How do we recover from shoulder and back pain?

0
367

በአብዛኛው ከአቀማመጥ ጋር በተያያዘ የትከሻ እና ጀርባ ህመም በተደጋጋሚ ሲከሰት ይስተዋላል።

የትከሻ ህመም ደግሞ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥም የሚያጋጥም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለመደ አይነት ችግር ነው።

በአብዛኛው ኮምፒውተር ላይ እና መሰል መገልገያዎች ላይ የሚጽፉ ከሆነ ከዚህ ችግር ጋር ተያይዞ ለሚፈጠር ችግር ተጠቂ የመሆን አጋጣሚው ሊፈጠር ይችላል።

በትከሻ እና ሰውነት መገጣጠሚያዎች ላይ ህመም የሚያስከትለው ይህ ችግር ግን በቀላሉ ሊድን የሚችል ነው።

በዚህ ህመም ሲያዙ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አለመቻል፣ ትከሻ አካባቢ ረዘም ላለ ጊዜ የሚሰማ ህመም እና ያዝ የማድረግ ስሜት ይሰማል።

ይህን ህመም ለማከም ደግሞ በቀላሉ ቤት ውስጥ ማከምና ስሜቱን ማስወገድ ይቻላል።

በበረዶ ማከም፦ ህመሙ የሚሰማበት አካባቢ በፌስታል አልያም በስስ ጨርቅ የተጠቀለለ በረዶን ማኖርና ጫን አድርጎ መያዝ።

ይህን ሲያደርጉ ህመሙ የተከሰተበት ቦታ ላይ ያለውን የማቃጠልና የህመም ስሜት ለመቀነስ እንዲሁም በዚህ ወቅት የጡንቻ ህመም የሚያባብሰውን የላክቲክ አሲድ መጠንን ለመቀነስ ያግዛል።

ይህን ፈውስ ለማግኘት ታዲያ የተጠቀለለውን በረዶ ህመሙ በተከሰተበት ቦታ ላይ በማድረግ ዙሪያውን በስሱ ማሸትና እስከ 15 ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ በቦታው ላይ ማቆየት።

ይህንንም በየሁለት ሰዓት ልዩነቱ ለ48 ሰዓት ያክል ማድረግ፤ ግን በረዶውን ቀጥታ የሰውነት ቆዳ ላይ ማድረጉ ጉዳት ስለሚያስከትል በረዶው ለሰውነት የሚበቃውን ያክል ቅዝቃዜ ሊሰጥ በሚችል መያዣ መጠቅለል ይኖርበታል።

በሞቀ ውሃ የሚደረግ ህክምና፦ ውሃ መያዣ ጠንካራ የቆዳ እቃ አልያም የሞቀውን ውሃ መያዝ በሚችል እቃ በማድረግ ህመሙ ባለበት ቦታ ላይ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ በማድረግ በየቀኑ እስከሚሻለዎት መደጋገም።

ከዚህ ባለፈም በጣም ባልሞቀ ውሃ ገላን መታጠብ በተለይም የተጎዳውን የሰውነት ክፍል ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ሞቅ ባለው ውሃ በማስመታት እዚያው እንዳሉ ቀስ እያሉ ሰውነትዎን ማፍታት ይህን እስከሚሻለዎት መደጋገም።

ይህን የሚያደርጉት በበረዶ የሞከሩት ህክምና በሁለት ቀናት ውስጥ ለውጥ ካላሳየ ነው።

ሙቀቱ በተጎዳው የሰውነት ክፍል አካባቢ የደም ዝውውርን በመጨመር ያዝ የሚያደርገውንና የህመሙን ስሜት ለመቀነስ ይረዳል።

የተጎዳውን የሰውነት ክፍል መጫንና ማዝናናት፦ ትከሻዎ አካባቢ መጠቅለያ ባንዴጅ በመጠቀምና በመጠቅለል ለተወሰነ ቀን ማቆየት።

አልያም ሲተኙ ለስለስ ያሉ ትራሶችን በመጠቀም ከትከሻዎ ከፍ ብለው መተኛት፤ ይህ የተስተካከለ የደም ዝውውር እንዲኖር በማድረግ የተጎዳው ክፍል ቶሎ እንዲያገግም ይረዳዋል።

