1 ነጥብ 3 ኪሎ ግራም ኮኬን ይዞ በአዲስ አበባ በኩል ለማለፍ ሲሞክር የተያዘው ናይጄሪያዊ በእስራት ተቀጣ

0
1484

መነሻው ከብራዚል ሳኦፖሎ በማድረግ 1 ነጥብ 3 ኪሎ ግራም እንዳይመረቱ እና እንዳይዘዋወሩ የተከለከሉ መርዛማ የኮክዮን እፆችን ይዞ ለማለፍ ሲሞክር የተያዘው ናይጀርያዊው ግለሰብ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ።

ናይጀርያዊ ዜግነት ያለው ግለሰቡ ሚስተር አማቺ ስቲቭ በመባል ይታወቃል።

ግለሰቡ ህዳር 26 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት በግምት ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ሲሆን ነው ትራንዚት ለማድረግ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ የተገኘው።

ግለሰቡ እንዲህ አስቀድሞ ከብራዚሏ ሳኦፖሎ ከተማ በመነሳት ወደ ናይጄርያ ሌጎስ ለመጓዝ ነው አቅዶ የተነሳው።

ነገር ግን 1 ነጥብ 3 ኪሎ ግራም እንዳይመረቱ እና እንዳይዘዋወሩ የተከለከሉ መርዛማ የኮኬን እፆችን ይዞ ለማለፍ ሲሞክር በተደረገበት ድንገተኛ ፍተሻ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውሏል።

በዚህም መሰረት ከሳሽ አቃቢ ህግ እንዳይመረቱ እና እንዳይዘዋወሩ የተከለከሉ መርዛማ እፆችን በማዘዋወር ወንጀል በግለሰቡ ላይ ክስ መስርቶበታል።

ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ እንደደረሰው እና ተነቦለት እንዲረዳው ከተደረገ በኋላ የእምነት ክህደት ቃሉን ተጠይቋል። ተከሳሹም የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን አምኗል።

በዚህም መሰረት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛው የወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔን አሳልፏል።

ግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርቡ በታዘዘው መሰረት ተከሳሹ ሶስት የቅጣት አስተያየቶችን ሲያቀርብ አቃቢ ህግ ግን አላቀረበም።

በዚህም መሰረት የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛው የወንጀል ችሎት ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስጠነቅቃል በማለት ተከሳሹን በሰባት ዓመት ፅኑ እስራት እና በ15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።