ከ641 ሺህ በላይ እናቶች ተመርምረው ከ4ሺህ በላይ እናቶች የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ተገኝቷል

0
845

‹‹ከ641 ሺህ በላይ እናቶች ተመርምረው ከ4ሺህ በላይ እናቶች የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ተገኝቷል፡፡››
‹‹ከ1 ዓመት 6 ወር በኋላ ከተመረመሩ ከ2ሺህ 800 በላይ ሕጻናት ውስጥ ደግሞ 102 ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቷል፡›› የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 13/2011 ዓ.ም (አብመድ) በ2010 በጀት ዓመት 102 ሕጻናት ከእናት ወደ ልጅ ኤች አይ ቪ እንደተላለፈባቸው የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የጤናማ እናት ባለሙያ ሲስተር አዲስዘመን ጫኔ ነግረውናል፡፡

ባለሙያዋ እንደገለፁት በ2010 በጀት ዓመት በክልሉ 641 ሺህ 887 እናቶች የኤች አይ ቪ /ኤድስ ምርመራ ተደረጎላቸዋል፡፡ በ4 ሺህ 789 እናቶች ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል፡፡ ይህም ከተመረመሩት ዜሮ ነጥብ 74 ከመቶ ያህሉ እናቶች በደማቸው ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል እንደማለት ነው፡፡
የኤች አይ ቪ /ኤድስ ካለባቸው እናቶች የተወለዱት ሕጻናት ከ18 ወራት በኋላ 2 ሺህ 852 ምርመራ ተደርጎላቸዋል፤ ከእዚህ ውስጥ ከ96 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ከቫይረሱ ነጻ ናቸው፡፡

ይሁን እንጅ 102 ሕጻናት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል፡፡ እንደምክንያት የተነሳው ደግሞ እናቶች በጤና ተቋማት አለመውለዳቸው፣ በእርግዝና ወቅት የፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት አለመጀመር፣ በጡት ማጥባት ወቅት በሚፈጠር ችግር እና መድኃኒት ማቋረጥ መሆናቸውን ሲስተር አዲስዘመን ነግረውናል፡፡ አንድን ልጅ ከኤች አይ ቪ ነፃ ለማድረግ ቢያንስ 2 ዓመት ከ7 ወር በባለሙያ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ነው ባለሙያዋ የተናገሩት፡፡

ኤች አይቪ በእርግዝና፣ በወሊድ ወቅት እንዲሁም በጡት ማጥባት ጊዜ ይተላለፋል፡፡ እናት በተለያዩ በሽታዎች ከተጠቃች በፅንስ ወቅት ሕጻኑ ምግብ ከእናቱ የሚያገኝበት የእንግዴ ልጅ ሲለሚጠቃ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ በቀላሉ ይተላለፋል፡፡

በወሊድ ጊዜ በሚከሰተው ከፍተኛ ምጥ የልጁ ሰውነት ስለሚላላጥ በሚያጋጥመው የደም መፍሰስና ንክኪም ቫይረሱ እንደሚተላፍም ከባለሙያዋ ሰምተናል፡፡ ስሆነም በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በወሊድ ጊዜ ችግር እንዳይገጥማቸው የተለየ ጥንቃቄ ስለሚፈልጉ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማድረግ እንደሚገባም ባለሙያዋ መክረዋል፡፡

ሕጻናት ጡት በሚጠቡበት ጊዜ የጡት ጫፍ እና የልጆች አፍ ከቆሰለ እና የልጆች እንጀት ከተጎዳ ቫይረሱ የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ በሐኪም የታገዘ ምክር በየጊዜው ማግኘት ይገባል፡፡

ባለሙያዋ እንደገለፁት በእርግዝና ወቅት ነፍሰጡር እናቶች ለምርመራ ወደ ጤና ተቋማት ሲሄዱ ክትትል እና ምርመራ ከሚደረግላቸው ውስጥ አንዱ የኤች አይ ቪ ምርመራ ነው፡፡ በምርመራው ወቅትም እናቶች በደማቸው ውስጥ ኤች አይ ቪ ከተገኘባቸው ወደ ሕጻናት እንዳይተላለፍ በደንብ ተከታትለው መድኃኒቱን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

እናቶች ከወለዱበት ጊዜ አንስቶ ለ6 ወራት ጡት ብቻ ማጥባት እንዳለባቸውም ነው ባለሙያዋ የተናገሩት፡፡ በምክንያትነት ያነሱት ደግሞ ከ6 ወር በፊት ተጨማሪ ምግብ መስጠት ሕጻናትን አንጀታቸው እንዲላጥ ስለሚያደርግ በቀላሉ ቫይረሱ እንዲተላፍባቸው ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2020 (እ.አ.አ) በነፍሰ-ጡር እናቶች የኤች አይ ቪ አጋላጭነት ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ዓለማቀፍ ስምምነት ፈርማለች፡፡ በስምምነቱ መሠረት ለነፍሰ ጡር እናቶች በሚደረገው ክትትል የሚያዙ ልጆች ቁጥር ከ5 በመቶ በታች እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ በአማራ ክልል በ2010 በጀት ዓመት አገልግሎቱን ካገኙት እናቶች ውስጥ በቫይረሱ የተያዙት ልጆች 3 ነጥብ 6 በመቶ ሲሆኑ በቁጥር ደረጃ 240 ናቸው፡፡

Amhara Mass Media Agency