ለፍቅር ብተኛት ለጠብ አረገዘች(ፌዛፌዝ ጨዋታ!): Dereje Minlargih

0
296
ለፍቅር ብተኛት ለጠብ አረገዘች ሁለተኛ ባሌ ነክ
Facebook image

ለፍቅር ብተኛት ለጠብ አረገዘች(ፌዛፌዝ ጨዋታ!)
(ደሬ ምንላርግህ)
. . .
ሚስቴን- ሚስቴኬን “ሊሊዬ!” ነው የምላት!
ስሟ ልዕልና እንዳይመስላችሁ!:: ሊስትሮ ይመስል እግሬ ስር ስለማትጠፋ ነው! ቂቂቂ…. ሁሌም እንዳጠፋች፣ “የዛሬን ማረኝ?! አይለመደኝም?!” እንዳለችኝ ስለሆነ ነው፣ ምጅምርታ “የኔ ሊስትሮ!”፣ ኋላም “ሊሊዬi” ብያት የቀረሁ ቂቂቂ….
ሊሊዬ! የኔ ታጥቦ ጭቃ! ተመልሳ እዚያው ናት፡፡
ግን እኮ ነፍሴ እስክትወጣ ነው የምወዳት፡፡ ስታቃጥለኝም፣ እርር! ድብን! ስለምታረገኝ አልፈልግምንጂ ዓይኗን ማየት፡፡
.
ሊሊዬን፣ ተግባቡ እንጂ ተጋቡ በማይለው የቢሮ ህይወት፣ እኔ ጉዱ ግን ሳልግባባት አገባኋት፡፡ ይሄው ነው ቀዳማዩ ጥፋት!

……….ጭቅጭቅ 11
ገና ተመጋባታችን፣ “ወልደን ካልሳምን?!” አለችኝ፡፡ “ቆይ እንጂ እኛ እንሳሳም?!” ብላትም፣ ወይ ፍንክች!፡፡ “ታልሆነ አልጋ እንለይ! በከንቱ አልጋውንም፣ እኛንም አናድክም!” ብላ ወገቧን በጇ አሰረችልኝ፡፡ “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ?” አለ ያገሬ ሰው፡፡ “ለመከራ የጣፈው ቢነግድ አይተርፈው” የተባልኩትኮ እኔ ነኝ ጎበዝ! ቂቂቂ……
“ደሬ አገባ?! ይገርማል?! ክፉ ሰው ነበር፤ ይገባዋል! እንኳን አገባ!” ብሎ ያላገጠብኝ ያ የድሮ ወዳጄ ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ቂቂቂ….
.
መጣችልኛ! የሆነ ዕለት፣ በጇ ይዛ አረገዝኩኝ ውጤት፡፡ መጣችልኛ! “Oh my God?!!!” እያለች በደስታዋ እብደት፡፡ እኔም ሾፍ አርጌው የሆዷን ሞላ ማለት፣ “ልጅ ከሆነ ይወለዳል፣ ድንች ከሆነም ይጎላል” ብዬ በሆዴ፣ እብስ ብዬ ወጣሁ ተቤት፡፡
ቆይ ብቻ ይወለዳት፣ ባልጠፈጥፈው ደሞ እሷን ላበሽቃት! ቂቂቂቂ……. አይ አነ ፍም እሳት?!

ጭቅጭቅ 12
“ጽንሱን ካልተከታተልነው!” አለችኝ ደሞ፤ ገና ሳይወጣልኝ የሀዘኔ ነገር፣ የማርገዟ ጉዳት፡፡ “ለምንድን ነው የምንከታተለው?! ኧረ ተይ አንቺ ሰው?! የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ! አንቺም ይሄ ያባትሽ ነገር አለቅሽ አለ?!” አልኳት፡፡
አባቷ ደንነት ነው፡፡
“አለሰማክም! ካልተከታተልነው ሞቼ እገኛለሁ!” አለችኝ፡፡ “አርጎት ነው?!” አልኳትi
“ገበሬ እንኳ ዘር መዝራቱን እንጂ፣ የዘራው ዘር አብቦ ከመሬት ውስጥ ብቅ እስቲል ድረስ፣ በመሬት ውስጥ ሳለ እየሆነ የነበረውን የእግዚሃርን ሚስጢር ያውቃልን?! ለምንድን ነው እኛስ ጽንሱን የምንከታተል?!” ብዬ ላሳምናት ብሟሟትም፣ ወይ ፍንክች እቴ እሷ፡፡
እኔኮ ምን ስል ስቀብጥ እንደተዳርኩ ነው እሚቆጨኝ! …. መዳር ማለትኮ መዳራት ብቻ ነበር እሚመስለኝ ቂቂቂ….
