እርድ

0
1499

ቅመማ ቅመምን አዘውትሮ በመጠቀም በቀዳሚው ደረጃ ላይ የሚቀመጡት በምስራቅ አለማችን ክፍል ያሉ በተለይ የእስያ ሀገራት ናቸው።  መጠኑና አይነቱ ይለያይ እንጂ በሀገራችንም በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜያት እና በገጠር አካባቢ ለቅመማ ቅመም የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው።  ብዙዎቻችን ቅመማ ቅመሞችን የምንጠቀመው ለምግቦቻችን የተለየ ቃና እና ጣዕም ለመስጠት ነው።  የስነ ምግብ ባለሞያዎች ግን አንዳንድ ቅመማ ቅመሞች ከማጣፈጫነታቸው ይልቅ መድሃኒትነታቸው ያይላል ይላሉ።  ከእነዚህ ቅመማ ቅመሞች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው እርድ ነው።  እርድ ከስራስር ተክሎች አንዱ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ነጭ ነገሮችን ወደ ቢጫነት ለመቀየር የምንጠቀምበት ቅመም ነው።  ይህ ቅመም በተለይ በሀገራችን ከሚዘወተር ቅመሞች ብዙ ጥቅም ላይ የማይውል እና ዋጋውም አነስተኛ ነው።  ለመሆኑ ይሄ ቅመም ምን አይነት ጠቀሜታዎች ይኖሩት ይሆን?

እርድ በተፈጥሮው ከርኩሚን የተባለ እና ቢጫ ቀለም እንዲኖረው የሚያደርገው ንጥረ ነገር አለው።  ይህ ንጥረ ነገርም የሰውነት መቆጣትን (inflammation) የመከላከል ከፍተኛ አቅም አለው።  በዚህም በሰውነት መቆጣት ሳቢያ የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል እርድን አዘውትሮ መመገብ ይመከራል።  ከሁሉም በላይ ግን እርድን መጠቀም ለካንሰር ህመም የሚኖረውን ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ጥናቶች ያመለክታሉ።  ከርኩሚን የተባለው ከእርድ የሚገኘው ንጥረ ነገር የካንሰር ሴሎች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ እንዳይበዙ የማድረግ አገልግሎት አለው ይላል ከእንግሊዝ ካንሰር ማዕከል የተገኘ መረጃ።  በመሆኑም ይህ ንጥረ ነገር ለጡት ካንሰር፣ ለሳምባ ካንሰር፣ ለሆድ ዕቃ ካንሰር፣ ለጉበት ካንሰር እና ለትልቁ አንጀት ካንሰር የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል።  ማዕከሉ በጥናት አረጋግጫለሁ እንዳለውም ይህ በእርድ ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ለካንሰር መንስኤ የሚሆኑ የሰውነት መቆጣት እንዳይፈጠር ማድረግ፣ የካንሰር ሴሎች በቂ የደም አቅርቦት አጥተው እንዲሞት የማድረግ እንዲሁም የካንሰር ሴሎች ወደተለየዩ የሰውነት ክፍሎች እንዳይሰራጩ የሚያደርግ መድሃኒትነት ባህሪ አለው።

