ የጥንቃቄን ጥበብ ይጠይቃል።
ቀዳማዊ ኃይለስለሴ፤ የአፍሪካ ህብረት ሲቋቋም ላበረከቱት አስተዋፅኦ መታሰቢያ የሚሆን ሃውልት እንዲቆምላቸው፣ የመንግስትና የህብረቱ ፈቃድ እንዲሁም የዋና ቀራፂው ፍላጎት መሆኑ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ሆኖም ይህ ሃውልት ባይቆምና በእምነበረድ ድንጋይ ላይ ስማቸውና የትውልድ ዘመናቸው እንዲሁም ለህብረቱ መቋቋም ያበረከቱት ፈር ቀዳጅ አስተዋጽኦ  ፅፎም ቢታለፍ በቂ መታሰቢያ ይሆን ነበረ። ዋናው መታሰቢያው መኖሩ ይመስለኛል፡፡  
ሰዓሊና ቀራፂ በቀለና  አጋዥ ቡድኑ፤ ይህን ከባድ ሃላፊነት በመውሰድና ከላይ እንዳልኩት ካስቲንግ በተባለው የቀረፃ ዘዴ፣ ከምንም በመነሳት፣ እጅግ በጣም ድንቅ የሆነና አድካሚ ጥበባዊ ሥራ በድል በመወጣቱ ከፍተኛ አድናቆቴን እገልጻለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ በምረቃው ሰሞን በየማህበራዊ ሚዲያው፣ ስለ ቅርፁ ብቁ አለመሆን በስሜትና በግልቡ ያሻቸውን ሲሉ ለነበሩና ማየት የሚፈልጉትን ክፋት ብቻ ለሚያዩ ሰዎች፤ እንዲሁም ባብዛኛው አላዋቂ ሳሚ ለሆኑ… (ከአጓጉል ተቺዎች በምንም ለማይለዩ)  ጋዜጠኞች፣ ቀራጺ በቀለ፤ “ድንጋይ ላይ ውሃ የማፍሰስ” ዓይነት ተደጋጋሚ ምላሽ መስጠቱ፣ ለኔ ስህተት መስሎ ታይቶኛል። እንደ እኔ አመለካከት፣ አብዛኛው የሰው ልጅ፣ እድሜውን ካጋመሰ በኋላ ቢግቱት እንኳ የሥነ-ጥበብ ጉዳይ  ይገባዋል ማለት ዘበት ነው። 
ንጉሡን በፎቶግራፍ ብቻ የሚያውቅ ሰው (እኔንም ጨምሮ)፤ የተሰራውን ሃውልት (ስታቹ) ለመተቸት የሚያበቃ ዕውቀት ይኖረናል ማለት የማይታሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የጥበብ ሥራ፤ ከቀራፂው ያልተናነሰ ብቃት ባላቸው የጥበብ ሰዎች ቢተች መልካም ነው። እንዲያውም ቀራፂው በቀጥታ ያየውንና ተገቢ ነው ተብሎ በቡድኑና በአሰሪዎቹ የታመነበትን የንጉሡን ተጨባጭ ገፅታ እንዳለ ከማስቀመጥ ይልቅ እንደ ጥበበኛ፣ ነፃነቱን ተጠቅሞ፣ ለእርሱ መሰል የጥበብ ሰዎች ፍጆታ፣ እነ ገብረክርቶስና እነ ፒካሶ ያደርጉት እንደነበረ፣ የራሱን “ኢማጅኔሽን” ጨምሮ ሰርቶት ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ከሰማነው የባሰ “የአላዋቂዎች” የአደባባይ ሰልፍና ረብሻም ጭምር ሊነሳ ይችል እንደነበረ፣ እየተሰነዘሩ ካሉት ጨዋነት የጎደላቸው ሃሳቦች መረዳት ይቻላል።
በቀለም ቅብ ሥራ፤ በቀለማቱ ጥንቅር (ኮምፖዚሽን) እንዲሁም ድምቀት፤ የተመልካችን ቀልብ ማጭበርበርና መያዝ ቀላል ነው። ነገር ግን ወደ ቅርፅ ሥራ ስንመጣ፣ የቀለማት እገዛ የሌለው ሲሆን የባለ ሶስት አቅጣጫ ይዘት ያለው ከመሆኑ፣ ሸካራነቱ የሚታይ፣ በተለያዩ ጎኖች የተለያዩ እይታዎች ያሉት በመሆኑ ለመተቸት ከፍተኛ ልምድና በተመሳሳይ ዘዴ የተሰሩ ብዛት ያላቸውን ሃውልቶች የማየትና የመገምገም ልምድ ይጠይቃል። እንዲያው የሚሰማኝ አገኘሁ ብሎ የመሰለን መናገር፣ ራስን ከግምት ውስጥ ከመጣል ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ 
ፎቶግራፍ ሌላ፣ ሃውልት ሌላ። ይህን ታላቅ ቀራፂና አብሮት የለፋውን ቡድን ሲሆን መሸለምና ማወደስ ተገቢ ነው፤ መወረፍ ግን ትክክል አይደለም፡፡ አወደስነውም አወገዝነውም እርሱ  የራሱን የታሪክ አሻራ አኑሯል፡፡ በተረፈ ለታላቁ ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን እንዲሁም በሥራው ለተሳተፉት፣ ያለኝን አክብሮት በመግለፅ፣ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡

ምንጭ:- /አዲስ አድማስ ጋዜጣ/