.
“ሳውቀው ገብቻለሁ!” አለ ያገሬ ሰው! ገና እኮ ያኔ….ተመዘጋጃ ቤት ውል ይዘን ስንወጣ ነው፣ በሩ ላይ መጠዝጠዟን የጀመረችኝ፡፡ ያን ቀን ላየን ሰው፣ ተጋብተን ሳይሆን ተፋተን እየወጣን ነበር የምንመስለው!(ለካን ስንፋታ አብረን አንወጣም! ቂቂቂ… አይ ሰው እኛ?!)
“ስማ እንግዲህ አቶ ባል! ከሰርጋችን በኋላ ግን ይሄን ጫት መቃምክን ታቆማለክ!” አለችኝ ጣቷን ዓይኔ ላይ ቀስራ!
“እና ምን እቅማለሁ?!!!” አልኳታ! ቂቂቂ….
ሌሎችን ማዕቀቧን ቀጠለች!፡፡ አይ ሊሊዬ?! ቀደምት ኮማንድ ፖስቴኮ ናት! ለዚህኮ ነው እኔ የይሃዲግ ነገር ብዙም የማይደንቀኝ! ቂቂቂ….
“ስሚ የኔ እህት! እንዴውም ብዙ ሳንርቅ፣ አሁኑኑ ተመልሰን ውላችንን እንቅደድ! አባባሉም ውነት ይሁን- ፊርማው ሳይደርቅ!” አልኳትና ከኋላዋ ቀረሁ፤ ተገትሬ ቆምኩ! የምሬን ነበር፡፡
“ትገርመኛለህኮ ጥጋብህ! በዚች ዘነዘና ቁመትህ!” አለችኝ፡፡ ደሞ ለመልስ ምት?! “ዘነዘና እንዴት እንደሚወቅጥ አይተሻል!” አልኳታ! ቂቂቂቂ……
.
ይሄው ጭቅጭቅ ቀለባችን እንደሆነ ደና አርጎ ቀጥሏል!!!
እንዴው ምን አለፋችሁ፣ በቅርቡማ “ፖሊስና ርምጃው” ላይ ጠብቁን!!! ውነቴን ነው ጠብቁን! እንመጣለን በቅርብ ቀን!!! ቂቂቂ…. ጎረቤቴም አስቀድሞ ሁኔታ ስለሞላብን፣ እንዴውም በቀጥታ ስርጭት እሚተላለፍ ይመስለኛል የኔና ሊሊዬ ክትክት!!! ቂቂቂ…..
.
…..ይሄው! ይሄን ያልታደለ ጥንስስ ህጻን፣ እንደጉድ ትከታተለዋለች፡፡
በሆዷ የያዘችው እሷ እያለች፣ ምን እንደሆነ ንገሩኝ?! እያለች ሀኪሞችን ትጨቀጭቃለች፡፡ ከተወለደም ይማርበታል ያልኩትንም ፍራንክ በያሳምንቱ እየሔደች ትገብረዋለች! ለናቶችና ህጣናት ጤና ጣቢያ ቤት፡፡
.
“ስማ ደሬ! እኔኮ አሁን ይሄ ፎቅ! ምናምን ባለው ሰው እንዳይመስልህ የምቀናው! ባላገባ ወንድ እንጂ!” ይለኝ ነበር ወዳጄ ጆኒ- ሚስቱ ደና አርጋ ለኩሳው ከቤቱ በወጣ ቁጥር፡፡ የሲጃራውን ሳይሆን የሆዱን ጭስ ይመስለኝ ነበር የሚያትጎለጉለው፡፡
“ውነቴን ነው እምልህ! እኔ እንዴው ሚስት ከማግባት ፓርላማ መግባትን እመርጣለሁ! ፓርላማ እኮ የምትጨቃጨቀው ከማታውቀው ሰው ጋ ነው! እንዴት ከምታውቃት ሚስትህ ጋ እንዲህ ትጨቃጨቃለህ?!” ብሎ ቀጠለ ደሞ የሆነ ቀን፡፡
“እንዴ ጆኒዬ?! የኛን አገር ፓርላማ እንዳይሆን መቼም የምትለኝ?!!! ዝም ጭጭንና ጭቅጭቅን እንዴት ነው መለየት ተሳነህ?!” ስለው ነበር ዲስኩሩን የተወው፡፡
(እድሜ ለሷ! ይሄው ስንት ጊዜ የሆነንን! የረሳሁትን ጆኒዬን አስታወሰችኝ፡፡ ጭር ባለ ህይወት ውስጥ ትዝታ እሚመጣ እንዳይመስላችሁ ጎበዝ! ምንም ሆነ ምን መለኮስ አለባችሁ! ቂቂቂቂ…)

ጭቅጭቅ 13
ደሞ ዛሬ ማታ፣ ልንተኛ ስንዘገጃጅ፣ የኔ ሊስትሮ! ሊሊዬ!- “እኔ ምልክ ደርዬ!” አለችኝ፣ እግር እግሬን እያየች፡፡ “ወይ መከራዬ?! ደሞ ምኑን ልታመጣው ነው?!” አልኩ በሆዴ፡፡
ሊሊዬ፣ ነገር ልትፈልገኝ፣ ልትነቁረኝ ስትል “አቶ ባል! አቶ ደረጀ!” ነው የምትለኝ፡፡
ማረኝ?! ልትል፣ ወይም የሆነ ነገር እንዳደርግላት ስትፈልግና በጅ በግሬ ገብታ ልትለማመጠኝ ስታስብ ደሞ- “ደርዬ!” ትለኛለች፡፡
“ስሜ ደረጀ ነው!” እላታለሁ- የውሸት ስገግምባት፡፡ “እሺ ደረጀዬ!” ትለኛለች፡፡ “ ‘ዬ’ን ምን አመጣው?!!! ደረጀ ብቻ አትይኝም?!” ብዬ በአገጬ ግትር! እልባታለሁ፡፡ ቂቂቂቂ……
በርግጥም፣ ብዙ ጊዜ፣ ይቺን ቁልምጫ- ይቺን “ዬ”ን ቅጥያ አልወዳትም፡፡ አጉል ውድቀት ይዛ ነው የምትመጣው ጎበዝ!
ደና እንደልቧ በሰማይ ላይ ትበር የነበረውን ዳክንም- “ዳክዬ!” ብለው ሲያቀብጧት ነው ዘጭ! ብላ ወደቃ ይሄው እንዲህ ባህር ላይ ተዘርፍጣ የቀረችው፡፡ ቂቂቂ….
ፓፓስ ብቶን?! “ፓፓ” ተብላ አልነበረም እንዴ ዛፍ ላይ በክብር ትኖር የነበረው?!፡፡ ይሄው! ይቺን “ዬ”ን ቀጠሉላትና “ፓፓዬ!” ሲሏት ጊዜ፣ ዘጭ! ብላ መሬት ላይ ወደቀቻ! ይሄው ማንም ሲገምጣት ይኖራል፡፡ ቂቂቂ…..(የሽዌና ወዙ ተባራሪ ጨዋታ ናት!)
ውነቴን ነው ጎበዝ! ከልብ ክፋትና ከዚች አሳሳች “ዬ” መራቅ ነው! ሃሳይ ቁልምጫ ናት፡፡
.
እናም ሊሊዬ! “እኔ እምልክ ደርዬ….” ብላ ጉዷን ጀመረችልኛ- በዚህ የምሽት ጨለማ፡፡ ወይ መከራዬ?! Nowhere to go! አለ እንግሊዘኛው፡፡
“በቃ ይቺን ብቻ የመጨረሻዋን ጥፋቴን- ሚስጥሬን ልንገርክና ከዚህ በኋላ ንስሃዋን የጨረሰች ንጹህ ሚስትክ ልሁንክ!” አለችኝ፤
“እ?! መዳኒያለም ይከካሽ!፡፡ ኧረ ተይ ይሄን ክ ማለትን?!”
