Ethiopia: የፌስቡኩ ጋኔን

0
1431

የፌስቡኩ ጋኔን ! ከአበረ አዳሙ

Posted by Bawza Ethiopian Newspaper on Monday, November 6, 2017

የፌስቡኩ ጋኔን

አበረ አዳሙ
ጥቅምት 25/2010 ዓ/ም
ባህር ዳር
በአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች የጋራ መድረክ ላይ የቀረበ
===========
ከረቂቅ ህዋ ውስጥ ገና ስንፈጠር፣
ብዙ አካል ኖሮን ነው፤ ብዙ ማግና ድር፡፡
ዓይን፣ ጆሮ፣ ፀጉር፣ አፍንጫ፣ ከናፍር፣
ልብ፣ ሳንባ፣ ጉበት፣ ሁለት እጅ፣ ሁለት እግር፤
ብዙ… ብዙ ነገር ::
የእነዚህ ጥቃቅን የህዋሳት ድምር፣
ሙሉ ሰው አርጐናል በዚች የዋህ ምድር፣
ሰው ሆነን እንድንኖር፡፡
ልክ እንደሰው ሁሉ…
ሙሉ አካላት ያላት የሰው ልጅ አምሳያ፣
ቅድስት አገርሀ ናት ታላቋ ኢትዮጵያ፤
“ጥቃቅን ህዋሳት” መስለው የሚታዩት፣
መላ ህዝቧ ናቸው ዳር እስከዳር ያሉት፡፡
ከእኒህ ህዋሳቷ አንዱ ከጐደለ፣
ነገር ተበላሸ፤ ጤናዋም ተዛብቶ አደጋ ላይ ዋለ፣
ለእኔ እንደሚመስለኝ…… ከእኒህ ህዋሶቿ፣
“ አማራ” “ኦሮሞ” የሚባሉት ናቸው ጠንካራ ክንዶቿ፣
ሁለቱ ዓይኖቿ፡፡
በሁለቱ ዓይኖቿ ከዓይኖቿ በአንዱ ጉድፍ ከገባበት፣
ጤና ይርቃታል፤ ይሳናታል ማየት፡፡
እርግጥ ነው ክቡራን ጉድፎቿ በዝተዋል፣
መተት ደጋሚዎች ቁጥራቸው በርክቷል፤
ሞቷን የሚመኙ ጉጉት አሞራዎች፣
በየዋሻው አሉ መርዶ ነጋሪዎች፡፡
በተለይ … በተለይ.. “ፌስቡክ” በሚባለው፣
የሟርተኞች ምሽግ የሚግተለተለው፣
እንዲያው ሳናጣራ ከተቀባበልነው፣
ፍፃሜው መራራ፣ ግቡም መፋጀት ነው፡፡
በወገኑ አስከሬን በሰው ንብረት መውደም፣
የሚደሰት ካለ እሱ ሰይጣን እንጅ ፍፁም ሰው አይደለም!
አንዱ ያንዱን ዝና ደፍሮ እያጐደፈ፣
አንዱ በሌላው ላይ እየተሰለፈ፣
እንዲፋጅ ኮ ነው ፌስቡክ በሚባለው መተት የተጻፈ፡፡
ግን… በተራ አሉባልታ፣ በመሠሪ ወሬ፣
አትበጣጠስም፤ አትፈርስም አገሬ፤
ያው….! ምልክቱ ታይቷል፣
“ዓባይ ኬኛ” ብሎ፣ ወጣቱ ተነስቷል፤
አዎ…!
ኦሮሞ የእኛ ነው፤ አማራ የኛ ነው፣
ትግሬና ከንባታ አፋሩ፣ ሶማሌው፣
ሐድያው፣ ጉራጌው፣ ቅማንቱና ኮንሶው፣
ሌላውም፣ ሌላውም ሁሉም የእኛ አካል ነው፣