ግን በባንዴጅ ሲጠቅልሉት ጠበቅ ባለ መልኩ መሆን የለበትም ሸብ አድርጎ ማሰርና ስሜቱን መቀነስ በሚያስችል መልኩም ሊሆን ይገባል።

መታሸት፦ በባለሙያ የሚደረግ የሰውነት መታሸት (ማሳጅ) ከዚህ የህመም ስሜት ለመዳን የሚረዳ ሌላው መፍትሄ ነው።

ጡንቻን ማፍታታት፣ የደም ዝውውርን መጨመርና ዘና የማለት ስሜትን ለመፍጠር ይረዳል፤ ከዚህ ባለፈም እንዲተኙ በማድረግ ለመዳን የሚያደርጉትን ጥረት በእጅጉ ያግዛል።

ከመታሸትዎ በፊት ሞቅ ባለ ውሃ ገላዎን መታጠብ፤ የተሳሰረውን ሰውነትዎን ለማፍታት ስለሚረዳ።

በተጎዳው የሰውነት ክፍል ላይ መታሻ ቅባቶችን ማድረግና መታሸት፥ ከዚያም ሞቅ ባለ ውሃ የተነከረ ፎጣን በተጎዳው ክፍል ላይ ለግማሽ ሰዓት ያክል ማስቀመጥ።

እስከሚሻልዎት ድረስም ሰውነትን መታሸት መልካም ነው።

ማሳሳብ፦ ሰውነትን ቀስ እያሉ በማሳሳብም ከዚህ የህመም ስሜት መዳን እንደሚቻል ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ይህን ሲያደርጉ የሰውነት በተለይም የጡንቻ ክፍሎች መሳሳባቸውን በመጨመር የተስተካከለ መተጣጠፍ እንዲኖር ያግዛል።

ለዚህ ህመም ደግሞ ቀጥ ብለው በመቆምና እጆችን በጭንዎ ላይ በማሳረፍ ሁለቱንም ትከሻዎች ወደ ላይ በመሳብ ለአምስት ሰከንድ መቆየት።

ትከሻን ወደ ኋላ ሳብ ማድረግና ለአምስት ሰከንድ ያክል ማቆየትና ትከሻን ወደታች ሳብ በማድረግ ለተመሳሳይ ጊዜ ያክል መቆየት።

ይህን እንቀስቃሴም ለ10 ደቂቃዎች ያክል ደጋግሞ መስራትና እስከሚሻልዎት በቀን ለ3 ወይም ለ4 ጊዜ ያክል በድግግሞሽ መከዎን።

ትክሻን ማዛዟር፦ ይህን እንቅስቃሴ ተስተካክለው በመቀመጥ የሚሰሩት ሲሆን፥ የላይኛው የጀርባ ክፍል፣ አንገትዎ አካባቢ ያሉ ጡንቻዎች አካባቢና ትከሻዎ ላይ ያለውን የህመም ስሜት ለመቀነስ የሚረዳ ነው።

በመጀመሪያ ተስተካክለውና ቀጥ ብለው መቀመጥ ከዚያም ደረትዎን ወደ ፊት ገፋ ማድረግ፤ በዚያው ልክ ጀርባዎ ቀጥ ባለ አኳኋን መከተል ይኖርበታል።

ከዚያም ትከሻዎን እስከ ጆሮዎ በማስጠጋት ከፍ በማድረግ ቀስ እያሉ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ትከሻዎን ማዟዟር፤ ይህን እንቅስቃሴም ለአምስት ጊዜያት ያክል እረፍት እየወሰዱ በቀን ውስጥ መስራት።

በእንቅስቃሴዎች መሃል ግን እረፍት ማድረግና ጥቂት ሰውነትን ማዝናናትም ያስፈልጋል።

ከዚህ ባለፈም እጅን አጠላልፎ በደረት ትይዩ ማንቀሳቀስ፣ ቁጭ ብለው አልያም ቆመው አንገትን ማሳሳብ እንዲሁም በተቀመጡበት ቦታ ሆነው ቀስ እያሉ በሁለቱም አቅጣጫ

ሰውነት ማዛዟር መልካም መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ምንጭ:- ኤፍቢሲ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here