“እሺ እተዋለሁ! ጌታን!!!” አለችኝ፡፡
“የ..ባሰው መጣ?! ደሞ ይሄን በሌሎች ሰዎች ላይ የምጠላውን- ‘ጌታን!’ እያሉ መማልን ጭራሽ አንቺም ጀመርሽልኝ?!….. ኧረ ተይ አንቺ ሴት?! ፈጣሪ አምላክ እግዜር በፍጹም ጥሞናና ክብር ነው ስሙ ሊጠራ የሚገባ! ይሄሄ… ዕቃ በወደቀና ታክሲ ፍሬን በያዘ ቁጥር፣ እንደ ተራ ወዳጅሽ ሁሉ- ‘በኢየሱስ ስም!’ እያልሽ መጮህሽን ተይ ብልሽም ይሄው እምቢ ብለሽ እንደቀጠልሽበት ነው! ጭራሽ ደሞ ‘ጌታን!’ ማለትም ጨመርሽበት?!” ከልቤ አበድኩባት!
እንደተለመደው መልሷ፣ “ደርዬ ድረስ!!! ስለማልልክ ቀንተክ ነው!” ትለኛለች ብዬ ስጠብቅ፣ “እሺ በቃ የኔ ማር! ይቺን ብቻ የደበኩህን ሚስጥሬን ልንገርህና ይቅር በለኝ እንጂ ከዚህ በኋላ አልልም!!!” ተማጸነችኝ፡፡
ካልታዘልኩ አላምንም ነውና “እውነት በይኝ እስኪ?!” አልኳት
“ጌታን!!!” አለችኛ፡፡ ኧረዲያ! ምን ያለው አሞራ ከዛፍ ይሟገታል?!….. አለ ያገሬ ሰው፡፡
.
“በቃ ልንገርክ?!” አለችኝ፡፡ ዝም ብዬ አየኋት፡፡ ቀጠለች!
“ካንተ በፊትኮ ሌላ ባል አግብቼ ነበር… በሰርግ፡፡ አንተኮ ሁለተኛ ባሌ ነክ!” ብላኝ እርፍ! የስ…ላ…ሴ ያለህ?! ከዚህ በላይማ መብረቅስ መች ይመታኛል?!
ደሞ እኮ እምትገርመኝ፣ ይሄእእ…. ማለሳለስ፣ አለስልስ እሚባለውን የጭፈራ መግቢያ አታውቀውም፡፡ መንጭቃ ነው የምትነሳው! ዱብ ዕዳ ነው የምታረገው ነገሯን፡፡ እንዲያው ለቡናዋ ቁርስ፣ ለነገሯ ለዛ የሌላት ፍጡር!!! እህህህ…..
.
“አንተኮ ሁለተኛ ባሌ ነክ!” አለችኛ! It is okay ሃኒዬ! እላት ይመስል፡፡
“ሎሚና ትርንጎ ሞልቶልህ ባገር፤
እንቧይ ታሸታለህ የድሃ ነገር” የተባለው ነገር ይሄው እኔ ጋ ከች አለልኛ!
ወይ አነ?! “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል” ነው እንዴው የኔ ነገር፡፡ እንጉርጉሮ ትዳሬ ሆኖ ይቅር?!
“አንተኮ ሁለተኛ ባሌ ነክ!” ተባለልኛ! “ጥሩ ነው! የዳበረ ሲቪ ነው ያለሽ!” እላት ይመስል፡፡
“ድሮስ የተነዳ መኪናን የማላውቅ መስሎሽ ነበር?!” ብዬ መለስኩላት፡፡ ባልላት ጥሩ ነበር፡፡
.
ደሞ…. ማንቴስ ነው አለችኝ ስሙን- ይሄእእ ተኔ በፊት አግብቷት ሰፈፉን የወሰደውንና ፈቶ የለቀቀብኝን ክፉ ሰው፡፡ ይዤዋለሁ እዲያ!…. ካሳ ነው ያለችኝ- ይከስክሰውና! እንደ ኮሶ መሮኛል ለራሴ፡፡ ቂቂቂቂ…. የታባቴንና! ይበለኝ! እኔን ብሎ ባል! ቂን ቂን! ብዬ ያመጣሁት ዕዳ ነው!
