የ2010 ዓ.ም. የአጽዋማትና የበዓላት አወጣጥና ሥርዐቱ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

0
1928

❖የ2010 ዓ.ም. የአጽዋማትና የበዓላት አወጣጥና ሥርዐቱ

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ንዌጥን በረድኤተ እግዚአብሔር ጽሒፈ ባሕረ ቀመረ ሐሳብ ዘድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን

ብዙዎች አባቶች እና ወንድሞች በውስጥ መስመር የ2010 ዓመት የባሕረ ሐሳብ የጉባኤውን አወጣጥ እንድልክላችኊ በብዛት የጻፋችኹልኝ በመኾኑ፤ ባሕረ ሐሳብን መስከረም 1 ለምታወጡ ይልቁኑ በውጪም ላላችኊ አበውና አኀው እነሆ ብያለኊ

ይኽ መጽሐፍ መርሐ ዕውራን፤ ባሕረ ሐሳብ ይባላል፤ መርሐ ዕውራን አለው አላዋቂዎችን መርቶ ወደ ዕውቀት የሚያደርስ ስለኾነ፤ ሐሳብ ቊጥር ነው ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኀጢአቶሙ ወለእለ ኢኃሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ እንዲል፤ ባሕረ ሐሳብ አለው ባሕር እስኪለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል፤ ከለመዱት በኋላ በልብ ተኝቶ ይውሏል ይኽም መጽሐፍ እስኪለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር አስታውቆ ደስ ያሰኛልና፤ አንድም ባሕር ከለመዱት በኋላ ከመሠረቱ ወርዶ አሸዋ ይዞ ይወጧል ይኽም መጽሐፍ ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር ያስታውቃል ያስመርምራል፤ አንድም የባሕር አዟሪቱ መንገዱ ብዙ ነው የዚኽም መጽሐፍ መንገዱ ስልቱ ብዙ ነውና፤ አንድም ሐሳበ ባሕር ይላል ባሕር ዘመን ነው ሠፈራ ለባሕር በመሥፈርት ወደለዋ ለዓለም በመዳልው መኑ ዘአእመረ ስፍሐ ሰማይ ወዕመቀ ቀላይ እንዲል በባሕር ውስጥ ያለውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው እንዳያውቀው በዘመንም ኹሉ የሚደረገውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው አያውቀውምና፤ ኢኮነ ለክሙ ታእምሩ መዋዕለ ወአዝማነ ዘሠርዐ አብ እንዲል፡፡ 

❖ ድሜጥሮስ ማለት መጽሔት ማለት ነው፤ አንድም ፀሓይ ማለት ነው ሰውን በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና የድሜጥሮስ ትውልዱ ነገዱ ከአዝማደ እስክንድርያ ነው ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ ያባቱ ወንድም ያጐቱ ሴት ልጅ ነበረችው አባቷ ሲሞት ልጄን ከልጅኽ አትለይብኝ አደራ ብሎት ሞተ፤ አብረው አደጉ አካለ መጠን አደረሱ ዘመኑ መናፍቃን የበዙበት ነበርና ርሱንም ከሌላ ብናጋባው ርሷንም ለሌላ ብንድራት ከሃይማኖት ይወጣሉ ከምግባር ያድጻሉ ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንጻ ሥጋ ይፍረስ ርስ በርሳቸው እናጋባቸው ብለው መከሩ መክረው አልቀረ ሠርግ አደረጉ፤ ሥርዓተ ከብካቡ ሲፈጸም ሥርዓተ መርዓዊና ሥርዓተ መርዓት ያድርሱ ብለው ከጫጉላው ቤት አግብተዋቸው ኼዱ፡፡ 

❖ ርሷን አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶ ድሜጥሮስ ያንት ወንድምነት ለኔ የኔ እኅትነት ላንተ አልበቃ ብሎ የባዕድ ሥራ እንሥራ አልኽን አለችው፤ እኔስ የናት ያባቴን ፈቃድ ማፍረስ ይኾንብኛል ብዬ ነው እንጂ ፈቃዴም አይደል ፈቃድሽ ካልኾነ አንተወውምን አላት እንተወው አለችው፤ እንኪያስ የተለያየን እንደኾነ አንችን ለሌላ ወንድ እኔንም ለሌላ ሴት ያጋቡናልና መስለን እንኑር አላት እንኑር አለችው፤ በአንድ ቤት በአንድ አልጋ እየተኙ 48 ዘመን ኖሩ፤ ርሱን መልአኩ ቀኝ ክንፉን ርሷን ግራ ክንፉን እያለበሳቸው ያድራል፤ ሲነጋ በመስኮቱ በአምሳለ ርግብ ወጥቶ ሲኼድ ያዩታል ስለምን ቢሉ በቅተዋልና አንድም በንጽሕናቸው ይትጉበት ብሎ::

