Babani Sissoko, The “Black Magician” (ዓለም አቀፉ ምትሃተኛ’): BBC

0
921

ጊዜው በፈረንጆቹ ወርሃ ነሃሴ 1995 ዓ.ም.፤ ፎቱንጋ ባባኒ ሲሶኮ የተባለ ግለሰብ ወደ ዱባይ እስላማዊ ባንክ ጎራ ይልና “መኪና ልገዛ ነው ብድር ስጡኝ” ይላል። የባንኩ ስራ አስኪያጅ ሞሃመድ አዩብም “ምን ገዶን ዕዳህን በጊዜው ክፈል እንጂ” ይለዋል። በዚህ የተደሰተው ሲሶኮ ስራ አስኪያጁን “ፈቃድህ ሆኖ እራት አብረን እንበላ ዘንድ እንዳው ቤቴ ብቅ ብትል” ሲል ግብዣ ያቀርባል። በዓለማችን ከታዩ አስደናቂ ማታለሎች አንዱ የሆነው ታሪክ የሚጀምረው እንዲህ ነው። የቢቢሲዋ ብሪዢት ሺፈር እንዲህ ታቀርበዋለች።                            እራት እየበሉ ሳለ ሲሶኮ ለስራ አስኪያጁ አንድ አስደናቂ ታሪክ ያካፍለዋል። “አንድ ኃይል አለኝ” ይለዋል. . .ይህን ኃይል ተጠቅሜም ገንዘብ እጥፍ ማድረግ እችላለሁ። እንደውም በሚቀጥለው ጊዜ የተወሰነ ገንዘብ ይዘህ መጥተህ ለምን አላሳይህም?” ሲል ሲሶኮ ጥያቄ ያቀርባል። ምትሃት በእስልምና የተወገዘ ሲሆን እንደ ትልቅ ኃጥያትም የሚቆጠር ነው። ቢሆንም በርካታ ሰዎች በምትሃት ያምናሉ። ሞሃመድ አዮብ ከአንድ ከከተማ ራቅ ብላ ከምትገኝ የማሊ ገጠራማ ሥፍራ ወደመጣው ሲሶኮ ገንዘቡን ይዞ ተከሰተ። ልክ በሩን ከመርገጡ አንድ ሰው ከውስጥ ወጥቶ “መንፈስ (ጅኒ) መታኝ” ይለዋል። “ወደ ውስጥ ስትገባ ጅኒውን እንዳታበሳጨው ጠንቀቅ በል፤ ያለዚያ ገንዘብህ እጥፍ አይሆንም” ሲል ይነግረዋል። አዩብም ወደውስጥ ከዘለቀ በኋላ ገንዘቡን አስቀምጦ እጥፍ እንዲሆንለት በጥሞና ይጠብቅ ጀመር። “ድንገት ከክፍሉ ውስጥ መብራት እና ጭስ እንዲሁም የመናስፍቱ ድምፅ መውጣት ጀመረ” ይላል አዩብ። ለጥቆም ገንዘቡ እጥፍ ሆነለት፤ አየብም ፊቱ ፈካ። በአውሮፓውያኑ 1995 እስከ 98 ባለው ጊዜ ብቻ አዩብ ለሲሰኮ ምትሃቱን ተጠቅሞ ገንዘቡን እጥፍ እንዲያደርግለት በማለት 83 ጊዜ በባንክ ደብተሩ አማካይነት ገንዘብ አስገብቶለታል፤ ገንዘቡ የባንኩ መሆኑ ሳይረሳ። 98 ላይ የዱባዩ ባንክ እየከሰረ መሆኑ መዘገብ ያዘ። ዜናውን ያነበቡ የባንኩ ደንበኞችም ገንዘባቸውን ለማውጣት በየቅርንጫፉ ተሰለፉ። ቢሆንም የዱባይ ባለሥልጣናት ዘገባው ሃሰት የተሞላ ነው እንጂ ባንኩ የገንዘብ እጥረት አልገጠመውም ሲሉ ተደመጡ። እውነታው ግን ይህ አልነበረም። ኋላ ላይ በጉዳዩ ጣልቃ የገባው የዱባይ መንግሥት ባንኩን በገንዘብ በመደጎም ራሱን ችሎ እንዲቆም አደረገው።ይህ ሁላ ሲሆን ታዲያ ሲሶኮ በጣም ሩቅ ሥፍራ ነበር፤ ምትሃቱን የበለጠ ድንቅ የሚያደርገው ደግሞ ገንዘቡን ለማግኘት ዱባይ መገኘት ግዴታ አለመሆኑ ነው። ጊዜው ጥቅምት 1995…ምትሃቱን በሞሃመድ አዩብ ላይ የተጠቀመው ሲሶኮ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ኒው ዮርክ በማቅናት ተመሳሳይ ድርጊት ፈፀመ። ሲቲባንክ የተባለ ባንክ በመዝለቅ አንድ የደንበኞች አገልግሎት ሠራተኛ ተዋወቀ፤ ትንሽ ቆይቶም አገባት። ይህንን ተጠቅሞም ከሲቲባንክ ጋር ያለውን ግኑኝነት ማሳመር ቻለ። ሲሶኮ ከሲቲባንክ ወደ ዱባይ እስላማዊ ባንክ ደብተሩ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳስተላለፈም ይታመናል፤ ለዚህ የረዳችው ሚስቱን በረብጣ ዶላሮች እንደካሳትም ተነግሯል። ስለሲሶኮ ይህንን መረጃ የሚናገሩት የዱባዩ ባንክ በጉዳዩ ላይ ክስ በከፈተ ጊዜ ጠበቃ አድርገው የቀጠሩት አለን ፋይን ናቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ምትሃቱን ተጠቅሞ ገንዘብ ማፍራቱን የቀጠለው ሲሶኮ ምኞቱ የነበረውን በምዕራብ አፍሪካ አየር መንገድ መክፈት ያመቸው ዘንድ ቦይንግ አውሮፕላን ገዛ። አየር መንገዱን በትውልድ መንደሩ ስም ዳቢያ ብሎ ሰየመው። ነገር ግን ወርሃ ሐምሌ 1996 ላይ ሲሶኮ አንድ ስህተት ሠራ። ሁለት ከቪየትናም ጦርነት የተረፉ ሄሊኮፕተሮች ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ለመግዛት ሞከረ። ሄሊኮፕተሮቹ ለጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ በመሆናቸው ምክንያት ለመብረር ልዩ ፍቃድ ያሻቸዋል። ይህን ያስተዋሉት የሲሶኮ ሰዎች ፖሊሶችን ለመደለል ሲሞክሩ ለእስር በቁ። ዓለም አቀፉ ኢንተርፖልም ሲሶኮ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ትዕዛዝ አወጣ። ሌላ የባንክ ደብተር ለመክፈት ወደ ጄኔቫ አቅንቶ የነበረው ሲሶኮ በቁጥጥር ሥር ዋለ፤ ለጥቆም ወደ አሜሪካ ተላከ። ምንም አንኳ የአሜሪካ መንግሥት ሲሶኮ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ቢፈልግም በ20 ሚሊዮን ዶላር ዋስ እንዲለቀቅ ሆነ።                                                                               ሲሶኮ ለዚህ ላበቁት የህግ ሰዎች ውድ የሚባሉ መኪኖችን ሸለመ። አንድ መኪና ሻጭ ሲሶኮ ቢያንስ 53 መኪናዎችን ገዝቶኛል ሲል ይናገራል። ነዋሪነቱን ማያሚ ያደረገው ሲሶኮ በከተማዋ ታዋቂ ሆነ፤ በርካታ ሚስቶችንም አገባ፤ 23 አካባቢ አፓርትማዎችንም ተከራየ። ሲሶኮን የሚያውቁት ግርማ ሞገስ ያለው፣ አለባበሱ ያማረ እና መልከ-መልካም ሰው ነው ሲሉ ይገልፁታል። አልፎም ከገንዘቡ ወደ 413 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለእርዳታ አዋሏል። ጠበቃዎቹ ከነበሩ በርካታ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ስሚዝ የተባለ ሰው ሲናገር ሲሶኮ ዘወትር ሃሙስ በመኪናው እየዞረ ለቤት አልባ ሰዎች ገንዘብ ያድል ነበር። የጠበቃዎቹን ምክር አልሰማም ያለው ሲሶኮ ጥፋተኛ ነኝ ሲል አመነ። ለ43 ቀናት እሥር እንዲሁም ለ250 ሺህ ዶላር ቅጣትም ተዳረገ። ከተፈረደበት ፍርድ ግማሹን የፈፀመው ሲሶኮ 1 ሚሊዮን ዶላር ለቤት አልባ ሰዎች በመስጠት የተቀረውን ፍርድ በቤት ውስጥ እስር እንዲጨርስ ሆነ። በዚህ ጊዜ ነው ታድያ የዱባዩ እስላማዊ ባንክ ኦዲትሮች የሆነ ነገር ትክክል እንዳልሆነ መጠርጠር የጀመሩት። አዩብም ፀባዩ መለዋወጥ ታየበት፣ ሲሶኮም እንደ ድሮ በተፈለገ ጊዜ ስልክ አላነሳ ማለት ይጀምራል።በስተመጨረሻም አዩብ ለሥራ ባልደረባው ያጋጠመውን ይተነፍሳል። “ምን ያህል ብር ነው የጠፋው?” ሲል ለጠየቀው ጓደኛው በቃላት ምላሽ መስጠት የተሳነው አዩብ በብጣሽ ወረቀት ፅፎ ያቀብለዋል. . .242 ሚሊዮን ዶላር።                                                                                            