በጉዲፈቻ ወደ ውጭ የተወሰዱ 7ሺ ህፃናት የደረሱበት አልታወቀም

0
1078

ከኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ወደ ውጭ አገራት በጉዲፈቻ የተወሰዱ ሰባት ሺ ህጻናት ስላሉበት ሁኔታ እና የሚገኙበት አገር መረጃ አለመኖሩን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 15ተኛው መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ያካሄደ ሲሆን፤ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የ2010 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት አዳምጧል፡፡
የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቲ ሃምቢሳ የሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ትኩረት እንደሚፈልግና በተለይም ወደ ወጭ በጉዲፈቻ የሚሰጡ ህጻናት በተገቢው ህጋዊ አሰራር እየተፈፀመ አለመሆኑን ለምክርቤቱ ገልፀዋል፡፡ የሴቶች ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት ብሎም ፖለቲካዊ የውሳኔ ሰጭነት በሚፈለገው ልክ አለማደጉንም አመልክተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ ከአስር ዓመታት በፊት ደላሎች ወላጆችን በማታለልና ከሌሎች አካላት ጋር በመመሳጠር በህገወጥ ህፃናትን ወደ ተለያዩ ሀገራት ልከዋል፡፡ በደላሎች ተታለው ልጆቻቸውን ልከው ያሉበትን ያላወቁ ወላጆች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልጆቻቸውን እንዲያገናኛቸው እየተማፀኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ህጻናቱ ለአሳዳጊዎቹ ሲሰጡ በቂ መረጃ እና አድራሻ ያልተያዘ በመሆኑ ፍለጋው አዳጋች እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ሚኒስቴሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እያፈላለገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ህጻናቱ ሊገኙ ይችላሉ ተብሎ በሚታሰብባቸው ስፔን፣ ጣሊያን እና አሜሪካ በሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት መካሄዱንና ጥረቱ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑንና ወላጆችም በሀገር ውስጥ ልጆቻቸው የሚያድጉበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል፡፡
በተያያዘም በህፃናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችም አሳሳቢ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡ በተለይም በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ‹‹ሚንጊ›› በሚል የሚፈጸመው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት፣ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ሌሎች አልተቀረፉም ብለዋል፡፡ ለመፍሄው ከሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጉዲፈቻ ህጋዊነት እንዲጠናከር፣የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲበረታታ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቀንሱ ፣ የሴቶች ማሕበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ብሎም ፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጭነት ሚናቸው እንዲጎላ በማድረግ ረገድ በትኩረት እንዲሰራ አሳስቧል፡፡