“አንቺ ሆዬንና ባቲን በአደጋ አጣኋቸው” ማሲንቆ ተጫዋችና ድምፃዊ ካሣሁን ባዬ/ Exclusive Interview With Artist Kassahun Baye

0
2196
 ካደገበት ጎንደር “ማክሰኝት” ከተባለ ገጠር ወደ ባህርዳር የሄደው ወደ ስፍራው የሚመላለሱ ሙዚቀኞች የማሲንቆ ችሎታውን ተመልክተው እረኝነት ጥጃ ከሚጠብቅበት ወደ ባህርዳር አስኮበለሉት፡፡ በባህርዳር የምሽት ክበቦች ማስንቆ ሲጫዎት በጊሽአባይ ባለስልጣኖች ተመልምሎ የጊሻባይ ኪነትን እንዲቀላቀል ሌላ እድል አገኘ:: በማሲንቆና በድምጻዊነት በኪነት ቡድኑ ውስጥ የአጭር ጊዜ  ቆይቶ  በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በምሽት ክበቦች ውስጥ ይሰራ ነበር - ከአንጋፋ ድምጻዊያን ጋር፡፡
ከድምጻዊት አበበች ደራራ፣ ከድምጻዊ ማርታ አሻጋሪ ጋር በምሽት ክበቦች ውስጥ ቆይትዋል፡፡ ከድምጻዊት አበበች ደራራ ጋር በጋራ የሙዚቃ አልበም ያሳተሙ ሲሆን የራሱን ሁለት ሙሉ ካሴት ለገበያ አብቅቷል፡፡ በማስንቆ ተጫዋችነት ወደ ኬንያ አምርቶ በምሽት ክበብ ውስጥ ሲሰራ የቆዬ ሲሆን ከአስራ አራት ዓመት የኬንያ ቆይታ በኋላ ካናዳ በመግባት የግሉን ስራ እየሰራ ነበር፡፡ ይሁንና ከልጅነት እስከ ዕውቀት መተዳደሪያው በሆነውና ወደፊትም በማሲንቆ ሞያ ለመስራት አቅዶ ነበር፡፡ ይሁንና ለአጭር ጊዜ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ፡፡ በፋብሪካ ውስጥ የተበላሸ መሳሪያ ሲገጣጥም ነበር በአጁ ላይ አደጋ የደረሰው፡፡  የባወዛ የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሙዚቃ ባለሞያው ጋር ቆይታ አድርጓል፡
የተፈጠረብህ አደጋ ምንድን ነው?
በስራ ላይ እያለሁ ነው፡፡ የተሰበረ ማሽን ስንጠግን ነው አደጋው የተፈጠረብኝ፡፡ በአደጋው የግራ እጄን ሶስት ጣቶቼን አጥቻለሁ(ተቆርጠዋል)፡፡ እነዚህ ጣቶቼም ለማስንቆ መሣሪያ ወሳኝ የነበሩ ናቸው፡፡ ባቲና አንቺ ሆዬ የምጫዎትባቸው ጣቶቼ ናቸው፡፡
አደጋው መቼ ነው የተፈጠረብህ?
ጃንዋሪ 15/2015ዓ.ም. ነው፡፡ ህክምናውን እየተከታተልኩ ነው፡፡ ምንም የጎደለብኝ ነገር የለም ነገር ግን ከአደኩበትና ከኖርኩበት ሞያ በመለየቴ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡
መተዳደሪያህ የማስንቆ ሞያ ነበር?
ካናዳ ከመጣሁ ወዲህ በርግጥ በሞያው ላይ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ዓላማዬ የነበረው ወደፊት ነገሮችን አስተካክዬ ሙሉ በሙሉ ወደ ሙዚቃው ለመመለስ ነበር፡፡ ቦታዎቼን አስተካክዬ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የራሴን ቤት ለመክፈት ነበር ዕቅዴ፤ ነገር ግን አልሆነም፡፡
የሙዚቃ መሣሪያ ከመጫዎት በተጨማሪ ድምፃዊም ነህ?
