Ethiopia: Gonder Jan Tekel Warka!

0
1848

ጎንደር ጃንተከል ዋርካ | በአፄዎቹ ገፅ |
ጎንደር የአፍሪካ ካሚሎት በሚል ከሚገለጹ የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን አሻራዎች አንዷ ስትሆን ከተማዋ የቅርስ ብቻ ሳይሆን የባህል እና የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከልም ናት። ከ17ኛዉ እስከ 19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መቀመጫ የነበረችውና በአፄ ፋሲለደስ ዘመን የተቆረቆረችው ጎንደር ከባህላዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች በተጨማሪ በተለያዩ የሥነ-ጽሑፍና የስነ ስእል ጥበቦች የበለጸገች ናት፡፡
ከተማዋ በጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር በ1636ዓ.ም በአፄ ፋሲል የተገነባውን የፋሲል ግቢን ጨምሮ በርካታ ቅርሶችን በጉያዋ ይዛለች፡፡ ጥቂቶቹን ለማንሳት እቴጌ ምንትዋብ ያስገነባችዉና ድንቅ የስነ ህንፃ ጥበብ ያረፈባት የቁስቋም ቤተ ክርስትያን፣ አድያም ሰገድ እያሱ ያስገነቡትና የኢትዮጵያዉያን የስእል ጥበብ የታየባት ጥንታዊዋ የደብረብርሃን ስላሴ ቤተክርስትያን፣ አፄ ፋሲል ያሰሯቸዉ ጎንደርን ከአጎራባች ከተሞች ጋር የሚያናኟት ሰባቱ ድልድዮች እና ሌሎች ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ ሆኖም ከላይ ከጠቀስናቸው ታሪካዊ ቅርሶች በተለየ በእድሜም ሆነ በርካታ ታሪካዊ ኩነቶችን በማስተናገድ የጃንተከል ዋርካን የሚስተካከለው አይገኝም፡፡
በፋሲል ግቢ በስተ ደቡብ አቅጣጫ የሚገኘዉና በአራዳ እና በፒያሳ መንደሮች አማካይ ላይ የተንሰራፋዉ የጃንተከል ዋርካ የስሙ ትርጉም ሁለት መላምቶች ይንፀባረቁበታል። አንደኛዉ ጃንተከል የሚለዉ ጃንሆይ የተከሉት ሲሆን ሌላኛዉ ደግሞ ” ጃን ” ትልቅ በሚል ትርጓሜ ትልቅ ሰዉ የተከለዉ የሚል ነዉ፡፡ ዋርካዉ ካለዉ እድሜ አንፃር ካየነዉ የሁለተኛው መላምት በይበልጥ ሚዛን የሚደፋ ይሆናል፡፡
በከተማችን ቁጥራቸዉ ከ40 የሚበልጡ በርካታ ሰፋፊና ዕድሜ ጠገብ ዋርካዎች ይገኛሉ፤ ነገርግን ከነዚህ መካከል ረጅም ጊዜን በመቆየትም ሆነ ብዙ ታሪካዊ ክንዋኔዎቹን በማስተናገድ ጃን ተከል ዋርካ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የጃንተከል ዋርካ በ1628 ዓ.ም በአፄ ፋሲለደስ የተገነባዉን የፋሲል ግንብን ከ100 ዓመታትን በላይ እንደሚቀድም የታሪክ ድርሳናት የሚያስረዱ ሲሆን በወቁቱ ንጉሱ አፄ ፋሲለደስ ወደ ጎንደር መጥተዉ ቤተመንግስታቸዉን ከማሰራታቸው በፊት ከዋርካዉ ስር ድንኳን ሰርተው ህዝቡን ያስተዳድሩ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሌላ በኩል አሁን ከምናየዉ የጃን ተከል ዋርካ አጠገብ በእድሜ የቀደመ ሌላ ዋርካ እንደነበርና ዕድሜ ጠገብ በመሆኑ ምክንያት ሊወድቅ እንደቻለም ይነገራል፡፡
ጃንተከል ከሶስት ክ/ዘመናት በላይ እንደመቆየቱ በእነዚህ ጊዜያቶች በርካታ ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና የተለያዩ ኩነቶችን አስተናግዷል፡፡ አጤ ቴዎድሮስ ደጃዝማች ውቤን ድል አድርገው ደረስጌ ማርያም የንግሥና ሥርዓታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ጎንደር መጥተው የንግሥና በዓላቸውን ለማክበር በፈለጉበት ወቅት ካህናት የቴዎድሮስን የትውልድ ሐረግ በመቁጠር “መንገሥ የሚችለው ከነገሥታት የሚወለድ ነው” በማለት በቴዎድሮስና በካህናቱ መካከል የተነሳው ክርክር የተደረገው በዚህ ታሪካዊ ቦታ ነዉ፡፡
ከዚህም ሌላ አሁን ወደ ከተማዋ አደባባይ የዞረዉ የመስቀል በአል ቀደም ባሉ ጊዜያት ደመራው ይደመር የነበረው በንጉሡ አደባባይ “ጃንተከል ዋርካ” ወይም በፊት በር ነበር። ይህ ዋርካ ከጥንት ጀምሮ የከተማይቱ ዋና አደባባይ ሲሆን፥ ቦታዉ ደማቁን ዓመታዊ የመስቀል በዓል ከማክበር ባሻገር አዋጅ የሚነገርበት፣ ትልቅ የገበያ ማዕከል ሁኖ ገበያተኛው የሚገበያይበት፣ ሹምሽር የሚለፈፍበት፣ ወንጀለኞች የሚቀጡበት፣ ሊቃውንቶች ጉባየ የሚያስተናግዱበት፣ ለነገስታት ደጅ የሚጸናበት፣ መስዋዕት የሚቀርብበት፣ ነገስታቱ ወታደሮቻቸውን የሚመለምሉበት፣ ባላባቶች ተሰብስበው የሚመክሩበት፣ የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት፣ ፍቅረኛሞች የሚገናኙበትና የመሳሰሉ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግባራት የሚከናወኑበት ሥፍራ ነበር፡፡
ዋርካዉ ካስተናገዳቸዉ ኩነቶችና ከረጅም እድሜዉ ሌላ ከጥንት ጀምሮ እየተላለፈ የመጣ ቀደምት ብሒልም ይነገርበታል፡፡ ይህም የጃን ተከል ዋርካ ቅርንጫፎች መሬት ከነካ በሴቶች ላይ ችግር ይፈጠራል የሚል እምነት የነበረ ሲሆን ይህንንም ምክንያት በማድረግ የዋርካዉ ቅርንጫፎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በብረትና በእጨንት ባላዎች ይደገፍ ነበር፡፡
ቦታዉ በበርካታ ታሪኮችና ትዉፊቶች የተከበበ ቢሆንም በክልሉም ሆነ በከተማው ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤቶችም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት በደንብ ተይዟል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጎብኞችና ተመራማሪዎች ወደቦታው ሲመጡ ስለዋርካዉ የሚገልፁ የጡሁፍም ሆነ የምስል ማስረጃ በበቂ ሁኔታ ቢዘጋጅ መልካም ነዉ እንላለን፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡
በአፄዎቹ facebook ገፅ