የሰሀራ በረሐን በክራንች ያቋረጡት ስደተኞች

0
1131

ወቅቱ ከ13 አመታት በፊት ነው።በ1970ዎቹ ለነጻነት በተካሄደዉ ትግል የዘመቱና በጦርነቱ ጊዜ አንዳንድ እግራቸዉን ያጡት አበደ ተስፋይና የማነ ጊላጋብርን ለደህንነታቸዉ በመስጋት በሕገ ወጥ መንገድ የአገራቸዉን ድንበር በክራንች አቋርጠዋል።

በከባድ ፈተናም ሱዳን መግባት ችለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰዎች ለተሻለ የትምህርት እድል፣ ስራ እና ህይወት ይሰደዳሉ ቢልም እንኳ አብዛኛዎቹ በድህነት፣ ጦርነት፣ ግጭትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ አለመረጋጋትና የመልካም ኣስተዳደር እጦት፣ የማህበራዊ ኣገልግሎት እጦትና ሌሎች ምክንያቶች እንደሚሰደዱ አስቀምጧል።

ለነዚህ የቀድሞ ታጋዮች የተሰደዱበት ምክንያትም በሀገራቸው ነፃነት ማጣትና በፖለቲካው አለመረጋጋት ነው።

በአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 2000 በተካሄደዉና የ20 ሺ ወጣቶችን ህይወት ያስከፈለዉ የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ጦርነት በአልጀርስ የሰላም ስምምነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ጦርነቱንም ተከትሎ ሚኒስትሮች እና ጀነራሎች የሚገኙበት ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች ህገ-መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ ማሻሻያዎችንም በአገሪቷ ውስጥ ለማካሄድ ውይይቶች ተጀመሩ።

“ጉዟችንን ገምግመን አካሄዳችን እናስተካክል በሚል በ1997 በብሄራዊ ምክር ቤት ያጸደቅነዉ አቋም ተግባራዊ እናድርግ” የሚሉ ጥያቄዎችም መነሳት ጀመሩ።

በወቅቱም አበደ እና የማነም ማሻሻያ መደረግ አለበት እንዲሁም ህገ-መንግሥቱ ይከበር የሚሉት ሃሳብ ደጋፊዎች ነበሩ።

ምላሹ ግን የከፋ ነበር “እነዚህ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በሃይል ተጨፈለቁ። በብዙ ተቋማትና ኃላፊነት ያሉ የመንግስት ካድሬዎችን ማደንና ማሰር ከተጀመረ በኋላ፤ ለህይወታችን በመስጋት ነዉ ያመለጥነው” በማለት ከአገራቸው የወጡበትን ምክንያት ይናገራሉ።

በአውሮፓውያኑ መስከረም 2001 ዓ.ም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን በማሰር የተጀመረዉ ጉዳይ የዚህ ሃሳብና አመለካከት አራማጅ ናቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ ሁሉ እስር ቤት ገቡ።

ለነፍሱ የሰጋው ሁሉ ከዚህ ውርጅብኝ ለማምለጥ ስደትን ምርጫቸው አደረጉ ፤ በዚህም ወቅት ነው አበደ ቤተሰቡን ትቶ አቅሙ የፈቀደለትን ዝግጅት አድርጎ ለሚያውቁትም ሰዎች ሳይናገር ተደብቆ የወጣው።

በእግሩ ፈታኝ የሚባለውን የኤርትራ በረሃዎችን በማቋረጥ ከስንት ድካም እና እንግልት በኋላ ከባድ የወባ በሽታን ሸምቶ ካርቱም ገባ።

አበደ ተስፋይImage copyrightABEDE

የማነም አንጀቱን አሰር አድርጎ የ3 ወር ህጻን ልጁን ጨምሮ ሶስት ልጆቹ እና ባለቤቱን ይዞ ስደትን ጀመረ።

በአንድ እግሩም እያነከሰ፣ እየወደቀና እየተነሳ በክራንቹ ታግዞ ወደ ሱዳን ገባ።

በመጀመሪያ ሃሳባቸው የነበረው ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ሱዳን ላይ ሊቆዩ ነበር ፤ ነገር ግን ሱዳንም ላይ ከፍተኛ እክል ስለገጠማቸው ከባዱ የሰሃራ በረሃንና ባህርን አቋርጠው ለመጓዝ ወሰኑ።

ሁለቱም የበረሃ ጉዟቸውን በምሬት ያስታውሳሉ።አበደ ሰዎች በሰዎች ላይ ተደራርበው ከተጫኑ ወጣቶች ጋር ነዉ የተጓዘዉ።

አምስት ቤተሰቡን ይዞ የወጣዉ የማነ ደግሞ ከ10 ኤርትራዉያን ጋር እቃ መጫው ላይ ተጭኖ ነው በረሃውን ያቋረጠው።

ሁለቱም ፈታኝና አሰቃቂ የሚባለውን ጉዞ ገጥሟቸዋል። በውሃ ጥም መንገድ ላይ የሞቱትን አስከሬን እያዩ ተጉዘዋል።

ከ20 ዓመታት በላይ የታገሉለትም አላማ ነፃነትን ሳይሆን ለስደትና እንግልት ምንጭ መሆኑ አሳዝኗቸዋል።

አጋጣሚዎቻቸው አሰቃቂ ከመሆናቸውም አንፃር ለመናገር ከባድ ናቸው። አበደ በጉዞው ላይ ብዙ ምስላቸዉ የማይለይ በዉሃ ጥም የሞቱ አስከሬኖች መሃከል የአንድ ዘመዱን መታወቂያ አግኝቷል።

