Ethiopia: Athlete Haile gebre selassie & Mr. Tesfaye Fichala | ሀይሌ ገ/ስላሴ እና ተስፋዬ ፊቻላ

0
372
ሀይሌ ገ/ስላሴ እና ተስፋዬ ፊቻላ
(ዳዊት ታዬ)
አቶ ተስፋዬ ፊቻላ ይባላሉ፤ በሽግግሩ ዘመን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ፥ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ። እዚህ ቻይና ቤጂንግ ላይ ነው ያገኘኀቸው ፥ለመግባባት የማይከብዱ ቀለል ያሉና ተጨዋች ሰው ናቸው። በጨዋታ መሐል ተነሳና ስለ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ይህን አወጉኝ ።
.
በ1980 ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ለሚባል የአትሌቲክስ ውድድር ከተለያዩ አገሮች አትሌቶች ይጋበዛሉ ፤ በአጋጣሚ የውድድሩ ጊዜ ሀይሌ ገ/ስላሴ (ያኔ ገና ታዋቂ አልሆነም) ጀርመን ስቱትጋርት ላይ ከሚያደርገው ውድድር ጋር ይገጣጠማል ፤ በመሆኑም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስፖርት ዘርፍ ሀላፊዎች ከውጪ አትሌቶች እየጋበዝን የኛዎቹ ወደ ውጪ እንዲወጡ መፍቀድ ተገቢ አይሆንም በሚል ሔዶ እንዳይወዳደር ይከለክላሉ ።
.
ይሔኔ ነው እንግዲህ፥ ከመንደሩ ሠዎች ውጪ ማንም የማያውቀው የያኔው ሀይሌ
ገ/ስላሴ ምክትል ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ፊቻላ ቢሮ ቀርቦ አቤቱታ ያቀረበው።
አቶ ተስፋዬ አቤቱታውን አዳመጡትና አሰልጣኝህን ይዘህ ና ብለው ሸኙት ፤ እንደተባለው አሰልጣኙን ይዞ መጣ ፤
.
አቶ ተስፋዬ ጠየቁ “ይሔን ልጅ ብንልከው ውጤት ያመጣል ?” አሰልጣኙ ዶ/ር
ወ/መስቀል ኮስትሬ በልበ ሙሉነት መለሱ “ልጁ አይደለም ኢትዮጲያን አፍሪካን ሊያሰጠራ ይችላል ብዬ ተስፋ የጣልኩበት ነው ፤ እድሉ ቢሰጠው ውጤት ያመጣል።” አቶ ተስፋዬ ወዲያው ያቀረበው ወረቀት ላይ አጠፍ አድርገው ለሳቸው ተጠሪ ለሆኑት የስፖርት ዘርፍ ዳይሬክተር እንኳን ሳያሳውቁ ፦ ለውድድሩ እንዲሄድ የተፈቀደ በመሆኑ አስፈላጊው ሁሉ ይደረግ ብለው እሳቸው ክሬዜ የሚሉትን ውሳኔ አሳለፋ ።
.
ሀይሌ ስቱትጋርት ሔደ ፤ ተወዳደረ ፤ አሸነፈ ፤ ማሸነፍ ብቻ አይደለም ፥ ለራሱ የመጀመሪያ የሆነውን የአለም ሪከርድ አስመዘገበ ፤ እና ተሸለመ ፤ ሽልማቱ ማርቸዲስ መኪና እና adidas adventure ሰአት ነበር ።
.
ከጊዜ በኋላ ሀይሌ ጋሽ ተስፋዬ ጋር መጣ፤ የሽልማት ሰአቱን አመስግኖ እጃቸው ላይ አሠረ ፤ ሰአቷ 20 አመት ሙሉ ከጋሽ ተስፋዬ እጅ አልወለቀችም ፤ በፎቶው ላይ እንደምታዩት አሁንም አዲስ ነች፤ አሁን ግን ሰአት ብቻ ሳትሆን ታሪክም ጭምር ነች ። ሰአቷ የኢትዮጵያ አትሌቲክስና የአንበሳው ኢትዮጲያዊ አትሌት ታሪክ አንድ ፈርጥ ነች።
.
ይሔ ብቻ አይደለም አትሌቶች ተወዳድረው ከሚያገኙት ላይ 75% ለራሳቸው እንዲወስዱ የሚፈቅደው መመሪያ የፀደቀውና ተግባራዊ የተደረገው ተስፋዬ ፊቻላ በሚለው ፊርማና ማህተም መሆኑን ነግረውኛል።
.
ይሔን ያሕል ፍንጭ ከሰጠሁ ቀሪውን ዝርዝር ጉዳይ ለጋዜጠኞች እተዋለሁ፤ ጋሽ ተስፋዬ ፊቻላ አሁንም በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት በማገልገል ላይ ናቸው ።
.
ቻይና ቤጂንግ
— at Beijing.