አዎ፡፡ ነገር ግን ከሙዚቃው የማይቀረው ነገር ደግሞ ድምጻዊነቱ ነው፡፡
በድምጻዊነት እቀጥላለሁ የተዘጋጀሁትም ለዚሁ ነው፡፡ አደጋው ከተፈጠረብኝ በኋላ በሳይኮሎጂስቶች የተሰጠኝ ምክር
“ሌላ የሙዚቃ መሣሪያ እንዴት ነው መጫዎት የምቻለው፤ በግራ እጄ ምንም ማድረግ አልችልም፤ በቀኝ እጄ ምንድን ነው ማድግ ያለብኝ” ብዬ ስጠይቃቸው
ያመጡት ሃሳብ
“ኪቦርድ መጫዎት” የሚል ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ኪቦርድ ገዝቼ እየተማርኩ ነው ያለሁት፡፡ ነገር ግን እንደዋና ሞያተኞች እሆን እንደሆነ አላውቅም:: ነገር ግን ዜማ ለማውጣት ልምምድ ለማድረግ እየተለማመድኩ ነው - ወደፊት እንዴት እንደሚመጣ አላውቅም፡፡
የተሰጠህ ህክምና ደረጃው እንዴት ይገለፃላ?
ህክምናው በርግጥ ብዙ ይቀረዋል፡፡ አውራጣቴ የለም ምክንያቱም ከአውራ ጣት ቀጥሎ ያሉ ጣት(ሌባ ጣት) አንስተው እንደ አውራ ጣት አስቀመጡት በራሳቸው ፈጠራ:: አደጋው ከተከሰተ በኋላ ያጣኋቸው ጣቶቼ ለመተከል እድል ነበራቸው:: ነገር ግን በአጋጣሚ በሰዓቱ የደረሱ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሁለቱን ጣቶቼን ብቻ ከጠረጴዛ ላይ አንስተው፤ አውራ ጣቴን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ሆስፒታል ካስገቡኝ በኋላ ዶክተሮቹ
“አይዞህ ጣቶችህን በሙሉ ታገኛቸዋለህ” አሉኝ ነገር ግን ጣቶቼ ከወደቁበት ተለቅመው ሲመጡ ሁለቱ ጣቶቼ ብቻ ነው የተገኙት፡፡ አንደኛው ከወደቀበት አንስተው አላመጡትም ነበር፡፡ ስህተቱ የእኔ አልነበረም፡፡
በኋላ አንድ ጓደኛዬ ተቆርጣ የቀረችውን ጣቴን ይዞልኝ መጣ:: እነሱ የሚፈልጉት ሃያ ደቂቃ ነበር፡፡ 45 ደቂቃ አልፎት ነበር ሴሉ ሞቷል ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ እያንዳንዱ ጣታችን የራሱ ሃይልና ስራ አለው ከዛም ሌባ ጣትዋን እንደ አውራጣት ሰሯት - ለአስር ሰዓት በቆዬ ቀዶ ጥገና፡፡
ጣቶቼ እንዳሉ ነበር የማስበው፡፡ በሶስተኛው ቀን ግን ዶክተሩ የተረፉትን እና ወደ ፊት በሌላ ቀዶ ጥገና ቀጣዩን ነገር እንደሚያደርጉ ገለጹልኝ፡፡ አሁንም በህክምና ላይ ነው ያለሁት::
ከኬንያ ወደ ካናዳ ከመጣህ ስንት ዓመት ሆነህ?
ከኬንያ ካናዳ ስመጣ ሶስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ቅድሚያ የሰጠኋቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ትንሽ ስራ እየሰራሁ ቋንቋ መማር ነበር እቅዴ፡፡
ከዛም ወደ አሜሪካና ካናዳ  ወደ ሌሎች ስቴቶች ማሲንቆዬን ይዤ እየተዟዟርኩ ለመስራት ነበር፡፡ ዋናው ህልሜ ካናዳ ውስጥ የምሽት ክበብ መክፈት ነበር፡፡
ኬንያ ስንት ዓመት ቆይተሃል?
አስራ አራት ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ ኬንያ ልቀመጥ እንጂ የምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች በማስንቆ ሞያ ስራ ተዘዋውሪያለሁ:: በርግጥ ወደ ኬንያ ከመሄዴ በፊት ወደ ጀርመን ልሄድ ነበር::
ነገር ግን ወደ ኬንያ ሄጄ በምሽት ክበብ ውስጥ ማስንቆ መጫወት ጀመርኩ፡፡
ናይሮቢ ውስጥ “አቢሲኒያ” የሚባል ባንድ ነበረን፡፡
በኋላም “ማዘር ላንድ” ብለን ሌላ ባንድ አቋቁመን ነበር፡፡ የሀበሻ ሬስቶራንት ውስጥ ለአስር ዓመታት ማስንቆ በመጫዎት ስራ ቆየሁ፡፡
ማስንቆ የፈለግ ስለነበር ሰርግ፣ ኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ ዩኤንኤቺሲአር ውስጥ አንዳንድ በዓላት ሲኖሩ እና ከሌሎች ድርጅቶት ጋር እንሰራ ነበር፡፡ በሰዓቱም ማንስቆ ተጫዎች ከእኔ ውጭ ናይሮቢ ውስጥ ማንም አልነበረም፡፡
ነገር ግን ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ፣ ዳሬሴላም ለስራ ተዘዋውሪያለሁ፡፡ ካየኋቸው የምስራቅ አፍሪካ አገሮች እንደ ዳሬሰላም የወደድኩት የለም፡፡
በኬንያ ቆይተህ የስራ ግብዣ የሚቀርብልህ በኢትዮጵያውያን ብቻ ነው?