 በዘመኑ የተሾመው ሊቀ ጳጳስ ሉክዮስ ሉክያኖስ ይባላል አረጀ ደከመ፤ ሕዝቡ ተሰብስበው አባታችን አንተ አረጀኽ ደከምኽ ካንተ ቀጥሎ የሚሾመውን ንገረን አሉት፤ እናንተም ወደ እግዚአብሔር አመልክቱ እኔም ወደ እግዚአብሔር አመለክታለኊ ብሎ ቀን ቀጥሮ ሰደዳቸው ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጣ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ካንተ ሊባረክ ይመጣል ካንተ ቀጥሎ የሚሾመው ርሱ ነው አለው፤ ሕዝቡም በቀጠራቸው ቀን መጡ አገኛችኹት አላቸው እኛስ አላገኘንም አሉት እኔ አገኘኹላችኊ አላቸው፤ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ሊባረክ ይመጣል ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ርሱ ነው ለጊዜው እንቢ ይላችኋል ግድ ብላችኊ ሹሙት አላቸው፡፡

ይኽም ድሜጥሮስ ተክል አጽድቆ ዕርፍ አርቆ የሚኖር ገበሬ ነበር ይላሉ፤ ከዕለታት በአንድ ቀን ተክል ለመጐብኘት ከተክል ቦታ ገብቶ ሳለ ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ አገኘ ይኽንስ ከሊቀ ጳጳሱ ወስዶ ሊባረኩበት ይገባል ብሎ በንጹሕ ዕቃ አድርጎ ይዞ ኺዶ ንገሩልኝ አለ፤ እንዲኽ ያል ይዞ የመጣ ሰው ከደጅ ቁሟል ብለው ነገሩት እንዲኽ ያል ይዞ የመጣውን ከደጅ ያቆሙታልን ያገቡታልን እንጂ ግባ በለው አለው፤ ገብቶ ተባርኳል፤ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ይኽ ነው ብሏቸው ወዲያው ዐረፈ፤ ቀብረው ሲመለሱ ሕዝቡ ተሾምልን አሉት በማርቆስ ወንበር የሚቀመጥ የተማረ ነው ደግሞም ንጹሕ ድንግል ነው፤ እኔ እንደምታውቁኝ ሕዝባዊ ነኝ ደግሞም ሥጋዊ ነኝ እንደምን አድርጎ ይኾናል አላቸው፤ እኛስ አባታችን ያዘዘንን ትተን ሌላ አንሾምም አሉት፤ ርሱም እንደማይተውት ዐውቆ ሊቀ ጳጳሱ ሲሾም ምን ያደርግላችኊ ነበር አላቸው አንቀጸ አባግዕን አንብቦ ይተረጒምልን ነበር አሉት ወንጌል አምጡልኝ አለ፤ አመጡለት እንኳን ትርጓሜውን ንባቡን አያውቀው የነበረ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ተርጒሞላቸዋል፤ ይኽም ብቻ አይደለም ብሉይና ሐዲስ ተርጒሟል፡፡

 ከዚኽ በኋላ ከደጀ ሰላም ቆሞ አንተ በቅተኻል ተቀበል አንተ አልበቃኽም ቆይ እያለ ከልክሏቸዋል፤ ሕዝቡም ቆንጆ ሚስቱን ከቤቱ አስቀምጦ እኛን ይከለክለናል ብለው አምተውታል፤ መልአኩም ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእስከ ወብእሲትከ አላ አድኅኖ ሕዝብከ አለው፤ ርሱም ዕንጨት እየያዛችኊ ተሰብሰቡ ብሎ ዐዋጅ ነገረ ምእመናኑም ዕንጨት እየያዙ ተሰበሰቡ ደመራ አሠርቶ በእሳት አቃጥሎ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊቀድስ ገባ ጸሎተ ቅዳሴውን ፈጽሞ ልብሰ ተክህኖውን እንደለበሰ በእሳቱ መኻከል እየተመላለሰ ያጥን ጀመር፤ ሚስቱም ከዚያ ነበረችና ስፍሒ አጽፈኪ ልብስሽን ዘርጊ አላት ዘረጋች እሳቱን እየታፈነ ከልብሷ ላይ አደረገላት ልብሷ ሳይቃጠል ቀርቷል ሕዝቡም አባታችን ይኽን ተአምራት ያደረግኸው ስለምን ነው አሉት፤ አምታችኹኝ አላቸው፤ አላበጀንም በድለናል ይቅር በለን አሉት፤ ይፍታሕ ወይኅድግ ያንጽሕ ወይስረይ ብሎ ናዟቸዋል፤ ኑዛዜ ከዚያ ወዲኽ ተጀምሯል፡፡

