I am original and real Raya!!!!!

0
1633

ራያ ነኝ፣ ያውም ራያ!!!!!
(((ማስታወሻነቱ ፤ ራያነትን ባጠባችኝ ጡትና በዘመን አይሽሬ የራያነት ትርክት ነፍሴን ላበጀችው የራያዋ ሸጋ ለእናቴ ታድሳ ተፈራ )))
እንደ አቦሸማኔ፣ እንደዝናር ካራ፣
እንደ ዞብል ዳዩ፣እንደ መንደፈራ፣
ከድብ ከቅብቅቡ፣ጃምዮ እምዘራ፣
የነ ዳርጌ ሚዜ፤
የነኩሌ ወንድም፤ ረብሶ ደንጎራ ፤
መገን የራያ ልጅ፤
የነካኩኝ ጊዜ ፤
የሰማዮን እንጅ፣ አፈር የማልፈራ።
ሄይ ብየ እማገሳ፣ እንደጋራ ሌንጫ፣
ጥርሴ የነተረው፣ በወይራ ሟሟጫ፣
እርጎ ያሰከረኝ፣
በወይራና በሬት፤ በታጠነ ዋንጫ።
ይህን ፍትፍት ጥርሴን ፤
ፈገግታውን አይተው ፤ ሞኝ ነው ለሚሉ ፤
በጮሌ ቀረርቶ ፤
እርሻውን እንቀማው ፤
በሚል የጅል መተት ለሚንጦለጦሉ ፤
እጄ መረሬ ነው ፤
መገልበጥ መመንሸር ፤ ይኸው ነው አመሉ ።
ራያ ነኝ ያውም ራያ
መቀነቴ፣ ሀሸንጌ ዳሩ፣
ተረከዜ፣ መሆኒ ምድሩ፣
ከራማየ፣ እንደ አጋማረ፣
ጮቢ በር ላይ ፣ ባላ ነኝ ያለ።
ራያ ነኝ፣ ያገው ገመገም፣
ራያ ነኝ፣ የትግሬ ገጠም፣
ራያ ነኝ፣ ያፋር አንገቱ፣
ከዋጅራት፣ እስካዳይቱ፣
የለበስኩት፣ ሸጋ ጎንቢሶ፣
ሮቢት ላይ፣እዳይት ቀምሶ፣
ጎፈሬየ፣ ሚዶ ተነቅሶ፣
አርከይ ልቤ፣ ብሎ ቢያገሳ፣
የእርቦው ጥለት፣ ዝናር አነሳ።
እንደ ጎመጅ ላም፣ እንደጓደናዋ፣
ዋጃ ነው ማእጠንቷ፣ መረማመጃዋ።
አላ ነው ጠበሏ፣ የታጠበችበት፣
ጎሊና ፍል ውሃ፣ የተሞቀችበት።
ከቦለቂያው ስር፣ከጭሱ ማእጠንቱ፣
አሳዲ ሙናዋ፤
ሸጋ ልጅ ይፈልቃል፣ ልክ እንደወተቱ።
ራያ ነኝ የዋጃ፤
ባለውጅግራ ባለጠመንጃ፤
አትነዝንዘኝ እንጃልህ እንጃ ፤
ልቤም አይመኝ፤
የሰውን ቅብቅብ፤ የሰውን ጥጃ፤
ስንዝር የማልሰጥ ፤ እርቦና ኩታ ፤
የማልቀላውጥ ፤
ከሰው አውድማ ከሰው ገበታ ።
ራያ ነኝ እንጅ ፣
ራያ የራሴ፤ የማንም ያልሆንኩኝ፣
በአደሱ በቁኒው፤
ሸላልሙኝ ነው እንጅ፣ ውሰዱኝ መች አልኩኝ።
ምኞት ያሰከረው፤
ይኸ ቅብቅብ ገፊ፤
እንኳን ሊወሽመኝ፣ ሊተኛብኝ ቀርቶ፣
ማን ጎበዝ ያመሻል፣ ከማጀቴ ገብቶ።
ያላማጣ ልጅ ናት፣
