የኢትዮጵያ ባህል ዲፕሎማሲ ቀን ተከበረ

0
937

የኢትዮጵያን ባህል፣ ቅርስና ታሪክ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማቶች ለማስተዋወቅ ያለመ የኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲ ቀን ተከብሮ ውሏል።

የባህል ዲፕሎማሲ ቀኑ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነን ጨምሮ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ አፍሪካ ሀገሮች አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የባህል ዲፕሎማሲ ቀንን በማስመልከትም የእንጦጦ ቤተ መንግስትና ሙዚየም፣ የአዲስ አበባ ቱሪስት መዳረሻ ፓርክ እና ያያ ቪሌጅ ጉብኝት ተደርገዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጥበባትና ባህላዊ እሴቶች፣ ባህላዊ ሙዚቃዎችና ባህላዊ ምግቦች እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶች ለበዓሉ ታዳሚዎች ቀርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእከት፥ “እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነን ይህንን ደማቅ የባህል ቀን በጋራ በማክበራችን ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል።

“ይህ የመጀመሪያችን ነው እንጂ የመጨረሻው አይደለም” ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፥ “እንዲህ አይነት ክብረ በዓሎች የአፍሪካ ውንድሞች እና እህቶቻችን ኢትዮጵያ በሚሆኑበት ጊዜ እንደቤታቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባህል ዲፕሎማሲ ቀንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስሰ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ናቸው በጋራ ያዘጋጁት።