 ድሜጥሮስ በተሸመ በ27 ጌታ ባረገ በ207 ዘመን ይኽን መጽሐፍ ተናግሮታል፤ ስለምን ቢሉ ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ ርሱ የነበሩ ምእመናን ዐቢይ ጾምን የጥምቀት ሳኒታ ጀምረው በየካቲት 21 ይፈጽሙ ነበር፤ ሕማማትንም ወአጐንድዮሙ መዋዕለ ይላል በመጋቢት ያደርጉ ነበር እንዲኽ ማድረጋቸው ተጠምቆ ጹሟል ሕማሙም በመጋቢት ነው ሲሉ፤ አጽዋማትን በዓላትን እንዳገኙ ያደርጉ ነበር፤ ርሱ ግን በዘአለበዎ መንፈስ ቅዱስ ይላል ሰኞ የሚኾነውን ከሰኞ ረቡዕ የሚኾነውን ከረቡዕ ኀሙስ የሚኾነውን ከኀሙስ ዐርብ የሚኾነውን ከዐርብ እሑድ የሚኾነውን ከእሑድ እንዳይወጣ ኢየዐርግ ኢይወርድ እየሰጠ ወስኖታል፤ አይወጣም አይናወጥም ቢናወጥስ አጽዋማት በዓላትም እንደቀድሞ በኾኑ ነበር፤ ርሱም በዘአለበዎ መንፈስ ቅዱስ ባልተባለም ነበር፡፡ 

 ድሜጥሮስ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፤ ርክብ፣ ምሕላ ድኅነት ከረቡዕ፤ ዕርገት ከኀሙስ፤ ስቅለት ከዐርብ እንዳይወጣ ግለጽልኝ ብሎ ግብር ገባ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከሌቱ በ23 በ23 እስከ 7 ሱባኤ ቈጥረኽ 161 ይኾናል፤ 150ውን ገድፈኽ 11 ይተርፋል፤ አበቅቴ በለው ብሎታል፤ መልአኩም ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ከመዓልቱም እስከ 7ት ሱባኤ ቈጥረኽ 49 ዕለት ይኾናል 30ውን ገድፈኽ 19ኝን መጥቅዕ በለው ብሎታል፤ የድሜጥስ ጥንተ አበቅቴና መጥቅዕ ይኽ ነው፡፡ 

 የሌሊቱን አብዝቶ የቀኑን ስለምን አሳነሰው ቢሉ የሌሊት ልቡና ክት የቀን ልቡና ባካና ነውና፤ አንድም ቀን ሲፈርድ ሲተች ጉባኤ ሲያደርግ ይውላልና፤ ሕማማትን ያስቀድማል ትንሣኤን ያስከትላል ሐዘኑ ለደስታው እንዲመች፤ ካላዘኑ ደስታ ካልጾሙ ፋሲካ የለምና፤ የሐዲሱን ያስቀድማል ዘመኑ ነውና የብሉዩን ወደኋላ ያደርጋል፤ አልቦ መጥቅዕ ወአበቅቴ አንድ ወገን ያደርጋል፤ ታሪክ፣ መቅድም፣ አርዕስት እየሰጠ ወስኖታል፤ ታሪኩ ይኽ ነው፤ መቅድሙን ያመጣዋል፤ በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብለን ምንም ለአጠይቆ አካለት ሦስት ስላልነ በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ጸሎቱ ልመናው በረከቱ ክብሩ ይደርብንና የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ የተናገረውን የባሕረ ሐሳብ ቊጥር መጽሐፍን በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን፡፡

 እግዚአብሔር እንደዛሬው ኹሉ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት ሳለ ክብሩ በብቻው እንደቀረ ዐውቆ ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፤ አስቦም አልቀረ ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የቀረውን ፍጥረት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ ፈጠረ “ወኲሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምህሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተገብሮ፤ ወእንዘ ኢየኀድግ ርእሶ ዘእንበለ ሰማዕት፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘንተ እምአፍአ ብከ ሰማዕት ወመምህር ዘይመርሐከ ኀበ ዝንቱ፤ ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ” እንዲል፤ እግዚአብሔርስ የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቈጠር ፍጡር ተናግሮ ባልፈጸመውም ነበር፤ እየወገን እየወገኑ ግን ብዙውን አንድ ብዙውን አንድ እያሉ ቢቈጥሩ ከእሑድ እስከ ዐርብ የፈጠረው ሥነ ፍጥረት 22 ነው፡፡

 እስከዚኽ አርዕስት ነው፤ ይኽንንም በሥነ ፍጥረት ይመለከቷል፤ የፀሓይ ጥንታት ሦስት የጨረቃን ዐምስት የሚል ነውና፤ ይኽ ዓለም የተፈጠረበት ዕለተ እሑድ ጥንተ ዕለት፤ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፀዋት የተፈጠሩበት ዕለተ ሠሉስ ጥንተ ቀመር፤ ብርሃናት የተፈጠሩበት ዕለተ ረቡዕ ጥንተ ዮን ይባላል፤ “እሑድ ወሠሉስ ወረቡዕ ዘውእቶሙ ሠለስቱ ጥንታት” እንዲል