የጥሙጋ ሸጋ፤የላይኛው ኮረም፣
መስሏቸው ነው እንጅ፤
አዳሪ ሙናዋን፤
ከራያ ልጅ ድካ፣የሚለያት የለም።
የሸሆቹ ልጅ ናት፣
የዳውድ ማርዬ፤ የበድሬ መሃመድ፣
ገደመዩ በላይ፤
የሚዘየንላት የዛውያው መደድ።
በሀድራው መኪና፣
በማሽላው አንገት፤
ባውድማው ጭፍቆ፤
በእርጎ በመንገሌው የተዘወረችው፣
መገን የራያ ልጅ፣
በእርጎ ዳማይ ጥርሷ፤
በሚያምረው ወገቧ፤ ስንቱን ሾፈረችው።
ሆርማት ወንዛ ወንዙ፣
ወይለት ጥጋ ጥጉ፤
አላውሃ መሌው ዳር፤
ውሃው ገነፈለ፤ ተናደ መሬቱ፣
ባለ ጥርቅ ጫማ፤ ባለ መልጎሚቱ፤
መጥታለች ማለት ነው፣ ዘልቃለች ልጅቱ።
ልክ እንደመሬቱ፣ እንዳፈሩ ስባት፣
ልውሰድሽ እያለ፤
ያችን የራያ ልጅ፣ስንቱ ሰው ተራባት፤
እምቢኝ ነው አመሏ፤
አይወስዱሽም የሚል፤ ያባት ቃል አለባት።
ራያ ነኝ፣ያውም ራያ፣
ጎረቤቴ፣የጁ ወልዲያ።
መቀነቴ፣ባለመለያ፣
ማሽላየ፣ ሰንደቅ መስቀያ።
ጎንቢሶየን፣ ያገለደምኩኝ፣
ድካው ጠፋኝ ብየ፣ ድካ ላይ ያልቆምኩኝ፣
የራሴን በሽታ፣በራሴው ያከምኩኝ።
ራያ ነኝ አባ ግርሻ፣
አዋዶ ኗሪ፣ ሞፈርና እርሻ።
መገን ጃሪ ጋማ፣ጋማ አባ ጅጉርቴ፣
እሱም ለመንገሌው፣እኔም ለወተቴ።
ጃውሳው ተነሳ፤
ሄደ ተራመደ፣ ወረደ ጎመጅ፣
መሌውን ሰንጥቆ፤
መስኖውን ሸንሽኖ፣ እርሻውን ሊያበጅ።
ወረደ ይሉኛል፣
ዋጃ ጥጋጥጉን፤ ታቹን በጎለሻ፣
እንደተሸከመ፤ ጋንፉሩን ማረሻ፤
መቸም አይጨክንም፣በሸጋና በእርሻ።
ራያ ነኝ፣አዘቦ፣
ሽንሽን፣ወርቀዘቦ፣
ላካላቴ፣ማይ ማዮ እርቦ፣
ሳቄ፣የማር ገንቦ፣
የሚፈሰው፣ወደ ቆቦ።
ራያ ናት፣ራያ ናት እሷ፣
ታሽማ ብቅ አለች፣ባሽኩቲ ባደሷ።
ቅምጥል ናት ልጅት፣ አራሽ ነው አባቷ፣
ቀሚሷ ናብኝ ነው፣ ሴኮ ነው ሰአቷ።
እንደው ብቅ ስትል፤
እንደ በልጅግ ጥይት፣ ያበራል አንገቷ።
ይህች የራያ ልጅ፣
በጥርሷ ውቅራት፤
በከንፈሯ ማእጠንት፤ ባይኗ ሰው ገላለች፣
ፍቱልኝ እያለች፣
ማርያምን ፍለጋ፤ ራማ ገብታለች፣
በራማ በራማ፣ በወለላይቱ፣
ከራያ ልጅ ከንፈር፣
የውበት ማጠኛ፤ ወጥታለች ጣይቱ።
ራያ ነኝ፣ዥንጉርጉር፣
ቀለመ ብዙ፣እንደነብር።
ሙልት ያልኩኝ፣
ኦሮሞን ድረውኝ፣ ትግሬን ያዋለድኩኝ፣
