ዩክሬናዊው ጠንካራ ሰው ግዙፍ ፈረስ ተሸክሞ በመጓዝ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል

0
337

ዩክሬናዊው ጠንካራ ሰው አሁን ደግሞ በህይወት ያለን ፈረስ ተሸክሞ በመጓዝ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

ሰዎች ፈረሶችን ለበርካታ ዓመታት ለመጓጓዣነት ሲጠቀሙ እና ሲጋልቡ ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰዋል፤ ዩክሬናዊው ግዙፍና ጠንካራ ሰው ግን ፈረሶች በተራቸው ሰዎችን ሊጋልቡን ይገባል በሚል ግዙፍ ፈረስ ተሸክሞ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሷል።

የክብደት ማንሳት ሻምፒዮኑ ድሚትሮ ካላድዚ በህይወት ያለ እና ንቁ ፈረስ በትከሻው ተሸክሞ በመጓዝ ነው አዲስ የጥንካሬ ታሪክ ለራሱ ያስመዘገበው።

እንደ በርካታ ጠንካራ ሰዎች ሁሉ ድሚትሮ ካላድዚ በርካታ አስገራሚ ተግባራትን ሰርቷል።

ለምሳሌ ተኝቶ ተሽከርካሪ በሰውነቱ ላይ እንዲሄድ ማድረግ፣ የግንባታ ብረቶችን በጥርሱ መጠምዘዝ፣ ሚስሮችን በእጁ በመምታት በእንጨቶች ላይ ማስገባት እና መኪና በእግሮቹና በእጆቹ ማንሳትን የመሳሰሉ አስገራሚ ስራዎችን ሰርቷል።

አሁን ላይ ደግሞ ፈረስ ተሸክሞ መንቀሳቀሱ በብዙዎች የተደነቀለት የጥንካሬው ውጤት ሆኗል።

ፈረሶች እንዳያስቸግሩና ጉዳት እንዳያደርሱበት እግራቸው በገመድ ታስሮ ነው የሚሸከማቸው።

ሆኖም ንቁ በመሆናቸው ሰውነታቸውን እያንቀሳቀሱ ካላድዚ ሚዛኑን እንዲስት የማድረግ አቅም ቢኖራቸውም፥ ጠንካራው ሰው ግን ይህ ሳይበግረው ተሸክሟቸው ይንቀሳቀሳል።

ካላድዚ 63 የዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ክብረወሰኖችን የያዘ ሲሆን፥ የዩክሬን ከአበረታች እፅ ነፃ በሆነ ከፍተኛ ክብደት የማንሳት ውድድር የመጀመሪያው ሻምፒዮን ነው።

የ38 ዓመቱ ጠንካራ ሰው ጦርነት በማይለያት የዩክሬን አካባቢ መኖርን የመረጠው፥ የየእለት እንቅስቃሴውን ለመስራት አመቺ ሆኖ ስላገኘው መሆኑን ተናግሯል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ የተገንጣዮች ቡድን አባል ሆኖ በአስደናቂ የጥንካሬ ስራዎቹ እያዝናናቸው መሆኑም ተሰምቷል።

ምንጭ፦ኤፍ ቢ ሲ