 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ቢቈጠር በፀሓይ 7510 ዘመን፤ ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ የነበረው በፀሓይ 5500 ዘመን፤ በጨረቃ 5668 ዘመን ከ10 ወር ከ9 ዕለት፤ ይኽ ዓመተ ኩነኔ፣ ዓመተ ፍዳ ይባላል፡፡ ከልደተ ክርስቶስ ወዲኽ ያለው ግን በፀሓይ 2010 ዘመን ነው ይኽ ዓመተ ሥጋዌ፣ ዓመተ ምሕረት ይባላል፤ መላው ዓመተ ዓለም ነው፤ ዓመተ ዓለም ባለው ዓመተ ምሕረት የሚል ይገኛል፤ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድም ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል፤ ስለምን ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት አለው ቢሉ? ሰው በዚኽ ዓለም ሳለ ኀጢአት ሠርቶ ንስሓ ቢገባ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት የሚያገኝበት ስለኾነ ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል “በዕለት ኅሪት እሰምዐከ ወበዕለተ መድኀኒት እረድአከ ወናሁ ይእዜ ዕለት ኅሪት ወናሁ ዮም ዕለተ አድኅኖት” እንዲል፡፡

 ለዚኹም መሥፈሪያ ሰባት አዕዋዳት አሉት፤ ምንና ምን ቢሉ? ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡ ከሊኹም ሦስቱ በዕለት አራቱ በዓመት ይቈጠራሉ፤ በዕለት የሚቈጠሩት ሦስቱ ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት ናቸው፤ በዓመት የሚቈጠሩ አራቱ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡ ዐውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቀዳሚት ያሉ ሰባት ዕለታት ናቸው፤ እሊኽም አውራኅን ለማስገኘት በሰባት በሰባት ሲመላለሱ ይኖራሉ “እስመ ኊልቊ ሰብአቱ በኀበ ዕብራውያን ፍጹም ውእቱ” እንዲል

 ዐውደ ወርኅ በፀሐይ ዘወትር ፴ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29፤ አንድ ጊዜ ፴ ይኾናል፤ እሊኽም ዓመታትን ለማግኘት በ፴ በ፴ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡ ዐውደ ዓመት በፀሓይ 365 ዕለት በጨረቃ 354 ዕለት ነው፤ በፀሓይማ ምነው 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት፤ በጨረቃ 354 ዕለት ከ22 ኬክሮስ ከ1 ካልዒት ከ37 ሣልሲት ከ52 ራብዒት ከ48 ኀምሲት አይደለውም ቢሉ “ወበውስተ ውሁድኒ ንብል አልቦ ወኢአሐዱ” እንዲል መጽሐፍ ትርፍ ትቶ ጐደሎ መልቶ መቊጠር ልማድ ነውና ፷ ካልመላ ብሎ እንዲኽ አለ እንጂ ቊጥሩስ አለ “እስመ ልማደ መጽሐፍ ይነግር ኊልቈ ምሉዓ ወፍጹመ ወየኀድግ ዘተርፈ ወይዌስክ ዲበ ሕፀፅ ካልዐ” እንዲል፤ ዕለታትን አዕዋድ አላቸው አውራኅን የሚያስገኙ ስለኾነ፤ አውራኅን አዕዋድ አላቸው ዓመታትን የሚያስገኙ ስለኾነ “ወበከመ ይትወለዳ አውራኅ እምዕለታት ወዓመታት እምአውራኅ ከማሁ ይትወለዳ አዕምሮታት እመከራት ወእምግባራት እንዲል፡፡

 ዐውደ አበቅቴ 19 ዓመት ነው በዚኽ ፀሓይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩበት ኆኅት ይገናኙበታል፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ መምህራነ ወንጌል ሐዋርያት፣ ሊቀ ጳጳሳት ዲሜጥሮስ ከ፳ው አንድ ቀመር አንድ ተረፈ ቀመር፤ ከ፵ው ኹለት ቀመር ኹለት ተረፈ ቀመር፤ ከ፷ው 3 ቀመር 3ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፹ው 4 ቀመር 4ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፻ው 5ቀመር 5ት ተረፈ ቀመር እያላችኊ ቊጠሩ ማለታቸው ከዚኽ የተነሣ ነው “ወእምዘተርፈከ እምዐሠርቱ ወተሰዓቱ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ እስመ ለዛቲኒ ዐሠርቱ ወተሰዓቱ ሙሴ ገብራ በጥበበ እግዚአብሔር ዘይገብሩ ባቲ ፍሥሐ አይሁድኒ ወክርስቲያንኒ” እንዲል

 ዐውደ ፀሓይ 28 ዓመት ነው፤ በዚኽ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ረቡዕ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ረቡዕ ማቴዎስ እንዲል፤ ዕለትን ፀሓይ አለው “ወበትእዛዝከ ይቀውም ዕለት” እንዲል፤ ወንጌላዊዉን ፀሓይ አለው “አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም” ካለው አንዱ ርሱ ነውና፤ በሰንጠረዥ ፀ፣ ደ ይላል፤ ዐውደ ፀሓይ ማለት ነው፡፡

