Hot-Potato !(New Year In Atlanta)-From Tewodros Tadesse

0
1877

የኢትዮጵያ አዲስ አመት አከባበር በአትላንታ part 1

Posted by Wesen Photoatlanta on Tuesday, September 12, 2017

(ከቴዎድሮስ ታደሰ)
//////////////////// ትኩስ-ድንች ///////////////////
(የአትላንታውን አዲስ ዓመት አከባበር በተመለከተ)
(Photo Credit for Addis Mengesha )
2010 ን እንዴት አያችሁት ጎበዝ?! ገና ከጅምሩ “አክብሩኝ” የሚል ዓይነት “ጉልቤ” ይመስላል ዓይደል?! ሳንወድ በግድ ሶፋችን ላይ ሰፍቶን ቀረ ‘ኮ!!! በአንድ እጃችን ሪሞት በሌላኛው እጃችን ደሞ ሄኒከን ጨብጠን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። CNN ፣ ABC ፣ NBC… ወዘተረፈ የዜና አውታሮች “ንፋሱ ሊጠርግህ…ጎርፍ ሊሰለቅጥህ ነው ዋ!!! ” እያሉ የቤት ውስጥ እስረኛ ካረጉን ሰዓታቶች ተቆጠሩም አይደል?! ደግነቱ ‘ማር እስከ ጧፍ’ የቪዲዮ ክሊፕ ተለቋል። ስንቴ አየሁት መሰላችሁ። ቴዲ “አምላኬ ሰው በልኬ” ሲል ለአምላኩ ያቀረበው ተማፅኖ እንደያዘለት ያወኩት ዛሬ ነው። እውነትም ፈጣሪው ‘ግራ-ጎኑን’ በልኩ ሰጥቶታል። አመለሰት በቴዲ ልክ የተሰራች ድንቅ የጥበብ ሰው ናት…ዳሬክት ማድረግ ትችላለች።(ፍቅር እስከመቃብርን ያነበበ ሰው አመለሰት ዳሬክት ያደረገችውን ‘ማር እስከ ጧፍ’ የዘፈን ክሊፕ ከማድነቅ ውጭ ሌላ ምርጫ የለውም)
ወደ አትላንታችን እንመለስ። ትላንት እንዴት ነበር ?! የኮሚኒቲያችን የዓዲስ ዓመት በዓል ማለቴ ነው።) አሪፍ ነበር አይደል?! ድፍን አትላንታ ነቅሎ የወጣ ነው የሚመስለው። ፀዳ ያለ ዝግጅት ነበር ። በርግጥ ፀዴነቱ (አሪፍነቱ) እንደየእድሜና አመለካከታችን ይለያያል። አዛውንቶች ቢጠየቁ …በሕፃናቶች ቡረቃ ፣ በታዳሚው ብዛትና ባሕላዊ አለባበስ ተመስጠው “እፁብ-ድንቅ” ሊሉ ይችሉ ይሆናል። ጎልማሳው ቢጠየቅ “የዛችኛዋን ጠጅ … የዚችኛዋን ጠላ… የከሌን ጥብስ … የማንትስን ቁርጥ” ጠቅሶ በዓል ብሎ ዝም ሊል ይችላል። ጎረምሶቹን ሰብስበን እንዴት ነበር ብንል ደሞ “በጠበሳና ጠቀሳ ቢዚ ነበር” ሊሉን ይችሉ ይሆናል። በትላልቅ ድገሶች ውስጥ ትናንሽ ሰርጎች ይፀነሳሉና …ስንት ሎሚ (ወይም በፈረንጅኛ ስንት አይፎን) ኮረዶች ደረት ላይ እንደተወረወረ የምናውቀው ከ 6 ወር በኃላ በከተማችን በሚጣሉ የሰርግ ዳሶች መጠን ይሆናል 
 ሁሉም የሚስማሙበት አንድ ሀቅ ግን አለ። እለቱ ግሎባል ዋርሚንግን ያስረሳ ግሩም ቀን ሆኖ መዋሉ። አየሩ እኮ በቃ በማንኪያ እየቆረሱ የሚውጡት ዓይነት እርጎ ነበር። ዶናልድ ትራንፕ “ግሎባል ዋርሚንግ የሚባል ነገር የለም” ያሉት እውነት ይሆን እንዴ እስከማለት ሁሉ ደርሻለሁ

😉

አሁንም ወደ ስታዲየሙ እንመለስና በአንዳንድ ጉዳዮች ዙርያ እንጨዋወት። ከወዳጆቼ ዮናስ እና ተክሌ ጋር በመሆን ፕሮግራሙን የመምራት አጋጣሚው ስለነበረኝ መድረኩ አካባቢ ሆኜ ነገሮችን በቅርበት ተከታትያለሁ። በዚሁም መሰረት ለዛሬው ቢያንስ በሁለት ጉዳዮች ዙርያ እንመክራለን። አንዱ ገብስ ነው። አይጎረብጥም። ሌላኛው ግን ትኩስ ድንች ነው። ማንም እጁ ላይ እንዲቆይ አይፈቅድም። ይፋጃል። 
(ገብስ ገብሱን እናስቀድም) … የተለያዩ ሐይማኖቶችን ወክለው በመጡ አባቶች አካባቢ ባስተዋልኩት ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ዙርያ ይሆናል። ይህንን የኢትዮጵያውያን ስብስብ ለመባረክና ለመቀደስ እንደወትሮው ሁሉ የኦርቶዶክስ ፣ የሙስሊምና የፕሮቴስታንት አባቶች ሰዓታቸውን አክብረው በጊዜ ተገኝተው ነበር። ሁል ግዜ የማስተውለው አሪፍ ነገር ቢኖር … በሙስሊሙ ፣ በኦርቶዶክሱና በፕሮቴስታንቱ አባቶች ዙርያ የሚታየው መቻቻል እና መከባበር ነው። ፍቅርን መስበክ ቀላል ነው። የፍቅር ሰው ሆኖ መገኘት ግን ከባድ ነው። ከቃል ተግባር ይልቃልና… እነኚህ በተለያዩ መሰረታዊ በሆኑ ሐይማኖታዊ አስተምሮቶች እንዲሁም አስተዳደራዊ መዋቅሮች (የሐገር ቤትና የውጭ ሲኖዶሶች) ዙርያ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ የሐይማኖት አባቶች በአንድ መድረክ ላይ በሚሰየሙበት አጋጣሚ አንዱ ለሌላኛው የሚያሳየው አክብሮትና መቻቻል ሁሌም ያስደምመኛል። ይህ እራሱን የቻለ ስብከት ነው። የማያይ የማያስተውል ይመስላል እንጂ በሺዎች የሚቆጠረው ታዳሚ የእያንዳንዱን አባት ገፅታና ቃላት ይመረምራል። ያስተውላል። እናም እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ አባቶች ፍቅርን በተግባር ከሚሰብኩባቸው እድሎች አንዱ ነው። በመሆኑም እለቱን አክብረው ያንን ታላቅ ስብስብ ለመባረክ የታደሙ ጳጳሳት፣ ካህናት ፣ ሐጂዎችና ፓስተሮች ሊመሰገኑ ይገባል። በተለይ ደሞ የመጋቢ አዲስን ጥበብ ፣ አስተዋይነትና ትህትና አዚህ ላይ መጥቀስ የግድ ይላል ።
“አይደፈሬ” ወደሆነው ሁለተኛው “ትኩስ-ድንች” እናምራ…
(ይቀጥላል)