የሚያበጣብጠን ምን አይነት ጋኔን ነው?!
እንደ ብዙ ህዋስ፣ እንደ አንድ ሰው ገላ፣
ፀንተን እንኖራለን ምን ትሆን አንኮላ?
ወዮልህ እንግዲህ በደም የምትነግድ አሳባቂ ሁላ፡፡
ኦሮሞ አማራ ነው፤ አማራም ኦሮሞ፣
በፍፁፍ አይኖሩም አካላቸው ታሞ፤
እያደር ይድናል፤ በፌስ ቡኩ ሳይሆን በራሱ ታክሞ፡፡
አንዱ ካንዱ ሳይበልጥ፣
አንዱ ላንዱ ሳይጐብጥ፤
አንዱ አንዱን ሳይረግጥ፣
በፍቅር ለመኖር በል እንግዲህ ቁረጥ!
ተናግሮ እሚያሳምን አባቦኩ እያለ፣ መክሮ የሚመልስ አባገዳ እያለ፣
ስንቱ ሼህ፣ ስንቱ ቄስ ባገር ሞልቶ ሳለ፣
አንድነትን መስበክ፣ ከፋፋይን ማረቅ ምነው አልተቻለ?
ግደለህም ጐበዝ !ክፋ መንፈስ አለ፡፡
ምስኪኑን ሱማሌ ከደጉ ኦሮሞ፣
ኦሮሞን ከአማራ፣ ከቤኒሻንጉሉ፣ በመርዙ አቀያየሞ፣
ለማፋጀት ቋምጦ ሾተሉን ያሰላ፣
የፌስቡኩ ሰይጣን አፈርድሜ ይብላ!
ከእንግዲህ በኃላ…..
አንዱ በአንድ አይዘምትም፤
አንዱ በአንዱ አይሞትም፤
ሰላሙን ተነጥቅ በገዛ አገሩ ላይ አይንከራተትም፡፡
እንዲያውም በተራው ከፋይ ይከፈላል፤
መርዘኛ፣ ሰብቀኛ እንደአምጃ ጉልጥምት ሥሩ ይነቀላል፤
በእሱ መቃጠር ላይ እንደ እህል ተዘርቶ ፍፁም ስላማችን እንደ አዲስ ይበቅላል፡፡
ልዩነት ውበት ነው ኢትዮጵያን ያደምቃል፤
ሕዝብስ የህዝብ ጠላት መቼ ሆኖ ያውቃል?
ኢትዮጵያ ሆይ! ስሚኝ እስኪ ልመርቅሽ፣
ሁለት ዓይኑ ይጥፋ በክፋ የሚያይሽ፡፡
ሕዝብሽን ከፋፍሎ ለመክበር የሚሻ፣
ዘርማንዘሩን ያጥፋው እስከ መጨረሻ፣
ተንኮል እንደ ገመድ እየተበተበ ሕዝብን የሚያጣላ፣
የፌስቡኩ ጋኔን አፈርድሜ ይብላ!!
ሃይማኖት ሳይለየን፣ ቋንቋ ሳይገድበን፣
ብዙ ብንሆንም እንደ አንድ ሰው ቆመን፣
ሰላሟ የበዛ፣ ከችጋር የፀዳች ታላቋ ኢትዮጵያን፣
በጽኑዕ ክንዳችን እንገነባታለን!
አትጠራጠሩ……….!
ደመኞቿ ወድመው “እፎይ” እንላለን!!
የፌስቡኩ ጋኔን ክንፉ ይሰበራል፣
ሰላም በምድራችን እንደ እርግብ ይሰፍራል፣
ዳሩ…
በምኞት አይደልም ይኸ የሚሆነው ፤
ለሰላም ዘብ ቆመን ሌት ቀን ሥንሰራ ነው፡፡
አበረ አዳሙ
ጥቅምት 25/2010 ዓ/ም
ባህር ዳር
በአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች የጋራ መድረክ ላይ የቀረበ
Amhara Mass Media Agency