 ዐውደ ማኅተም 76 ዘመን ነው፤ በዚኽ አበቅቴ ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ አበቅቴው 18 ወንጌላዊዉ ዮሐንስ ነው፤ ማኅተም አለው አበቅቴው ለአበቅቴ ወንጌላዊዉ ለወንጌላዊው ፍጻሜ ነውና፡፡ ዐውደ ቀመር 532 ዘመን ነው፤ በዚኽ ዕለት፣ ወንጌላዊ፣ አበቅቴ እሊኽ 3ቱ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ሠሉስ፣ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ሠሉስ ማቴዎስ እንዲል አበቅቴው አልቦ ነው “ጥንቱ ለቀመር ዕለተ ሠሉስ ወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰኑይ ወንጌላዊ ዮሐንስ” እንዲል፤ በዐውደ ፀሓይ ቦታ ዐውደ ማኅተም፤ በዐውደ ማኅተም ቦታ ዐውደ ፀሓይ የሚል ይገኛል፤ ከኹለቱ አንዱ ቢታጣ አንዱ ከቀመር ገብቶ ይቈጠራል፤ ቀመርን ለሦስቱ ስም በሰጡ ጊዜ ዐውደ ቀመር ዐቢይ ቀመር፤ ዐውደ ማኅተም ማዕከላዊ ቀመር፤ ዐውደ አበቅቴ ንዑስ ቀመር ይባላል፤ ዐቢይ ቀመር መደቡ 14 ቊጥሩ 532፣532፤ ማዕከላዊ ቀመር መደቡ 6 ቊጥሩ 76፣76፤ ንዑስ ቀመር መደቡ 3 ቊጥሩ 19፣19 ነው፡፡


ከዚኽም ዓመተ አበቅቴን ለማግኘት 7510 ዘመን በዐቢይ ቀመር ቢቀምሩ 532፤ 532 የተፈጸመለት 14 ዐቢይ ቀመር፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኾኖ 5 ዓመት ይተርፋል፡፡ 

መላውንም በማእከላዊ ቀመርም ቢቀምሩ 76፤ 76 የተፈጸመለት 98 ማእከላዊ ቀመር 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኹኖ 5 ዓመት ይተርፋል፡፡ 

በዐውደ ፀሓይም ቢቀምሩ 28፤ 28 የተፈጸመለት 267 ዐውደ ፀሓይ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኾኖ 5 ዓመት ይተርፋል፡፡ 
 መላውንም በንዑስ ቀመር ቢቀምሩ 19፤ 19 የተፈጸመለት 395 ንዑስ ቀመር ኹኖ 5 ዓመት ይተርፋል፡፡

7510 ን ዘመን በቀመረ ዐረብም ቢቀምሩ 228፤ 228 የተፈጸመለት 32 ቀመረ ዐረብ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 11 ንዑስ ቀመር ኹኖ 5 ዓመት ይተርፋል፤ ስመ አቅማር ብዙ ነው አይቶ መተው ነው፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተጀመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ5ቱ አንዱን ቢያትቱ 4 ይተርፋል፤ 4 ዓመተ አበቅቴ ወጣ ገጠር ወንበር ይላል፤

 አበቅቴን ለማግኘት ከ4ቱ ዓመተ አበቅቴ 11፤ 44 ይኾናል፤ ፴ውን ቢገድፉት 14 ይተርፋል፤ 14 አበቅቴ ወጣ በዘመነ ማርቆስ፡፡ 

መጥቅዕንም ለማግኘት ከ4ቱ ዓመተ አበቅቴ 19 ዕለት ቢነሡ 76 ይኾናል፤ 30ውን በ2 ሱባኤ ቢገድፉት 16 ይቀራል፤ 16 መጥቅዕ ወጣ በዘመነ ማርቆስ፤ 14ት አበቅቴ እና 16 መጥቅዕ ፴ ይኾናሉ እንጂ ከ፴ አይወጡም ከ፴ አይወርዱም፤ “ዓዲ መጥቅዕ ወአበቅቴ ክልኤሆሙ እመ ይበዝኁ ወእመ ይውኅዱ ኢየዐርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወባሕቱ ወትረ ይከውኑ ፴” እንዲል 

(ከዚኽ በኋላ አበቅቴ ከመጠነ ሠርቀ መዓልትና ከሚለው ዠምሮ…ኢየዐርግ ኢይወርድ ኹሉ እንደ ታሪኩ አስገባ) 

 ከዚኽም በዘመኑ የኾኑ አጽዋማትና በዓላትን ይናገሯል፤ 
መጥቅዕ 16 መጥቅዕ ቢበዛ በመስከረም ይውላልና መስከረም ሰኞ ይብታል፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 8፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 15፤ ማግሰኞ 16 በዐለ መጥቅዕ መስከረም 16 ማግሰኞ ይውላል፤ የማግሰኞ ተውሳክ 5፤ 16 ና 5= 21 መባጃ ሐመር ይገኛል፤ በመስከረም ሳኒታ ጥር ማግሰኞ ይብታል፤ ማግሰኞ እስከ ማግሰኞ 8፤ ማግሰኞ እስከ ማግሰኞ 15፤ ማግሰኞ እስከ እሑድ 21 ጥር 21 ነነዌ ይውላል፡፡

 የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ 14 ና 21=35፤ ፴ውን ገድፎ 5 ይቀራል፤ የካቲት ኀሙስ ይብታል፤ ኀሙስ 1፤ ዐርብ 2፤ ቅዳሜ 3፤ እሑድ 4፤ ሰኞ 5 የካቲት 5 ቀን ዐቢይ ጾም፡፡


 የደብረ ዘይት ተውሳክ 11፤ 11 ና 21=32፤ ፴ውን ገድፎ 2 ይቀራል፤ መጋቢት ቀዳሚት ይብታል፤ ቅዳሜ 1፤ እሑድ 2 መጋቢት 2 ቀን ደብረ ዘይት

 የሆሳእና ተውሳክ 2፤ 2ና 21=23፤ ቅዳሜ እስከ ቅዳሜ 8 ቅዳሜ 15 ቅዳሜ እስከ ቅዳሜ 22 እሑድ 23 መጋቢት 23 ሆሳዕና 

 የስቅለት ተውሳክ 7፤ 7 ና 21=28፤ ቅዳሜ እስከ ቅዳሜ 8—–15———-22——29 አንዷን ታግሦ መጋቢት 28 ስቅለት፡፡

 የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ 9 ና 21= 30፤ ዐርብ 28 ቅዳሜ 29 እሑድ ፴ መጋቢት 30 ትንሣኤ

 የርክብ ተውሳክ 3፤ 3 ና 21=24፤ ሚያዝያ ሰኞ ይብታል ሰኞ እስከ ሰኞ 8 —-15 ——22 ማግሰኞ 23 ረቡዕ 24 ሚያዝያ 24 ርክበ ካህናት

 የዕርገት ተውሳክ 18፤ 18ና 21=39፤ ፴ውን ገድፎ 9 ይቀራል፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 8፤ ኀሙስ 9 ግንቦት 9 ዕርገት

 የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28፤ 28 ና 21=49፤ ፴ውን ገድፎ 19 ይቀራል፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 8፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 15፤ ኀሙስ 16፤ ዐርብ 17፤ ቅዳሜ 18፤ እሑድ 19፤ ግንቦት 19 በዓለ ጰራቅሊጦስ፡፡

 የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 29፤ 29 ና 21=50፤ ፴ውን ገድፎ 20 ይቀራል፤ …. ግንቦት 19 እሑድ ግንቦት 20 ሰኞ ግንቦት 20 ጾመ ሐዋርያት፡፡ 

 የምሕላ ድኅነት ተውሳክ 1፤ 1 ና 21= 22፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 8፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 15፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 22፤ ግንቦት 22 ምሕላ ድኅነት ይውላል፡፡

 ዓመተ ወንጌላዊን ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዓመተ ወንጌላዊ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ለእመ ተርፈ አሐዱ ማቴዎስ ወክልኤቱ ማርቆስ ወሠለስቱ ሉቃስ ወለእመ ዐረየ ክፍል ዮሐንስ እንዲል፤ ዓመተ ወንጌላዊን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ አንድ ቢተርፍ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ መኾኑ፤ ኹለት ቢተርፍ ማርቆስ፤ ሦስት ቢተርፍ ሉቃስ ቢተካከል መኾኑን በዚኽ ይታወቃል፤ 7510 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1877 ደርሷቸው 2 ይተርፋል፤ 2 ቢተርፍ ማርቆስ ያለው ይኽ ነው፤ ዛሬ ወንጌላዊዉ ማርቆስ መኾኑ በዚኽ ታውቋል፡፡

ጥንተ ዮንንም ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ጥንተ ዮን ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት ወትገድፎ በበሱባኤ ወዘተርፈከ እምሱባኤ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ ወእምዝ ይከውን ጥንተ ዮን እንዲል፤ ጥንተ ዮንንም ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ 5ኛ መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን አትቶ 1 ቢተርፍ ጥንተ ዮን ረቡዕ መኾኑን መስከረም ረቡዕ መባቱን፤ 2ት ቢተርፍ ኀሙስ፤ 3 ቢተርፍ ዐርብ፤ 4 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 5 ቢተርፍ እሑድ፤ 6 ቢተርፍ ሰኞ፤ 7 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፡፡ አከፋፈል እንዳለፈው፤ ይታወቃል፤ 7510 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1877 ደርሷቸው 2 ይተርፋል፤ ይኽን በሱባዔ ይገድፏል፤ ከሺው 300 ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ ከ800ው አንዱን መቶ ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ 400 ይተርል፤ ከ100ው 2፤ ከ400ው 8፤ ከ8ቱ አንድ፤ ከዚያም 1 እና 77= 78 ይኾናል፤ ከ78ኙ 77ቱን በ11 ሱባዔ ቢገድፉ 1 ይተርፋል፡፡

