ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር ለስራ የሚሄዱ ሰራተኞች ዝቅተኛ የክፍያ ወለል ተወሰነ

0
658

ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር ለስራ የሚሄዱ ሰራተኞች ዝቅተኛ የክፍያ ወለል መወሰኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ ከሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር ጋር በሰራተኞች ዝቅተኛ የክፍያ ወለል ላይ ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

በዚህም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሚሄዱ ሰራተኞች 1 ሺህ የሳዑዲ ሪያል፣ ወደ ኳታር ለሚሄዱና የቤት ስራዎችን ብቻ ለሚያከናውኑ ሰራተኞች 1 ሺህ 200፣ እንክብካቤ ላይ ለሚሰማሩ ሰራተኞች 1 ሺህ 300 የኳታር ሪያል እንዲሆን መወሰኑንም ነው የተናገሩት።

ከሀገራቱ ጋር የተደረገው ስምምነትም ረጅም ጊዜ የወሰደው ቀደም ሲል የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ያለ ሃላፊነታቸው የደመወዝ መጠን ስምምነት መዋዋላቸው ነው ብለዋል፡፡

ወደ ዓረብ ሀገራት የሚደረግ ህገ ወጥ ጉዞ ከቀን ወደቀን እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ይህን ህገ ወጥ ጉዞ ለማስቀረትና ህጋዊ የስራ ስምሪት ስርዓት ለመዘርጋት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ከ 240 በላይ ህጋዊ ኤጀንሲዎች ያሉ ሲሆን÷ ለምልመላ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎችን እንግልት ለማስቀረትም ኤጀንሲዎቹ በየክልሉ ቅርንጫፍ እንዲኖራቸውና ምልመላው በክልሎችም እንዲከናወን አሰራር መቀመጡን ሚኒስትሯ አንስተዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ዓረብ ሀገራት የሚጓዙ ሰዎችን ለመቆጣጠር ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ብሄራዊ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷልም ብለዋል።

ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታርና ዮርዳኖስ ጋር ስምምነት ላይ ቢደረስም እስካሁን ሰራተኛ መላክ አለመጀመሩን ከዚህ በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መዘገቡ ይታወሳል።

ሚኒስትሯ የሰራተኞችን ከላይ ወደ ተጠቀሱት ሀገራት መላክ ያዘገየው ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ የሰራተኞች ደመወዝ ላይ ተጨማሪ ድርድር ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዜጎች ደህንነታቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ ወደ ሚሰሩባቸው ሀገራት እንዲሄዱ ከስልጠና ጀምሮ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዲያሟሉና ኤጀንሲዎችም ይህን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ሀገራት በተጨማሪም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችና ዮርዳኖስ ጋርም ስምምነት እየተደረገ ሲሆን÷ ስምምነቱ ወደ መጨረሻው ሂደት ላይ እየደረሰ መሆኑም ተገልጿል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)