.
ሊስትሮዬ! ሊሊዬ! እንደቀጠለች ነው ኑዛዜዋን!……
“ከካስሽ ጋር አራት ዓመት ብቻ ነው በትዳር የቆየነው፡፡ ግን በቃ ልጅ መውለድ ስላልቻልን ተለያየን፡፡ ወልደን ካልሳምን ብዬ ያኔም እኮ የቸኮልኩብህ እእእ….” እያለች ስትጎትትብኝ፣ “ለመሀን እምዬ፣ ላገልጋይ እትዬ ብርቋ ነው!” ያልኳት መሰለኝ፡፡
“ለቅሶ ሳለ ከቤት ለቅሶ ይሄዳል ጎረቤት” አለ ያገሬ ሰው- የኔን ዓይነቱን ሰው፡፡ ልትደርቅ የደረሰች ምንጭ ጭል ጭል ትላለች ነውና፣ የትዳሬ ነገር ሲያበቃለት አየሁት፡፡
እሷ ቀጥላለች! ኑዛዜዋን….
እኔ ግን ደንዝዤ፣ ወደ ኋላ ተምዘግዝጌ ሄጄ፣ ያኔ ስንጀምር ያጃጃለችኝን፣ የመጀመሪያዬ እያለች የዘፈነችልኝን፣ ያን የድራማዋን ነገር እያሰብኩት ነው! የለሁም! ሔጃለሁ ባሳብ ንጉደት….
ደስ የሚለው ግን፣ ጥሎ አይጥሉ ጌታ ከሀዘን ውጣ ሲለኝ፣ ድሮ በባለ ትዳሩ ጓደኛዬ ላይ የተከሰተችው ያቺ የስርቆቱ ዱብዳ ጨዋታ ድንገት ድቅን አለችብኝና ሳቅ ጉንጬን አሸሻት፡፡ ለሊሊዬም ሳልገርማት አልቀረሁም! መርዶ እየተነገረው በሚስቀው በባሏ እኔ ጉዳይ፡፡
እናም እላችኋለሁ፣ ያኔ…. ኤች አይ ቪ እንደ ጉድ በተንሰራፋበት ዘመን እኮ ነው፣ ይሄ ባለትዳሩ ጓደኛዬ፣ ጎጃም ውስጥ ያለች ትንሽ የወረዳ ከተማ ለስራ ጉዳይ ሄዶ፣ አልጋ የያዘበት ቡና ቤት ውስጥ አንዲት ልጅ እግር፣ ገና አንድ ፍሬ የገጠር ጉብል ግቢውን አጎንብሳ ስትጠርግ ያያትና ይቋምጣል፡፡ እንደ ጅብ ጎምዥቶ፣ እንደ ውሻ ለሃጩን አዝረብርቦ ተመኛትና፣ በለስ ቀንቶትም በድብቅ ይዟት ተኛ(ወይ በለስ መቅናት እቴi…… የበለስ እሾህ ደና አርጎ ጠበሰቀው እንጂ! አፈር ልብላለት ወንድሜ! ቂቂቂቂ…..)
ለዚች አደይ አበባ፣ ልጃገረድ ጉብልማ የታባቱንና ኮንዶም! ብሎ ሌጣውን ነው የገባው!!! ቂቂቂ….
የአንሶላ ማጠቢያማ ያስከፍሉኛል እያለ በስጋት ቢገባም፣ ምንም ወፍ የለም! እጅግ ሰላም ነው! ሰፊ አገር ልጅ እግር ናት፡፡
ተጀመረልኛ ጨዋታው!
…..እናም፣ ተፈጣጥመው እንደጨረሱልኝ፣ ይቺ ልጅ እግር እህታችን ደረቱ ላይ ልጥፍ ብላ ተኛችበት- ደስ ብሏት፡፡ ሰውያችን ግን፣ ቆሌው ተገፎ፣ እንዲያ ኤርታሌ ሆኖ የገባው ደና አርጎ ቀዘቀዘና፣ ሲጃራውን ለኩሶ፣ ዓይኑን ጣራው ላይ ተክሎ በነገሯ ጉዳይ ግርምርም ብሎት ሲብሰለሰል ቆዬና…
“እኔ እምልሽ?! እንዴት ግን ወላጆችሽ ገጠር አልዳሩሽም?! እንዴት ባል አላገባሽም?!” አላት፡፡
“ኧረ አግብቼ ነበር እሱስ!” አለቺዋ! ቂቂቂቂ…..