በቴክሳስ ዩኒቨርስቲ ዶ/ር አንደርሰን ካንሰር ማዕከል የተደረገ ጥናት እንዳመለከተውም ከርኩሚን የተባለው ንጥረ ከደም ይልቅ በትልቁ አንጀት ገበር የመምጠጥ ባህሪይ ነው ያለው።  ይሄ ተፈጥሮው ደግሞ ንጥረ ነገሩ አንጀት ለካንሰር ሴሎች እንዳይጋለጥ በማድረግ ከፍተኛ ከለላ ይሆነዋል።  ይሄ ንጥረ ነገር የካንሰር ሴሎችን የሰውነት ክፍል እንዳይሰራጩ በማድረግም የቆዳ ካንሰርን ይከላከላል ያለው ጥናቱ፤ በተጨማሪም ንጥረ ነገሩ የማህፀን በር ካንሰርን በመከላከል ተስፋ ተጥሎበታል። ንጥረ ነገሩ የሰውነት መቆጣትን የመከላከል ባህሪይ ስላለው፤ ሄውማን ፓፕሎማ ቫይረስ የተባለውን ቫይረስ እንዲፈጠር የሚያነሳሱ ነገሮችን በመዝጋት እና የካንሰር ሴሎች እንዲሞቱ በማድረግ የማህፀን በር ካንሰርን የመከላከል አቅም እንዳው የማእከሉ ጥናት ውጤቶች አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ከርኩሚን ካለው የኬሚካል ይዘት የተነሳ በሰውነት ውስጥ የሚገኙት ፍሪራዲካልስ የተመጣጠነ እንዲሆኑ የሚያግዝ ጥሩ ኦክሲደንት ነው።  ኦክሲደንቶች ከተፈጥሯቸው ሰውነትን ፍሪራዲካልስ የሚከላከሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው።  ኦክሲደንቶች ባይቆጣጠሯቸው ፍሪራዲካልስ የተባሉት ንጥረ ነገሮች በሰውነት ውስጥ የሚገኙ እንደ ፋቲ አሲዶች እና ፕሮቲኖች እንዲሁም ዘረመሎችን የሚያጠቁ ነገሮች ናቸው።  በመሆኑም ከርኩሚን እነዚህ ፍሪራዲካልስ በሰውነት ውስጥ የሚኖራቸው ይዘት የተመጣጠነ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው።  በተጨማሪም ይህ ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ በተፈጥሮ ያሉ ኦክሲክቶች እንዲነቃቁ የማድረግ ጠቀሜታም አለው።

የእርድ ጠቀሜታ በዚህ የሚያበቃ አይደለም።  በውስጡ ያለው ከርኩሚን ንጥረ ነገር በአእምሮ ላይም ከፍተኛ ስራን ይሰራል።  በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ኒውሮኖች በየጊዜው የመቀጣጠል እንዲሁም በመራባት በቁጥር የመጨመር ባህሪይ አላቸው።  ይህ አይነቱ ባህሪይ እንዲኖራቸው የሚያደርጋቸው ደግሞ በክሬን ዴሪቭድ ኒውሮትሮፊክ ፋክተር የተባለ በአንጎል ውስጥ ያለ ሆርሞን ነው።  ይህ አይነቱ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል ታዲያ በሰው አንጎል ላይ የተለያዩ መቃወሶች ይከሰታሉ።  የኒውሮኖች ቁጥር እየቀነሰ የሚመጣበት ጊዜም እንደ ድብርት እና አልዛይመርስ፤ (የመጃጃት በሽታዎች) ይከሰታል።  እንዲህ አይነቱን ችግር ለመቅረፍ ከሚያገለግሉ ነገሮች መካከል ታዲያ አንዱ እርድ ነው።  በዚህ እርድ ውስጥ የሚገኘው ከርኩሚን ኒውሮኖች እንዲበዙ የሚያግዘውን ሆርሞን መጠን እንዲጨምር በማድረግ አንጎል ለእነዚህ ችግሮች የሚጋለጥበትን ጊዜ የማዘግየት ግፋ ሲልም የማስቀረት ጠቀሜታ አለው ተብሏል።  ከዚህ ጎን ለጎንም የዚህን ሆርሞን መጠን በመጨመር የአንጎልን የማስታወስ ችሎታ የማዳበር እና ቀልጣፋ የማድረግ አገልግሎት እንዳለው ነው የቴክሳስ ዩኒቨርስቲ ጥናት ያመለከተው።

ለልብ ህመም የመጋለጥ እድልንም እርድን በመጠቀም መቀነስ እንደሚቻል በጥናት ተረጋግጧል።  የልብ ህመም በአብዛኛው መንስኤው የደም ስሮችን የሚሸፍነው ኢንዶቴሪየም የተባለው ገበር ተግባሩን በአግባቡ ባለማከናወኑ የሚመጣ ነው።  በመሆኑም ይህ ነገር ስራውን በአግባቡ መስራት ሲያቅተው የደም ግፊትን፣ የደም መርጋትን እና ሌሎች ከደም ጋር የተያያዙ ሂደቶችን መቆጣጠር ያቅተዋል።  በዚህ ጊዜም ልብ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣል።  ይህ እንዳይሆን ታዲያ ይሄ በእርድ ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ጠቃሚ ነው።  ይህ ንጥረ ነገር የደም ስር ገበሩ ተግባራቱን በአግባቡ እንዲያከናውን ያደርገዋል።  የሚሰጠው አገልግሎትም ልክ የሰውነት እንቅስቃሴ እና ለዚሁ አላማ ተብለው የሚሰጡ መድሃኒቶች ከሚሰጡት ጠቀሜታ እኩል እንደሆነ ነው አጥኚዎች እየገለፁ የሚገኙት።  ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ንጥረ ነገሩ የሰውነት መቆጣትን የመቀነስ እንዲሁም የኦክሲደንትነት ባህሪይ ስላለው የልብ ህመምን የመከላከል አቅሙ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል።

