How familiar are you with the story of Dejazmach Belay Zeleke?

0
3106

በላይ ዘለቀ ከመኳንንትና ቤተ መንግስት አካባቢ ከኖሩ ሰዎች የተገኘ እንጅ በግብርና ስራ ከተሰማራ ቤተሰብ የወጣ ሰዉ አልነበረም፡፡ የበላይ ዘለቀ አያት ላቀዉ አጌ በአጼ ምኒሊክ መንግስት የቦረና ገዥ ነበሩ፡፡ የእርሳቸዉ ልጅ ባሻ ዘለቀ ላቀዉ ቤተ መንግስት ነዋሪና የልጅ ኢያሱ አንጋች ነበሩ፡፡
ወ/ሮ ጣይቱ አሰኔ የባሻ ዘለቀ ላቀዉ ባለቤትና የበላይ ዘለቀ እናት በወሎ ጫካታ የትልቅ ሰዉ ዘር እና ዘመደ ብዙ ሴት ነበሩ፡፡ ብዙ ወንድሞችም ነበሯቸዉ ፡፡አንደኛዉ ወንድማቸዉ ጎጃም በንጉስ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግስት ባለሟል ነበር፡፡ባሻ ዘለቀ ላቀዉ ፣ልጅ ኢያሱ ከስልጣን ሲወርዱ ህይወት ተመሰቃቅሎባቸዉ ከቤተ መንግስት በመዉጣት ወደ ሚስታቸዉ ሀገር ወሎ ፣ቦረና ሳይንት ጫካታ ሄደዉ ተቀመጡ፡፡
በላይ ዘለቀ እና እጅጉ ዘለቀ የተወለዱት ጫካታ ፣ልዩ ስሙ ጎጣ በተባለ ሰፈር ነዉ፡፡በላይ ዘለቀ የተወለደዉ በ1904 ዓ/ም ነዉ፡፡ባሻ ዘለቀ ላቀዉ ትንሽ ዓመታት ጫካታ እንደቆዩ በድንገት በእለት ግጭት ሰዉ ስለገደሉ ልጆቻቸዉን በላይ ዘለቀንና እጅጉ ዘለቀን ይዘዉ በጠፍ ጨረቃ ጫካታን ለቀዉ ወደ ትዉልድ ሃገራቸዉ ጎጃም ፣ቢቸና፣በለምጨን ቀበሌ መኖር ጀመሩ፡፡
በ1916 ዓ/ም በራስ ሃይሉ ተክለሃይማኖት የጎጃም ገዥነት ጊዜ ሰዉ ገድለዉ ከወሎ መምጣታቸዉ ተሰምቶ እጃቸዉን እንዲሰጡ ቢጠየቁ አልሰጥም ብለዉ ተዋግተዉ በመጨረሻም ሬሳቸዉ በመኖሪያ ቤታቸዉ አካባቢ ተሰቀለ፡፡በላይ ዘለቀ በሽፍትነት ያሳለፋቸዉ ዘመናት ከ1921 እስከ 1928 ዓ/ም ነበር፡፡በዚህ የሽፍትነት ኑሮ በላይ ብዙ ነገሮችን ተማረ፡፡ስለተኩስ፣አብሮ ስለመኖር፣ስለአስተዳደር ተማረ፡፡በላይ ጥንቁቅ፣ትጉህ፣ብልህ፣አልሞ ተኳሽ፣ጾመኛ፣እና ጸሎተኛ ስለነበር ሁሉም የልጅ አዋቂ ይሉት ነበር፡፡በዚሁ የበላይ ሽፍትነት ዘመን አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ንጉሰ ነገስት ተብለዉ ቅብአ ንግስ ተቀብተዉ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ/ም ዘዉድ ጫኑ፡፡
የጎጃሙን ገዥ ራስ ሀይሉ ተ/ሓይማኖትን አዲስ አበባ አስረዉ በምትካቸዉ የሽዋዉን ራስ እምሩ ኃ/ስላሴን የጎጃም ገዥ አድርገዉ ሾሙ፡፡ሆኖም የጎጃም ህዝብ ራስ እምሩን አልተቀበላቸዉም ፡፡ጎጃም በራስ መስፍን እንጅ በሌላ ተገዝቶ አያዉቅም፡፡በላይ ዘለቀ በሽፍትነት ዘመኑ ስራዉና ጀግንነቱ እየጎላ መጣ፡፡ዝናዉ በሸበል፣በበረንታ፣በእነማይ፣በእናርጅ እናዉጋ፣በእነሴናእነብሴ፣በጎንቻ ሳር ምድር ሁሉ ተናኘ፡፡አጼ ኃይለ ስላሴ ጠላት ኢትዮጵያን ከደፈረ በኋላ በዱር በገደል ለሚገኙት ሽፍቶች ሁሉ የምህረት አዋጅ አስነግረዉ ስለነበረ በላይ የዚህ ተጠቃሚ በመሆን ከሽፍትነት ህይወቱ ወጣ፡፡
ህይወቱንም ለሃገሩ ነጻነት ለማዋጋት ወሰነ፡፡የበላይ ዘለቀ ማህተም “በላይ ዘለቀ መላእከ ብርሃን ገ/ጊዮርጊስ-የኢትዮጵያ ደመላሽ” የሚል ነበር፡፡ ጀግናዉ በላይ ዘለቀ ጥቂት ጓደኞቹን ይዞ የአርበኝነት ስራዉን በጎጃም ቢቸና አካባቢ ላይ ጀምሮ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በተከታታይ በጠላት ላይ በደረሰዉ ጥቃት ዝናን ክብርን፣ብዙ ተከታዮችን አፈራ፡፡እንደ አቶ እያሱ ገለጻ በላይ ሁልጊዜም በዉይይት የሚያምን ፣በአንድ ጉዳይ ላይ ተከራክሮ የሚወስን፣ጓዶቹ የሚሉትን የሚያዳምጥ፣ዉሳኔዉም ሁል ጊዜ አጭርና ቀልጣፋ ነበር፡፡በመሆኑም ድሉ እየበዛ ፣ምርኮዉ እየተበራከተ ሲሄድ በበላይ ጫንቃ ላይ ያረፈዉ ኃላፊነት ጥልቀትና ብስለት እያገኘ መጣ፡፡ጦሩን ለማስተዳደርና ለመምራት ሁል ጊዜም አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ ማግኘት ፣በአርበኝነት ይዞታ ስር በሚገኙት ሀገሮች ላይ ግብር በስርዓት የሚከፈልበትንና የሚሰበሰብበትን ስርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ፣ያልተቋረጠ የጦር ስልጠና ለአዳዲስ ተመልማዮች ማድረግና ተተኪ ተዋጊዎችን ማዘጋጀት፣የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችንና ሌሎች ንብረቶች በስርዓት የሚይዙበትንና ጥቅም ላይ የሚዉሉበትን ዘዴ ቀይሶ ተግባራዊ ማድረግ፣በታቀደ ሁኔታ ተከታታይነት ያለዉ ጦርነቶችን ማካሄድ እና በየጦር ሜዳዉ ከፍተኛ ጀብዱ ለፈጸሙ አርበኞች የማነቃቂያ የማዕረግ ሹመትና ሽልማት መስጠት፣ስለጠላት እንቅስቃሴ የተጠናከረና የጠራ መረጃ ዘርግቶተጠቃሚ መሆን፣ለነበረዉ ከፍተኛ ጦር ስንቅና ትጥቅ በወቅቱ ማቅረብ የበላይ ዘለቀ ሁነኛ የጦር ጊዜ ተግባራት ነበሩ፡፡