ከአንዱ ወንጌላዊ 1 ከ4ቱ ወንጌላውያን 4፤ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜን 1877 ዕለት ትኾናለች፤ ርሷ በዕለት፤ ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና ግድፈት እንዳለፈው፤ መጠነ ራብዒት 5፤ ከዓመተ ወንጌላዊ የተረፈ 2 = 7 ይኾናል፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተዠመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ7ቱ አንዱን ቢያትቱ 6 ይተርፋል፤ 6 ቢተርፍ ሰኞ ያለው ይኽ ነው፤ የሰኞ ጥንተ ዮን 6 ነውና፡፡ ጥንተ ዮንም ማለት ጥንተ ፀሓይ፤ ጥንተ ጨረቃ፤ ጥንተ ከዋክብት ማለት ነው፤ ጥንተ ዮን ብሂል ጥንተ ተፈጥሮቶሙ ለፀሓይ፤ ወወርኅ ወከዋክብት እንዲል፡፡

 ዕለተ ቀመርንም ለማወቅ ለጥንተ ዮን ከወጣው አንዱን ሳያትቱ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 3 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 4 ቢተርፍ ዐርብ፤ 5 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 6 ቢተርፍ እሑድ፤ 7 ቢተርፍ ሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፤ ለጥንተ ዮን የወጣው 7 ነው፤ 7 ቢተርፍ ሰኞ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ቀመርም ማለት ቀመር የተዠመረበት ዕለት ማለት ነው፤ ቀመር የተዠመረው ማግሰኞ ነውና፡፡

ዕለተ ዮሐንስንም ከዚኽ ይናገሩታል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዕለተ ዮሐንስ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ፤ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት፤ ወክልዔተ ዕለተ ጠቢባን ወትገድፎ በበሱባዔ ወዘተርፈከ እምሱባዔ ኢተአትት አሐደ ዓመተ፤ ወእምዝ ይከውን ዕለተ ዮሐንስ እንዲል ዕለተ ዮሐንስን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ፤ 5ኛ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ 7ኛ 2ት ዕለተ ጠቢባንን ጨምሮ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን ሳያትቱ አንድ ቢተርፍ ዕለተ ዮሐንስ እሑድ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት መኾኑ በዚኽ ይታወቃል ለጥንተ ዮን የወጣ 7 እና 2 ዕለተ ጠቢባን= 9 ሱባዔውን ቢገድፉ 2 ይተርፋል፤ 2 ቢተርፍ እሑድ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ዮሐንስም ማለት አሻቅቦ ወደ ላይ እስከ ፍጥረተ ዓለም፤ አቈልቊሎ ወደ ታች እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ቢቈጥሩ ለወንጌላዊዉ ዮሐንስ የሚደርሰው ቀን ማለት ነው፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘኀለፈ ይመርሐከ ዝንቱ እስከ ፍጥረተ ዓለም ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘይመጽእ ያበጽሐከ ዝንቱ እስከ ምጽአተ ክርስቶስ እንዲል፤ አንድም ሠርቀ ቲቶን ዕለተ ዮሐንስ ይለዋል፤ ቲቶ የተባለው መስከረም ነው፤ የመጥምቁ ዮሐንስ በዓል የሚውልበት ቀን ማለት ነው፤ ርዕሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ እንዲል፡፡

✔ዕለተ በዓል ዘኀለፈ ዕለተ በዓል ዘይመጽእ የእሑድ አሚሩ ሰንበተ ክርስቲያንን ለማወቅ በዘመኑ የወጣውን ጥንተ ዮን፤ ሠርቀ መዓልት፤ 2 ዕለተ ጠቢባን በየወሩ የሚገኘውን አጽፈ ወርኅ እሊኽን 4ቱን አንድ አድርጎ ቈጥሮ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ እሑድ አሚሩ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ ሰኑዩ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ ሠሉሱ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ ረቡዑ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ ኀሙሱ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ ሰዱሱ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት ሰቡዑ፤ 8 ቢተርፍ በሱባዔ ገድፎ እሑድ አሚሩ የሚያሰኘው ይኽ ነው፡፡ 

አጽፈ ወርኅም ማለት የወርኁ ከወርኅ የሚደረብ ማለት ነው፤ ይኽስ ከምን ይገኛል ቢሉ? ወሩን በሱባዔ ቢገድፉ 4 ሱባዔ ኾኖ 2 ይተርፋል፤ የወርኁ 2 የዓመቱ 24፤ እንዲኽ ግን ስለኾነ ለመስከረም አጽፈ ወርኅ የለውም በጥንተ ዮን፤ በሠርቀ መዐልት በኹለት ዕለተ ጠቢባን ይቈጠራል፤ በእሊኽ በ3ቱ ይቈጠራል፤ ጥንተ ዮን 6፤ ሠርቀ መዐልት 1=7፤ ኹለት ዕለተ ጠቢባን 9 ይኾናል፤ በሱባኤ ሲገድፉ 2 ይተርፋል፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ ሰኑዩ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ጠቢባንም ማለት ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም የፈጠሩበት፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን የሚያመሰግኑበት ቀን ማለት ነው፤ (ዬ) ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም ከእሑድ እስከ ዐርብ ፈጥረዋል፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን ዘወትር ያመሰግናሉ ብሎ የቊጥር መጽሐፍን የተማሩ መምህራን ዕለተ ሰንበትን፤ 6ቱ ዕለታትን፤ ያለፉትን የሚመጡትን በዓላት የሚያውቁባቸው የሚያሳውቁባቸው ማለት ነው፤ ዕለተ ጠቢባንም የተባሉ እሑድና ሰኞ ናቸው፤ ከቀመር ገብተው አልተቈጠሩም፡፡

✔ዕለተ ምርያ አዕዋዲትንም ለማወቅ የፀሓይ ዐውደ ዓመት 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ነው፤ ይኽነን በሱባዔ ቢገድፉት 52 ሱባዔ ኾኖ 1 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይተርፋል፤ ይኽቺውም አንድ ዕለት የተባለችው ዐምስተኛዪቱ ጳጒሜን ናት፤ ዕለተ ምርያ አዕዋዲት ይላታል፤ ዕለተ ምርያ ማለት ዕለተ መድኀኒት ማለት ነው፤ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን የምታሳውቅ ማለት ነው፤ ርሷ በዋለች ልደት ይውላልና፤ አዕዋዲትም አላት ዘመኑን የምታዘዋውር የምታለዋውጥ ማለት ነው፤ እሑድ የዋለውን ሰኞ፤ ሰኞ የዋለውን ማግሰኞ እንዲውል የምታደርግ ርሷ ናትና፡፡

✔መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንም ለማወቅ የአንዱ ዓመት ኬክሮስ 15፤ የ2 ዓመቱ 30፤ የ4 ዓመቱ 60 ኬክሮስ ነው፤ 60ው ኬክሮስ 1 ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም በሉቃስ መጨረሻ ዮሐንስን ተጠግታ የምትውል ስድስተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ መጠነ ራብዒት፣ ሠግረ ዮሐንስ ይላታል፤ መጠነ ራብዒት አላት ርሷ በዕለት ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና፤ ሠግረ ዮሐንስም አላት ዮሐንስ ተራምዶ የሚውልባት ስለኾነ፡፡

✔ ዕሪና መዓልትና ዕሪና ሌሊትንም (7ተኛዪቱ ጳጉሜን) ለማወቅ የአንዱ ዓመት ካልዒት 6፤ የ5ቱ ዓመት 30፤ የ10ሩ ዓመት 60 ይኾናል፤ 60ው ካልዒት 1 ኬክሮስ ይኾናል፤ የ100ው ዓመት 10 ኬክሮስ፤ የ600 ዓመት 60 ኬክሮስ፤ 60ው ኬክሮስ አንድ ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም ሰባተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ ዓለም በተፈጠረ በ600 ዘመን ዕሪና መዓልት ዕሪና ሌሊት ኾኗል፤ ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 12 ዕሪና መዓልት 12 ዕሪና ሌሊት ኾኖ 13ኛው ከተዠመረ 310 ኾኖ በዘመነ ማርቆስ ይኸውም ሊመላ 290 ይቀራል፡፡

ከዚኽ በኋላ እንዲኽ ብሎ ባሕረ ሐሳብ አውጪው አሥርቆት ያውጣ፡፡
በዘንዜከር ሐሳባተ ሕጉ ወትእዛዙ ለእግዚእነ ወአምላክነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ሉቃስ ዜናዊ፤ ወንጌላዊ አለው ማርቆስን ባለዘመን ነውና፤ ዜናዊ አለው ሉቃስን የሚመጣ ነውና ወረኛ ንጉሥ እንዲሉ፡፡ በሰብዐ ወኀምስቱ ምእት ወዐሡሩ ዓመተ ዓለም፡፡ በኀምሳ ወኀምስቱ ምዕት ዓመተ ኩነኔ፤ በዕሥራ ምዕት ወዐሡሩ ዓመተ ምሕረት፤ ሠረቀ ለነ ወርኀ መስከረም ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ወርኀ ጥቅምት በሰላመ እግዚአብሔር አሜን፤ አበቅቴ 14 ሠርቀ መዓልት 1፤ ሕጸጽ 1= 16 ዐሡሩ ወሰዱሱ ሠርቀ ሌሊት፤ ዕሥራ ሠርቀ ወርኅ፤ አሚሩ ሠርቀ መዓልት፤ ሰኑዩ ሠርቀ ዕለት፤ ዮም በዛቲ ዕለት ዘአቅረብነ ለከ አምኀ ስብሐት ያዐርጉ ለነ መላእክት ተወከፍ ለነ እግዚአ ስብሐት፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
ከዚኽ ቀጥሎ ካህኑ ኑዛዜ ሰጥተው ዘመነ ማቴዎስ ዐለፈ ዘመነ ማርቆስ ተተካ ብለው በጭብጨባ በእልልታ በዓሉ ይታወጃል 
አዘጋጅ፡- መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