በዚህ ጉዳይ ጥፋተና ሆኖ የተገኘው አዩብ የሶስት ዓመታት እሥር ይፈረድበታል፤ “በምትሃት አምነሃልና ሸይጣንህን እናስወጣልህ” ተብሎ በኃይማኖቱ መሠረት ሸይጣን ማስወጣት እንደተካሄደለትም ይነገራል። አዩብ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ሲያልፍ ሲሶኮ ግን ዱባይ ሊገኝ ባለመቻሉ ምክንያት በሌለበት የሶስት ዓመታት ፍርድ ይወሰንበታል። ዓለም አቀፉ ፖሊስ ‘ኢንተርፖል’ ግን “አፈልገዋለሁ” ሲል ማስታወቂያ ይለጥፋል። ሲሶኮ ለ12 ዓመታት ያክል ማለትም በአውሮፓውያኑ ከ2002 እስከ 2014 ባለው ጊዜ በማሊ የሕዝብ እንደራሴ ሆኖ በመሾሙ ምክንያት ያለመከሰስ መብቱ ተጠብቆለት ቆየ። ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ ሃገሩ ማሊ ወንጀለኞች አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ከየትኛውም ሀገር ጋር ስምምነት ባለመፈረሟ ምክንያት ያለ ምንም ስጋት ሕይወቱን እያጣጠመ ኖረ። ከዚያ በኋላ ነው ሲሶኮን ፍለጋ ወደ ማሊ ርዕሰ መዲና ባማኮ ያቀናሁት ትላለች የቢቢሲዋ ብሪዢት። ከዚያም የሲሶኮ ሹፌር የሆነውን ሉካሊ ኢብራሂምን ታገኘዋለች። በትውልድ መንደሩ ዳቢያ ሊኖር እንደሚችልም መረጃው ለብሪዢት ይደርሳታል። ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ብሪዢት ሲሶኮ መኖሪያ የተባለው ቤት ትደርሳለች፤ በወታደሮች የሚጠበቅ ሰፋ ያለ ግቢ። በስተመጨረሻም ሰውየውን በአካል ታገኘዋለች. . .የሰባ ዓመቱን ‘ምትሃተኛ’ ፎቱንጋ ባባኒ ሲሶኮን። ለቃለ-መጠይቅ ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘው ሲሶኮ “ስሜ ፎቱንጋ ባባኒ ሲሶኮ ይባላል። የተወለድኩ ዕለት ማሪየቶ ወንድ ልጅ ወለደች በማለት ሰፈሩ ቀለጠ” በማለት ታሪኩን ለብሪዢት መተረክ ይጀምራል።“እንደው ከዱባዩ እስላማዊ ባንክ ጠፋ ስለተባለው 242 ሚሊዮን ዶላር የምታወቀው ነገር ይኖራል?” ለሲሶኮ የተሰነዘረ ጥያቄ ነው። “እመቤት…ይህ 242 ሚሊዮን ዶላር የማይመስል ታሪክ ነው። የባንኩ ሠራተኛ ቢያስረዳሽ ነው የሚሻለው እንጂ ያን ያክል ገንዘብ ሲጠፋ መቼም ዝም ብለው አይቀመጡም። በዚያ ላይ ይህን ያህል ገንዘብ ከባንክ ለመውሰድ በርካታ ቢሮዎች መሄድ አለብሽ።”

“አዩብ ግን. . . ?” ብሪዢት የሰነዘረችው ጥያቄ። “አዩብ የባንኩ ሠራተኛ? አዎ እሱን ሰውዬ አንድ ጊዜ አግኝቸዋለሁ። መኪና ለመበደር የሄድኩ ጊዜ። ምርጥ የጃፓን መኪና ነበረች። ዕዳዬንም በጊዜው ከፍዬ ጨረስኩ” የሲሶኮ ምላሽ። ጋዜጠኛዋ በስተመጨረሻም ስለ ‘ምትሃት’ ጠየቀችው። “እመቤት አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ኃይል ካለው ለምን ይሠራል? ቁጭ ብሎ ባንክ እየዘረፈ መብላት እየቻለ። ቢፈልግ ከአፍሪካ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ ያሻውን ባንክ እየዘረፈ መኖር ይቻል አልነበር።” “እና አሁንስ ሃብታም ነህ?” “ኧረ በጭራሽ። እኔ ሃብታም አይደለሁም። እንደውም ደሃ ነኝ።” ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ ፖሊስ ‘ኢንተርፖል’ አሁንም ሲሶኮን ፍለጋውን ቢቀጥልም፣ ምንም እንኳ በርካታ ገንዘብ አፍርቶ ቢያጠፋም ፎቱንጋ ባባኒ ሲሶኮ በሃገሩ ማሊ በጤና ኑሮውን እየገፋ ይገኛል።