የጉራ ፈርዳ ወረዳ ፀጥታ አስተዳደር ሀላፊን ጨምሮ 15 ግለሰቦች እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

0
685

በቤንች ማጂ ዞን የጉራ ፈርዳ ወረዳ ፀጥታ አስተዳደር ሀላፊን ጨምሮ 15 የስራ ሀላፊዎችና ግለሰቦች ላይ እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት የሚደርስ ቅጣት ተወሰነባቸው።

ግለሰቦቹ ህገ መንግስትን በሚፃረር መልኩ አንደኛው በሌላ ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ የንጹሃንን ህይወት በማጥፋትና ንብረታቸውን በማውደም ወንጀል ነው የተከሰሱት።

ተከሳሾቹ 1ኛ ፃዲቅ የራ ዘይስ የጉራ ፈርዳ ወረዳ ሚሊሻ፣ 2ኛ አርሶ አደር ካብትኔ ሳራ፣ 3ኛ አርሶ አደር ጋጉ ጫዳ፣ 4ኛ ከበደ ለኩዩ የወረዳው ፀጥታ አስተዳደር ሀላፊ፣ 5ኛ ረዳት ኢንስፔክተር ምስክር ሀጅዋቀ የወረዳው የፖሊስ አዛዥ እንዲሁም 6ኛ ምርሳ ታየ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎችና ግለሰቦች ናቸው።

የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ ወንጀሉን የፈጸሙት በ2007 ዓ.ም ነው።

በዚህም በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በህጋዊ መንገድ የሰፈሩ ሰዎች መሬታችንን ለቀው ይውጡ በማለትና ራሳቸውም በድርጊቱ በመሳተፍና ጫካ በመግባት በሌሎች ብሄሮች ላይ በመነሳት በመንግስት ላይም ጦርነት መክፈታቸው ተጠቅሷል።

በተለይም ከመስከረም 25 ቀን እስከ ጥቅምት 2007 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈጠረውን ግጭት ለማረጋጋት ለተንቀሳቀሱ የፌደራል ፖሊስ አባላት፥ ተጠርጣሪዎቹ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ በማለትና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርገዋልም ተብሏል።

በዚህም 43 ንፁሃን ዜጎችና 12 የፌደራል ፖሊስ አባላት ህይወታቸውን እንዲያጡ ያደረጉ ሲሆን፥ በሰባቱ ላይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ከ16 ሺህ በላይ የቤት እንስሳትና ከ12 ሺህ በላይ ቤቶች እንዲወድሙና ሌሎች ጉዳቶች እንዲደርሱ ማድረጋቸውንም የክስ መዝገቡ ያመላክታል።

ተከሳሾቹ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲፈናቀሉ አድርገዋልም ነው ያለው አቃቢ ህግ በክሱ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ የወንጀል ችሎት፥ ያቀረበባቸውን ክስ በተገቢው መልኩ መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

በዛሬው እለት በዋለው ችሎትም 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በ22 አመት ጽኑ እስራት፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን በ19 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም 6ኛ ተከሳሸ ደግሞ በ18 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
ቀሪ ተከሳሾች ደግሞ እስከ 3 አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል።