መንግስትንና “ሕዝብ”ን የሚስማሙ፡፡ ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎችን የሚያግባቡ የከሰሩ ሃሳቦች!

0
1051

• ኢኮኖሚን የሚያናጉ የመንግስት የብክነት እቅዶችና ተመሳሳይ የብክነት ተቃውሞዎች!
• ኑሮን የሚያሰናክሉ፣… የአድራጊ ፈጣሪ ባለስልጣን እርምጃዎችና፣ የትርምስ አመፆች!
• ዋናዎቹ ችግሮች፣… ብዙዎቻችን ከምንግባባቸው የተሳሳቱ ሃሳቦች የመነጩ ናቸው።
• “ከስኬት ይልቅ መስዋእትነት ይቅደም” በሚል ነባር ስብከት፣ ብዙዎች መስማማታቸው ነው ችግሩ።
• “መንግስት ገናና ይሁን” በሚለው ሃሳብ፣… ብዙዎች ይስማማሉ። ገናና ስልጣን ደግሞ ያጋድላል።
• ማንም ስልጣን ቢይዝ፣ በገናና መንግስት ስር፣ ገሚሶቹ ዜጎች ገባር ይሆናሉ – ገሚሶቹ ተመፅዋች።

“በራስ ጥረት፣… የግል ኑሮን፣… የማሻሻል አላማ፤… ቁጥር አንድ በጎ የኑሮ አላማ!” ቢሆን ነበር ተገቢ የሚሆነው። ኑሮን ከማሻሻል የላቀ አኗኗር ምን አለ? “ኑሮ እንዳይሻሻል የሚያደርግ፣ የኪሳራ፣ የመስዋእትነትና የብክነት እቅዶችን ያቀፈ የኑሮ አላማ” ነዋ ሌላው አማራጭ። ራሳችንን የማታለል ልማድ ጠንቶብን፣ ማመካኛና ሰበብ መደርደር ካልደረደርን በቀር፣… ጉዳዩ በጣም ግልፅ ነው።

ኑሮን ከማሻሻል የላቀ የኑሮ አላማ የለም።
ውይይት አስፈላጊ ነው ከተባለ፤ እዚህ ላይ ነበር መወያየት! የዚህ አገር ችግር መብዛቱ! ውይይት ማለት… እንደ እግርኳስ ፌደሬሽን የውዝግብ ማጥ ውስጥ መንቦራጨቅ ማለት እየሆነብን ነው። እለት በእለት በሰከሩ ሃሳቦችና በአሉቧልታ መነታረክ፣ በከሰሩ ስድቦችና ውንጀላዎች መፈነካከት፣… በረከሱ የጥላቻና የምቀኝነት ስሜቶች እርስበርስ ለማዋረድና ለመዋረድ መፎካከር የገነነበት ጩኸት ማለት ሆኖባቸዋል – ውይይት ማለት። እንዲህ አይነት ውይይት ቢቀር ይሻላል። የእግርኳስ ፌደሬሽን አይነት ውይይት፣… “ገና ለአቅመ ውይይት አልበቃንም” የሚያስብል ነው።
የሚበጀን ግን፣ ለአቅመ ሃሳብ፣ ለአቅመ ውይይት መድረስና፣ ዋና ዋና ቁምነገሮች ላይ በአስተዋይነት ብናስብ፣… በአስተዋይነትም ብንወያይ ነው። ኑሮን በሚመለከቱ ሦስት መሰረታዊ የስነምግባር (የኤቲክስ) ጉዳዮች ዙሪያ፣ አንድ ብለን መጀመር እንችላለን – “በጎ የኑሮ አላማ” በማለት።
“ውይይት”፣… እናም “አገራዊ መግባባት” ወይም “ብሔራዊ እርቅ” አስፈላጊ ነው ከተባለ፤… “በጎ የኑሮ ግብ፣ በጎ የኑሮ አላማ… ኑሮን የማሻሻል አላማ ነው” በሚለው ሃሳብ ላይ፣ በብዛት መግባባት አልነበረብንም? ግን እንዲህ አይነት “መግባባት” አልተፈጠረም። እንዲያውም የዚህ ተቃራኒ የሆነ፣ “የራስን ኑሮ መስዋእት ማድረግ” የሚል ስብከት ነው፣ በአገራችን ለረዥም ዘመን ገንኖና ሰፍኖ እስከዛሬ የዘለቀው። በዚህ የተሳሳተ ሃሳብና ስብከት አማካኝነትም፣ የብዙዎች ኑሮ፣ እንደማገዶ በመስዋዕት እሳት ውስጥ አመድ ሆኗል። ይሄ፣ ኑሮን ከሚያሻሽል አኗኗር በእጅጉ የራቀ ብቻ ሳይሆን፣ “የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት” ነው።
በተሳሳተ የኑሮ አላማ አማካኝነት ለሚፈጠር ችግር፣ ለዚያ ሁሉ ጉስቁልናና ህመም፣… ሁነኛው መድሃኒት፣… ነባሩ የተሳሳተ የኑሮ አላማን እንደገና ማግዘፍና መስዋዕትነትን መስበክ አይደለም። በትክክለኛ አላማ መተካት ነው – መፍትሄው። በሌላ አነጋገር፣ “ኑሮን የማሻሻል አላማ፤… በጎ፣ ተገቢ፣ ቁጥር አንድ የኑሮ አላማ” እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም።
ትክክለኛ የኑሮ አላማ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ የኑሮ መንገድም ያስፈልጋል።
ሌላው አማራጭኮ፣ “የዝርፊያ ሰለባ ወይም ለዝርፊያ መስዋእት የመሆን” እና “ዝርፊያ መፈፀም ወይም ለዝርፊያ መስዋእት የማድረግ” አማራጭ ነው። ሌላው ደግሞ መፅዋችና ተመፅዋች፣ ጥገኛና ደጓሚ የመሆን አማራጭ። እነዚህ አማራጮች፣ ለምልክት ያህል እንኳ ተመራጭ የሚሆኑበት እድል በአገራችን መኖሩ አይደለም አስገራሚው። ከነጭራሹ፣ በጉልህ የገነኑና ከሌላው ሁሉ በልጠው የሰፈኑት አማራጮች እነዚሁ ናቸው – እነዚሁ የመስዋእትነት አማራጮች – ማለትም የዝርፊያና የድጎማ ምፅዋት።
ይህንን የሚቀይር ትክክለኛ መንገድና አማራጭ የለም? አለ እንጂ።
በጎ የኑሮ አላማ፣… “ተገቢ የስኬት መንገድ” ያስፈልገዋል። ለሰው ተፈጥሮ የሚመጥንና ለኑሮ የሚበጅ፣… ዋነኛ የተግባር መርህ (የምግባረገብነት መርህ)… “ምርታማነት” እንደሆነ እስከዛሬ ብዙ ሰው የተግባባበትና በስፋት የሚታወቅ መሆን አልነበረበትም?
በእርግጥ፣ መልካም ጅምርንና ጥረትን ለማድነቅ መሸለም፣ እድገትን ለማፋጠን ማገዝ፣ በአስቸጋሪ ጊዜ መረዳዳትና መደጋገፍ፣… ይሄ ሁሉ ካልሆነም… አቅም ላጡ መለገስና መመፅወት ጭምር… ጥሩ ነው። ግን ከእነዚህ ተግባራት የሚልቅና የሚቀድም ቁጥር አንድ የኑሮ መንገድ፣… ለኑሮ የሚበጅ ቁጥር አንድ የምግባረገብነት መርህ አለ – ምርታማነት። ከመረዳዳትና ከምፅዋት በፊት፣…. በቅድሚያ ምርታማ መሆን፣ ሃብት መፍጠርና ንብረት ማፍራት ያስፈልጋል። ነገር ግን ይህም በቂ አይደለም።
አንደኛ፣… ኑሮን የማሻሻል በጎ አላማ፣… ሁለተኛ፣… ይህን የሚያሳካ ተገቢው የስኬት መንገድ (የምርታማነት መንገድ)… እነዚህ መታወቅና ጎልተው መታየት ነበረባቸው።
ሦስተኛ፣…
ከበጎ አላማና ከስኬት ግብረገብነት ጋር፣ … በምርት አይነት፣ መጠንና ዋጋ እያነፃፀሩ መገበያየት፣ የተባረከ ተገቢ ተግባር እንደሆነ መታወቅ አልነበረበትም?… ስርቆትና ዝርፊያን ከመሳሰሉ አጥፊ ድርጊቶች የፀዳ፣ ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነትም በእጅጉ የላቀ የሰውን ክብር የሚመጥን አስተማማኙ የሰዎች የኢኮኖሚ ግንኙነት፣… የምርት ግብይት (የነፃ ገበያ ስርዓት) እንደሆነ መታወቅ ነበረበት።

አሁን፣ “የመንግስት ሥራ ምን መሆን አለበት” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት እንችላለን።
ያው፣ “ሰዎች፣… በጎ የኑሮ አላማን መያዝ፣ በተገቢ የስኬት ምግባረገብነት ጎዳና (በምርታማነት መጓዝ)፣ ያፈሩትን ምርት መገበያየት እንዲችሉ፣ የእያንዳንዱን ነጻነት ማስከበር፣”… ዋነኛው የመንግስት ትክክለኛ ስራ እንደሆነ መታወቅ አልነበረበትም?
የመንግስት ትክክለኛ ስራ… ለእያንዳንዱ ሰው ስራ መስጠት አይደለም። የእያንዳንዱን ሰው የመስራት ነጻነት እንዲከበር መጠበቅ ነበር ትክክለኛው የመንግስት ስራ።
ከአንድ ሰው ላይ ምርትና ሃብት ነጥቆ ለመውሰድ የታክስ ሸክም መቆለል፣… ከጊዜ ወደ ጊዜም፣… ሃብት ፈጣሪና ስራ ፈጣሪ ምርታማ ሰዎችን እያዳከመ ማመናመን፤… ከአምራቾች የወሰደውን ሃብት፣… ግማሹን በከንቱ አባክኖ፣ ከፊሉን በሙስና አቀራምቶ፣ ቀሪውን ላላመረቱ ሰዎች በምፅዋት፣ በራሽንም ሆነ በሽሚያ ለማከፋፈል የድጎማ በጀት ማሳበጥ አይደለም – ተገቢው የመንግስት ስራ።
እያንዳንዱ ሰው፣ በገዛ ጥረቱ ያፈራውን ምርትና ንብረት ላይ የባለቤትነት መብቱ እንዲከበር መጠበቅ ነው – ትክክለኛው የመንግስት ስራ። በሌላ አነገራገር፣… በከንቱ ብክነት፣ በሙስና ቅርምትና በድጎማ ሽሚያ የማይተራመስ አገር፣… እንደማለት ነው።
ግን፣ ይሄ በእውን እየሆነ ነው? እየሆነ አይደለም። እንዲያውም፣… ገና ጅምር የማቆጥቆጥ ምልክት መፈንጠቅ ጀምሮ የነበረው የነፃ ገበያ ጭላንጭል፣… ባለፉት አስር ዓመታት… እየጠበበ፣ እየቀጨጨ፣ እየጨለመ መጥቷል።
አንደኛ፤
የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶች እንደአሸን እየፈሉና ለበርካታ ዓመታት እየተጓተቱ፣ በዚያው ልክ ከንቱ የሃብት ብክነት እየተባባሰ መጥቷል። ታዲያ፣… ለዚያውም በድሃ አገር፣… ከምርታማ ዜጎች የሚሰበሰበው ሃብት እንዲህ በከንቱ ሲባክን፣… ኑሮን የማሻሻል የሰዎች ጥረት መና አይቀርም? የኢንቨስትመንት አቅም እየተዳከመ፣ የስራ እድሎች እየቀነሱ… የኑሮ ቅሬታ ደግሞ እየከፋና ግራ የመጋባት ስሜት እየባሰ የመደናበር ትርምስ እየበዛ አይሄድም? ይሄም በተራው ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ቀውስ እየዳረገን… (ምርታማ ሰዎች የሚያፈሩት ሃብት፣… ኑሮን የሚያሻሽልና ለወደፊትም ይበልጥ ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር የሚችል ሃብት፣… በብድር የመጣ ሃብትም ጭምር፣ በመንግስት ተወስዶ፣ ኑሮን ለማናጋትና ኢኮኖሚን ለማቃወስ እንደማዋል ነው። ቤት ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ፣ የብድር እዳ ውስጥ እንደመግባት ነው – እጥፍ ድርብ ጥፋት!)።
ሁለተኛ፤
ባለፉት አስር ዓመታት፤… አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥሮችና የዘፈቀደ ክልከላዎች በየእለቱና በየአካባቢው እየተቀፈቀፉ፣… በፌደራልና በየክልሉ፣ በአዲስ አበባና በየወረዳው፣… ኢንቨስትመንትንና ምርታማነትን ማደናቀፍ ነው የበረከተው። ለዚያውም በብድር በሚመጣ ገንዘብ ነው፤ ፋብሪካንና ቢዝነስን የሚያሰናክሉ፣ ትርፋማነትንና የስራ እድልን የሚያመክኑ አዋጆችና ደንቦች፣… እልፍ አእላፍ የቁጥጥርና የክልከላ መመሪያዎች እንደጉድ የተፈለፈሉት። እግረ መንገዱንም ለሙስና ተቀራማቾችም ተጨማሪ በር እየከፈተ።
ሦስተኛ፤
ተደጓሚ ማብዛት፣ ለድጎማም የመንግስትን በጀት ማሳበጥ፣ ለዚህም ስራና ሃብት ፈጣሪ አምራቾች ላይ ታክስ ቆልሎ ማዳከም፣… ይህም አልበቃ ሲል፣… ከውጭ መበደር! በገጠር በየአመቱ ከመንግስት እርዳታና ድጎማ የሚመደብላቸው የገበሬ ቤተሰቦች ቁጥር ከ8 ሚሊዮን በላይ ነው። ግማሹ በጀት በእርዳታ ከውጭ እየመጣ በየዓመቱ የሚቆለል እዳ ሆኗል።
ምን ይሄ ብቻ! አሁን ደግሞ፣ በከተማም እንዲሁ የድጎማና የእዳ ጉዞ ተጀምሯል። ኢንቨስትመንትና ቢዝነስ እየተስፋፋ የስራ እድል የሚበራከትበት፣ በዚህም ሚሊዮኖች የስራ እድል አግኝተው በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበት፣ ራሳቸውን ችለው ክቡር ሕይወትን የሚያጣጥሙበት የነፃ ገበያ ስርዓት እየቀጨጨ በሄደ ቁጥር፤ በተቃራኒው ስራ አጥነት እየተባባሰ የመንግስት ጥገኛ የሚሆኑ ሰዎች እየበዙ ሲሄዱ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ አይደለም? ነው እንጂ።
በእርግጥ፣ አምራች ሰዎች ላይ የታክስ ጫና እየቆለሉ፣ የውጭ እርዳታና ብድር እየተጨመረበት፣… የድጎማ በጀት በየዓመቱ እያበጠ ለተወሰነ ጊዜ፣ የሚያስኬድ ሊመስል ይችላል። ግን እስከመቼ፣…
አምራቾች እስኪራቆተው ታክስ መክፈልም ሆነ የስራ እድል መፍጠር እስኪያቅታቸው ድረስ፣ አገሬው በስራ አጥ ተደጓሚ እስኪጥለቀለቅ ድረስ፣ የውጭ ብድር ተከምሮ ተራራ የሚያክል እዳ አገሪቱን እስኪደፈጥጣት ድረስ?

ዮሃንስ ሰ