አቶ እያሱ/2004/ ሳምሶን ማሞ/ቀ.የ/ን ዋቢ አድርገዉ በላይ ዘለቀ ብልህ፣ፈጣን፣አድማጭ፣ቆራጥ፣የአመራር ሰዉ ነበር፡፡የጦር ስልቱም በአብዛኛዉ ጊዜ በደፈጣ ዉጊያ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በጠላት ላይ ቅጽበታዊ እርምጃ በመዉሰድና በራሱ ወገን ላይ የሚደርሰዉን ጉዳት በመቀነስ የታወቀ ነበር፡፡ጀግናዉ በላይ ዘለቀ በአምስቱ የጠላት ወረራ ዘመን ከሰላሳ ስድስት በላይ ጦርነቶችን አከናዉኖ ከዘጠና ስምንት በመቶ በላይ የሆኑ ጦርነቶችን በድል መወጣቱና ይህም በአማካይ በየዓመቱ ከስድስት ጦርነቶች በላይ መምራቱን አስረድተዉ “በላይ ዘለቀ በርካታ ጦርነቶች ላይ የተዋጋ ብርቅ ድንቅ ፣አመራር በሌለበት ጊዜ ብቅ ያለ የኢትዮጵያ ኩራት የኢትዮጵያ ደመላሽ ልጅ ነበር ” ሲሉ አሞካሽተዉታል፡፡በላይ በዚህ ሁሉ ጦርነት ዉስጥ የሰከነ አስተዳደር የሚያከናዉን በእጅጉ የሰላ አእምሮ የነበረዉ ስልጡን ሰዉ ነበር፡፡
ብዙዉን ጊዜ ከበላይ ጋር የሚንቀሳቀሱት መትረየስ ተኳሾችና የጋሜ ጦር አባላት ናቸዉ፡፡የመትረየስ ተኳሾች መሪ አያሌዉ መሸሻ ሲሆን የጋሜ ጦር ደግሞ የሚመራዉ በሽፈራዉ ገርባዉ/የበላይ ዘለቀ አክስት የአያህሉሽ ላቀዉ ልጅ / ነዉ፡፡የበላይ ዘለቀ ሰራዊት እጅግ ብዙና በጥብቅ ስነ-ስርዓት የሚመራ ነበር፡፡በበላይ ዘለቀ አመራር አርበኞች የሚመዘኑት በፈጸሟቸዉ ጀብዱዎች ብቻ ነበር፡፡እንደየስራቸዉ የማዕረግ ስም በመስጠት በየጊዜዉ ይሾማቸዉ፣ይሸልማቸዉ ነበር፡፡ይህም በጦር ዉስጥ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ለራሱ የሰጠዉ ሹመት ግን አልነበረም፡፡ሚያዚያ 13/1933 ዓ/ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ እስከ ሁለት ሺህ ከሚጠጋ ጦር አጃቢዎቻቸዉ ጋር በደብረ ማርቆስ ከተማ የአርበኞችን የሰልፍ ትርኢት ተመልክተዉ ነበር፡፡በነጋታዉ ሚያዚያ 14/1933 ዓ/ም አጼ ኃይለ ስላሴ በንጉስ ተክለሃይማኖት ቤተመንግስት ሆነዉ አስጠሩት፡፡በላይ የቁርጥ ቀን ወንድሞቹን አስከትሎ ወደ ቤተ መንግስቱ አመራ፡፡
አጼ ኃይለስላሴ በላይን በአክብሮት ተቀበሉት፡፡ባሳየዉ ድንቅ የሰራዊት ሰልፍ ትርኢትም መርካታቸዉን እና ጣልያኖችን በግንባር ገጥሞ እስከ መጨረሻ ባለመፋለሙ ቅሬታቸዉን ገለጹለት፡፡ከሰፊ ዉይይት በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ አዘዉታል፡፡አዲስ አበባ ከሄደ በኋላ ከሱ ያነሰ ተጋድሎ የነበራቸዉ ልጅ ኃይሉ በለዉ ራስ ተብለዉ የጎጃም ገዥ፣መንገሻ ጀንበሬ ቢትወደድ ተብለዉ የጎጃም ጠቅላላ ግዛት እንደራሴ ሆነዉ በመጋቢት ወር 1934 ሲሾሙ በላይ ተዘለለ፡፡በመጨረሻ በማዕረግም በግዛትም ከመንገሻ ጀንበሬና ከኃይሉ በለዉ አሳንሰዉ በሃምሌ ወር 1934 ዓ/ም ንጉሰ ነገስቱ በላይ ዘለቀን ደጃዝማች ብለዉ የቢቸና ገዥ አድርገዉ ሾሙት፡፡