አልዛይመርስ (የመጃጀት) ችግር የሚፈጠረው ጥልፍልፍ የሆነ እና ኤሚሎይድ የተባሉ የፕሮቲን ግድርግዳዎች በአንጎል ውስጥ ሲፈጠሩ ነው።  በእርድ ውስጥ የሚገኘው ከርኩሚን ታዲያ እነዚህን ጥልፍልፍ የፕሮቲን ግድግዳዎች የማፅዳት አቅም አለው።  በመሆኑም በተለይ በአዛውንትነት እድሜ ላይ ላሉ ሰዎች እርድን አዘውትሮ መመገብ ይህን ችግር ለመቅረፍ ያግዛል ተብሏል።

ከርኩሚን የብሬን ዴሪቭድ ኒውሮትሮፊክ ፋክተር ሆርሞንን መጠን የመጨመር ጠቀሜታ ስላለው የድብርት ችግርን የመከላከል ጠቀሜታም አለው።  ድብርት የሚከተለው የዚህ ሆርሞን መጠን መቀነስ በሚከሰትበት ወቅት እንዲሁም ሂፓካምኖስ የተባለው እና ለመገንዘብ እና ለማስታወስ የሚያግዘው የአእምሮ ክፍል በሚሸማቀቅበት ወቅት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በእርድ ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር በህፃናት ላይ የሚከሰተውን የነጭ ደም ሴል መብዛት (leukemia) እንደሚከላከል በጥናት ተጋግጧል።  በችካጎ ሎዮላ ዩኒቨርስቲ የህክምና ማዕከል የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው እርድ የተካተተበት ምግብን አዘውትረው የሚመገቡ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት ለዚህ ለነጭ ደም ሴልች የመጋለጥ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው።  በአብዛኛው ለዚህ አይነቱ ችግር የሚያጋልጡት በቅድመ ወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት ለተለያዩ ጨረሮች፣ ቤንዚን፣ አካባቢን የሚበክሉ ነገሮች እንዲሁም ለአልካላይና መጋለጥ መሆኑን የጠቀሰው በማዕከሉ የተደረገው ጥናት፣ በእርድ ውስጥ የሚገኘው ከርኩሚን እነዚህን ነገሮች ጉዳት እንዳያደርስ በመከላከል ለችግሩ ያለውን ተጋላጭነት ይቀንሰዋል ብሏል።  ከዚህ በተጨማሪም ለጤናማ ጉበት፣ የምግብ ልመትን ለማፍጠን እርድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።  እርድን በምንመገብበት ወቅት በሰውነታችን ውስጥ ያለው መጥፎ ኮሌስትሮል መጠን እንዲቀንስ እንዲሁም ጥሩ ኮሌስትሮል ደግሞ መጠኑ እንዲጨምር በማድረግ የሰውነታችን ኮሌስትሮል የተመጣጠነ እንዲሆን ያደርጋል ሲል ጥናቱ ጠቀሜታዎቹን ዘርዝሯል።

የእርድ የማዕድን ይዘትን ስንመለከት በሁለት የሻይ ማንኪያ እርድ ውስጥ እንኳን 17 በመቶ ማግኒዚየም፣ 10 በመቶ ብረት፣ 5 በመቶ ቫታሚን ቢ6፣ አራት በመቶ አስር (ፋይበር)፣ ሶስት በመቶ መዳብ (copper) እና ሶስት በመቶ ፖታሲየም ይገኛሉ። በመሆኑም ይህን ጠቀሜታው ብዙ ዋጋው ግን ዝቅተኛ የሆነ ቅመምን በተለያዩ መንገድ በመጠቀም ራስ በራስ ማከምን ባለሞያዎች አበክረው ያሳስባሉ።

 ምንጭ:- ሰንደቅ ጋዜጣ