አፋርን ተድሬ፣ ወፍላን የሞሸርኩኝ።
አገው ድካየ፣ላዩን ሃሸንጌ፣
ወንዜ ከዳዮ፣ እስካምባላጌ።
የአፋር ሚዜ ነኝ፤ ኣ መሃሰኒ፣
እርሻየ ጎመጅ ፣ቤቴ መሆኒ።
ያማራ ማእጠንት ያውም ያማራ፣
በሮቢት ሸማኔ፣
አገሬን ሚያለብስ፤
ባለ ልዩ ጥለት፤ ጥበብ የምሰራ።
ራሴን ነኝ፣
የራሴ ነኝ፤
በዶባ ውብ ቀለም ፤ ሸማ የፈተልኩኝ፣
የሁላቸው ሚዜ ፣
ግን ደግሞ ፤
ግን ደግሞ ፤ የማንም ያልሆንኩኝ።
ገና ባሻጋሪ ፤
የትፍትፌ ቅቤ በአደስ የወፈረው ፤
ከጀማው መሃከል ፤
ራያ ናት ብሎ ጩኾ ሚናገረው ፤
የጅስሜን ወዘና ፤
ራዩ መሆኔን ፤ ከቶ ማን ነገረው ??!!
በወንዝ መሃከል ፤
የጅረት ውለታን ፤ እየደፈጠጡ ፤
ወንዙ የሞላ እለት ፤
ጅረት የለም ብለው ፤
በወንዛቸው ኮርተው አይን በልተው መጡ ።
ጅረት ያቄመ ቀን ፤ መች ጭቅጭቅ ያውቃል ፤
ከጎራ ላይ ቆሞ ፤
ጭል ጭል እያለ ፤
ያጎፈረውን ወንዝ ፤
አልሰጥም እያለ ፤ መልካውን ያደርቃል! !!
ራያ ነኝ አንድ ጅረት ፤
ወንዝ አየሁ ብዬ ፤
ከወንዝ ግንፋይ የማልለገት ፤
እንደመጭለፊያ እንደ ሽንክና ፤
ጅረቴን ይዤ ፤
ተውኝ ልንዛፈል ፤ ወደ አላ መሌ ወደ ጎሊና ።
ራያ ነኝ ወራባየ ፤
የአናዎቹ ልጅ የነሸህዬ ፤
ቅብቅቡ የኔ እርሻው የአበየ ፤
ውጣ በሉልኝ ፤
ያን ድካ ገፊ ፤ ያንን ሰውዬ ፤
ከንግዲህ ኻላ ፤
አይዘፍንብኝም ፤
የነየን ነዶ በጥጋብ ልቡ እያበራዬ ።
እያሚና በሎ፣ ሀ በሎ ሸግየ፣
ታችኛው ሮቢት፣ላይኛው ጎብየ፣
ፍቅር ካንች ቀየ፣ ይፈልቃል ቃሮየ።
እንደምን ከረመ፣መገን ጉራ ወርቄ፣
ታክሜ መጣሁኝ፣በጀመአው ስቄ።
የግዳን ምንትራስ፣የላስታ ሙዳይ፣
ተኩለሽ ማለዳ፣ቆቦ አትመጭም ወይ።
እስኪ ገፋ ገፋ፣ ደሞ እንደወተቱ፣
እስኪ ሰበር ሰበር፣ደግሞ እንደምክቱ፣
ሞልቶ እየፈሰሰ፣ሀድራና ሙሀባ፣
አርከይ ክተት ብሎ፣ዛሬ ቆቦ ገባ።
በሸዋየ ቦልጋ፣
በጥሌ ችኳንታ፤
መገናይ እያለ፤
አትግፉኝ እያለ ፤
ልቀቁኝ እያለ ፤
ሽመሉን ወድሮ ፤
ገለል በል እያለ ፣ ራያ እማይሄድ፣
እንኳን በሊጋባ፣ አይሽር በዘወልድ።
ሀበከው!!!!!!! ሀበከው!!!!!!!
(ጃኖ መንግስቱ፣ወሎ፣ራያ))