በዚህ ምክንያት ስሜቱ ተቀዛቀዘ፡፡ያም ሆኖ በላይ ዘለቀ ሹመት ተቀብሎ ጎጃም ሲገባ የደብረ ማርቆስ ህዝብና ከዚያም ወደ ቢቸና ሲገባ የቢቸና ህዝብ ለማመን የሚያስቸግር ድግስ ደግሶ ነበር የተቀበለዉ፡፡በላይ የቢቸና ገዥ ሆኖ ስራዉን ጀመረ፡፡ነገር ግን በላይ የሚሾማቸዉ ምስለኔዎች ኃይሉ በለዉ ይሽራሉ፣ኃይሉ በለዉ የሚልኳቸዉን ምስለኔዎችም በላይ አይቀበልም ነበር፡፡ሁሉም ይህንኑ የግል አመለካከቶች ለአገር ግዛት ሚኒስትር አዲስ አበባ ያሳዉቁ ነበርና በመካከላቸዉ የነበረዉን ችግር ለመፍታት የጎጃሙ ገዥ ራስ ኃይሉ በለዉ፣የጎጃም እንደራሴ ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬና የቢቸና ገዥ ደጃዝማች ነላይ ዘለቀ አዲስ አበባ እንዲመጡ አገር ግዛት አዘዘ፡፡
ራስ ኃይሉ በለዉና ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ አዲስ አበባ ሺኄዱ በላይ ዘለቀ ቀረ፡፡የጎጃም ሹማምንትና የሽዋ ሹማምንት ተመካክረዉ በመጨረሻ በላይ ዘለቀ ሸፍቷልና እጁን ይዛችሁ አምጡ የሚል የንጉሱን መልዕክት በአዉሮፕላን ተበተነ፡፡ስለሆነም በላይ ዘለቀ የእናት አባቱን ልጅ እጅጉ ዘለቀን፣አያሌዉ መሸሻን እና ሽፈራዉ ገርባዉን አስከትሎ ሶማ በረሃ ገባ፡፡
በላይ ከመንግስት ጦር፣/ከጎጃም፣ከጎንደርና ከወሎ በቅንጅት ከተዉጣጣዉ ጦር/ ጋር ለሶስት ወራት ያህል ሲዋጋ ቆይቶ በተደረገዉ ስምምነት መሰረት እጁን ለመንግሰት በሚያዚያ ወር 1936 ዓ/ም ሰጠ፡፡በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ አዲስ አበባ ተወሰዱና ታሰሩ፡፡በእስር ከቆዩ በኋላ በላይና እጅጉ ከእስር ቤት አምልጠዉ ወደ ጎጃም ሲያመሩ ተያዙ፡፡በላይና እጅጉ ታህሳስ 23/1973 ዓ/ም ልዩ ፍርድ ቤት ቀርበዉ የሞት ፍርድ ተፈረደባቸዉ፡፡ ዓርብ ጥር 4/1937 ዓ/ም በይግባኝ በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ዙፋን ችሎት አዳራሽ የሞት ፍርዱ በአጼ ኃይለ ስላሴ ፀደቀ ፡፡ቅዳሜ ጥር 5 ቀን /1937 ዓ/ም መርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ጀግናዉ በላይ ዘለቀና ጀግናዉ እጅጉ ዘለቀ ሁለቱ የነፃነት አርበኞች ተሰቀሉ፡፡ 
 ምንጭ፡-/ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ምስረታን ምክንያት በማድረግ ታህሳስ 2004 ዓ/ም ከተዘጋጀ ልዩ እትም የተወሰደ/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here