ይህ ክፉ አጋጣሚም ልቡን ሰብሮታል። የማነም በጉዞዉ በአንዲት የተበላሸች መኪና ዉስጥ በርካታ የሞቱ ሰዎች እንዳየ ይናገራል።

አበደ የሰሃራ በረሃን ለማጠናቀቅ ሁለት ሳምንታት ሲፈጅበት ለየማነ አንድ ወር ወስዶበታል።

መዘግየቱም ያጋጠመው መኪኖቹ መንገድ ላይ ስለተሰበሩ ሲሆን ከሁለቱ መኪኖች ለቅያሪ የሚሆን እቃ አዉጥተዉ ለአንደኛዋ ለመግጠም ሱዳን ስለተመለሱ ነዉ።

መጨረሻ ላይ ሊቢያ ለመግባት አንድ ቀን ሲቀራቸዉ ሁለቱም መኪኖች ተሰብረዉ መንቀሳቀስ አልቻሉም።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ያኔ የመኪኖቹ መንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ምግብና ነዳጅም አልቆ ነበር።

አብረዋቸዉ የነበሩ አዘዋዋሪዎች መልካም ስለነበሩ መኪኖችን ለማስተካከል የተቻላቸዉን ሞክረዉ የሚረዳቸዉን ሰዉ ለማምጣት ወደ ሊቢያ አቀኑ።

የስደት ጉዞImage copyrightYMANE

መንገድ ላይ ሌሎች ስደተኞች አድርሰዉ የሚመለሱ መኪኖች አግኝተዉ ሲመለሱ ገንዘብ ከፍለዉ መሄድ የሚችሉ ካሉ ብለዉ በጠየቁበት ወቅት የማነ ቤተሰቡን ይዞ ከጥቂት ስደተኞች ጋር ሊቢያ ገቡ።

ሌሎቹ ግን ተስፋ ቆርጠዉ በእግር እንደሞኮሩና መንገድ ላይ እንደቀሩ የተረፉ አንድ ሁለት ሰዎች አጫውተውታል።

ከዛ ሁሉ የበረሐ ጉዞ የከፋ የሚለውም አጋጣሚም የደረሰበት አንድ ቀን ጉዞው መሐል በፍተሻ ምክንያት ከመኪና አስወርደዋቸው በክራንቹ በመታገዝ 20 ኪሎ ሜትር ያክል የተጓዘውን ነው።

የባህር ወጀቡ እስኪረጋጋ ሊቢያ ለአራት ወራት ያህል ከቆየ በኋላ የማይቀረውን ሁለተኛዉን ፈታኝ ጉዞ ለመጀመር ተነሳሱ።

በመጀመሪያዎቹ ባህርን የማቋረጥ ጉዟቸው አልቀናቸውም። ሁለት ሶስት ጊዜም ከባህር ተመልሰዋል።

ከ72 ሰዓታት ጉዞ በኋላ እና ጭንቀት በሰላም ጣልያን ገቡ። ጉዟቸውንም ቀጥለው አበደ ወደ ሆላንድ የማነ ደግሞ ስዊዘርላንድ ገቡ።

ዛሬ ታህሳስ 9 በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ዘንድ “የስደተኞች ቀን” በሚከበርበት በተለያየ ምክንያት ለተሰደዱ ህዝቦች በተለይም ከባዱ የሰሃራ በረሃንና ባህርን ተሻግረዉ የሚያርፉበት አገር የደረሱ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን በስደት ያገኙትን አጋጣሚ በኣግባቡ እንዲጠቀሙ መማር የሚችሉ እንዲማሩና ሰርተዉ ሊቀየሩ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ይሄንን ቀን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ አገራትና መንግስታት እና ተቋማት ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን ፤ በሊቢያ በረሃ በጨረታ የተሸጡትን ስደተኞች ትኩረት እንዲሰጡና መፍትሄ እንዲተገብሩ ጥሪያቸዉን አቅርበዋል።

በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 4 2000 ዓ.ም በስደተኞች ጉዳይ የመከረዉና ታህሳስ 9 ዓለምአቀፋዊ ቀን ሆና እንድትከበር የወሰነዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1990 የሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸዉን መብት የሚከላከል ስምምነት ኣጽድቋል።

እየጨመረ የመጣዉን ዓለምአቀፋዊ ስደት በጠንካራ ፖሊሲ እንዲደገፍ፣ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች እንዲረጋገጡ እና ለስደተኞች የመንቀሳቀስ ነጻነት እንዲፈቀድ እና አህጉራዊና ከባቢያዊ መደጋገፍ እንዲሰፍንም 132 የድርጅቱ አባል ሃገራት የተቀበሉት ስምምት ነዉ።

ይሄንንም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ባለታሪኮቻችን አፅንኦት ይሰጣሉ።

ምንጭ:- ቢቢሲ