“እና ለምን ተፋታሽ?!”
“ኧረ አልተፋታሁም ነበር እሱስ!”
“እና ታዲያ…? ልጅስ? አልወለድሽም?!”
“ኧረ ወልጄ ነበር እሱስ!”
ቂቂቂቂ…
“እና ታዲያ ለምን እዚህ መጣሽ?!” (ቂቂቂ… “እና ታዲያ”ን እንደዚች ቀን ወዲያው ወዲያው ብሏት አያውቅም!)
“እእእ…. አብረን ስኖር ስኖር… ባሌ በጠና ታመመና፣ አንዴ ሳንባ ነው! አንዴ ቲቪ ነው! አንዴ ምንቴስ ነው! እያሉት፣ ደረቅ ሳል ውልቅ አርጎ አድክሞት… ከስቶ መንምኖ ሞተ!” አለችው፡፡
በረዶ ሆነ ወዳጃችን! እሷ ግን ተረት ተረት እንደመንገር ነበር ምንም ያልመሰላት፡፡
“እና ሌላ ባል አላገባሽም?!”
“ኧረ አግብቼ ነበር እሱስ!” ቂቂቂቂ….. ኧረዲያአያ!
“እዋ?! እና እሱስ?! ለምን ፈታሽው?!”
“ኧረ አልፈታሁትም ነበር እሱስ!” ቂቂቂ…
“እና?!” አላት፣ የበሰበሰ መች ዝናብ ይፈራና!
“እሱምእእ… እንደ መጀመሪያው ባሌ ዓይነት ህመም ታሞ፣ ተቅማጥ ተውከት! ተቅማጥ ተውከት! አጣድፎት፣ ደረቅ ሳል አድክሞት… ከስቶ መንምኖ፣ ይቺን አክሎ ሞተ!…. እንዴውም የመጀመሪያው ባሌ ቤተሰቦች እሱን ወዲያው በማግባቴ ጠምደውት ስለነበር- ‘ሳጥን ምን ያረጋል?! በኩርቱ ፌስታል አንቀብረውም ወይ?!’ ብለው ቀለዱበት አሉ” አለችውና ጧ! ያለ እንቅልፍ ወዲያው ወሰዳት፡፡ ቂቂቂ…..
አባዎራው! ወንድማችን ሆዬ ግን እንቅልፍ አልባው ሌሊት እጅግ እረዝሞበት፣ እንዳይነጋ የለም በጉዱ ነጋበት! ቂቂቂቂ….. እንግዲህ እንደ መግባት አይቀል ሂወትን ሲወጡት! ኧረዲያአያ! አፈር ልብላይእ!
.
እና ታዲያ…. ይሄንኑ ዓይነት ጅጤ ነው፣ የኔዋ ሊስትሮ- ሊሊዬም ዱብዳዋን ያከናነበችኝ! አንተኮ ሁለተኛ ባሌ ነክ! ብላ ያቀዘቀዘችኝ ቂቂቂቂ…..
ምንም አዲስ ነገር የለም ተሰማይ በታች፤ ይሻላል እንጂ አለማወቅና አለመስማት፡፡
ጭርሰናል ጎበዝ! ደና ሰንብቱ! ይሄው ነው ለዛሬ ከጉዳችን ጓዳ የዘከዘኩላችሁ ጉደ-ጨዋታ!!!
ተግባቡ እንጂ ተቻኩላችሁ አትጋቡ ባይ ነኝ! እንደኔ እንደኔ! ቂቂቂቂ…… ኧረዲያአያ! መምከሩ ቀርቶብሽ ላንቺው ባወቅሽ ዓይነት ፌዝ ስትፈተልብኝ ይሰማኛል ከሩቅ፡፡ ቂቂቂ……
ቻው ጎበዝ!!! ሚስቶች ለዘላለም ይኑሩ፤ ባሎች ሲለኮሱ እንዲኖሩ!!! ቂቂቂ…