የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት በሆኑት በ ዶ/ር ኢሳያስ አደፍርስ አማካኝነት የመጀመሪያውን ውጤታማ የሆነ የአንጎል እጢ ቀዶ ህክምና አደረገ፡፡

0
1292

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት በሆኑት በ ዶ/ር ኢሳያስ አደፍርስ አማካኝነት የመጀመሪያውን ውጤታማ የሆነ የአንጎል እጢ ቀዶ ህክምና አደረገ፡፡

ህክምናው ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለመጣች የ16 ዓመት ታዳጊ የተካሄደ ሲሆን ታዳጊዋ በአሁኑ ሰዓት በሆስፒታሉ ተኝታ ህክምናዋን እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ ታካሚዋ ከበፊቱ በተሻለ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ኢሳያስ አደፍርስ እንዲሁም ወላጅ አቧቷ ገልፀዉልናል፡፡

ከአሁን በፊት በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ በአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ ባለሙያ ባለመኖሩ እና በቁሳቁስ እጥረት ሳቢያ ህክምናውን ማከናወን ባለመቻሉ ታካሚዎች ለእንግልት እና ለስቃይ ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኢሳያስ አደፍርስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ አምስት ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከስምንት ወራት በፊት ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመመለስ የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በተለይም በህፃናት ላይ በተፈጥሮ የሚኖሩ የነርቭ የአፈጣጠር ችግሮች (የነርቭ ዘንግ ክፍተት) እና አንጎል ውስጥ የፍሳሽ መብዛት ላይ እየተሰራ ሲሆን በአደጋ ምክንያት የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር መጎዳት ላይ በተሻለ መልክ ተጠናክሮ እየተሰራ እንደሆነ እና ከዚህ በፊት የጀርባ ቀዶ ጥገና ህክምናዎች መከናወናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ከህፃናት ቀዶ ጥገና ህክምና በተጨማሪ የአዋቂዎች የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና በመሰራት ላይ ሲሆን ህክምናውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ከዩኒቨርሲቲው እና አጋር አካላት የተለመደው ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን በመግለፅ ከቀላል እስከ ከባድ የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ህሙማን መጥተው በማማከር አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ ዶ./ር ኢሳያስ አደፍርስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዘገባ – ደጄ አማረ
University of Gondar, Ethiopia