Remedies to boost immunity (በሽታ የመከላከል ስርዓት ማጠናከሪያ ዘዴዎች)

0
855
የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ስርዓት ለማጠናከር

በሽታ የመከላከል ስርዓታችንን በማጠናከር በቀላሉ ለተለያዩ በሽታዎች እንዳንጋለጥ ማድረግ ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች። ቀጥሎ የተዘረዘሩ ተግባራትም የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ስርዓት ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው ብለዋል ተመራማሪዎች።

1. የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን መስራት

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሰውነታችንን ከማጠንከር በዘለለ ለጤናችን በርካታ ጠቀሜታዎችን አንደሚሰጥ ይታወቃል። በተለይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትሮ መስራት ከአየር ፀባይ መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ እንደ ጉንፋን እና ኢንፌክሽን ላሉ በሽታዎች እንዳንጋለጥ በማድረጉ በኩል ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በምናከናውንበት ጊዜ የነጭ ደም ህዋሳችን በሰውነታችን ውስጥ በፍጥነት እንዲዘዋወር ስለሚያደርግ ነው። በተጨማሪም የበሽታ ስሜት በሚሰማን ጊዜም ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ጤንነታችንን ለመጠበቅ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑም ይነገራል።

2. ነጭ ሽንኩርት፣ እንጉዳይ እና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን መመገብ

ነጭ ሽንኩርት፣ እንጉዳይ እና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን በእለት ተእለት ምግባችን ውስጥ በማካተት አዘውትሮ መመገብ የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ስርዓት ከፍተኛ አቅም እንዲኖረው ያደርጋል። እንደ እርድ እና ሚጥሚጣ ያሉ የምግብ ማጣፈጫ ቅመሞች ከማጣፈጫነታቸው በዘለለ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ለህክምና ተግባራት እንደሚውሉ ይታወቃል። እንዲሁም እንደ ነጭ ሽንኩርት እና እንጉዳይ ያሉ ምግቦችም ለሰው ልጅ ጤና በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚሰጡ እሙን ነው። በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት እንዳመለከተውም በምግብ መልክ ተዘጋጅቶ የተሰራ እንጉዳይን በየእለቱ መመገብ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ርስዓት አቅምን ለማዳበር እንደሚረዳ ያሳያል። ነጭ ሽንኩርትም ቢሆን በውስጡ በያዘው ከፍተኛ ጠቀሚ ንጥረ ነገሮች አማካኝነት የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ስርዓት ለማጠናከር አይነተኛ አማራጭ ነው።

3. በቂ እንቅልፍ መተኛት

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለማችን ላይ በአዋቂ የእድሜ ክልል ላይ ካሉ ሰዎች ውስጥ ሁለት ሶስተኛው በቂ እንቅፍ አይተኙም። በቂ እንቅልፍ አለመተኛት አጠቃላይ ጤናችን ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያመጣ እሙን ነው።

እንደ ድርጅቱ ገለፃ አንድ ሰው በቂ እንቅልፍ ለማግኘት በቀን በአማካኝ ለ8 ሰዓታት መተኛት ይኖርበታል። ስለዚህ በቀላሉ ለበሽታዎች ላለመጋለጥ በቂ እንቅለፍ መተኛታችንን ልብ ልንለው ይገባል።

4. ውሃ አብዝቶ መጠጣት

ውሃን አብዝቶ መጠጣት የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ስርዓት እንዲጠንክር ያደርጋል የተባለ ሲሆን፥ በተለይም ኩላሊታችን መርዛማ ነገሮችን አጥቦ ከሰውነታችን ወስጥ እንዲያስወግድ ይረዳል።

ምንጭ፦ www.independent.co.uk