አፍሪካ በሙዚቃ መሳሪያ ጨዋታ ባለሃብት ናት:: በርግጥ ለኢትጵያውያን የሙዚቃ ባለሞያዎች ያላቸው አቀባበል ልዩ ነው፡፡ ማስንቆን ደግሞ ይወዱታል፡፡ ነገር ግን ባንዱ በሚጋበዝ ወቅት የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ባህል እንጫወት ነበር፡፡
ወደ ካናዳ ስትመጣ መሲንቆህን ይዘህ ነበር የመጣኸው?
ካለሷማ እንዴት መኖር እችላለሁ፡፡ ይዣት ነው እንጂ ምዞር:: አሁንም አለች አጠገቤ፡፡ ለማን እንደምሰጠው አላውቅም - ነገር ግን ማስታዎሻ አስቀምጠዋለሁ፡፡
ወደ ኬንያ ከመምጣትህ በፊት ኢትዮጵያ ምን ነበር የምትሰራው?
አዲስ አበባ ውስጥ የምሽት ክበብ ውስጥ አስራ ነበር፡፡ ቀን እማራለሁ ማታ እሰራለሁ፡፡
አባሳደር አካባቢ የነበረ የምሽት ክበብ ውስጥ ከእነ ማርታ አሻጋሪ ጋር የባህል ምሽት ቤት ውስጥ እንሰራ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ወደ ምሽት ክበቡም የዜማና የሙዚቃ ደራሲዎች ይመጡ ነበር፡፡ ከሃያ ዓመት በፊትም ከአበበች ደራራ ጋር ሙዚቃ የሰራሁት በዚህ አጋጣሚ ነው፡፡ የዜማ ደራሲው አምሳሉ ዘገዬ አየኝ አነጋገረኝና ሙዚቃውን አስጠኑኝ ስራውን ጀመርን:: በዚያ ጊዜ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም የሙዚቃ ፍላጎቱ ስለነበረኝ
“ከአበበች ደራራ ጋር ትዘፍናለሁ” ሲሉኝ ብር ከፍዬ የምዘፍን ነበር የመሰለኝ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ሙሉ ካሴት ሰርተን 5መቶ ብር ሲከፈለኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
“የሰላሌ ውሃ”፣ “ውብ ዓለም”፣ “ብቻዬን”፣ “ደሜደሜ”ና ወፌላላ” የተባሉ ዘፈኖችን  በጋራ ተጫውተናል ከአበበች ደራራ ጋር፡፡ ተስፋዬ ለሜሳ ነበር ያቀናጀን በጣም ታዋቂ የሙዚቃ ባለሞያ ነበር፡፡
በግልህ ሙሉ የካሴት ስራ አለህ?
ሙሉ ካሴት ስራዎችን ሰርቼ ነበር- ሁለት ነገር ግን እንደምፈልገው አልመጣም፡፡ ሊዋጣልኝ አልቻለም፡፡
የቀለም ትምህርቱን ዘለከው?
በርግጥ ከጊሽአባይ ኪነት ወጥቼ አዲስ አበባ እንደመጣሁ እየሰራሁ ትምህርቴን መማር ጀምሬ ነበር አስማቲክስ የጤና ችግር ነበረብኝ እሱ ሲያበሳጨኝ ከስምንተኛ ክፍል ነው ያቋረጥኩት፡፡
የጊሽአባይ ኪነትን እንዴት ተቀላቀልክ?
የጊሽአባይ ኪነትን ስቀላቀል ከጎንደር ባህርዳር መጥቼ ነው፡፡ “ማክሰኝት” ከተባለ ገጠር በእረኝነት ሳለሁ ጥጃ የምጠብቅበት ስፍራ ዘፋኞች ይመላለሱ ነበር - ማሲንቋቸውን ይዘው፡፡
እነሱ ሲተኙ እኔ የእነሱን ማሲንቆ እያነሳሁ እመታ ነበር:: ማሲንቆውን አቀላጥፌ ስጫወት ያዩኝ ሙዚቀኞች ወደ ባህርዳር ይዘውኝ ሄዱ፡፡
ባህርዳር ከተማ ማታ ቡና ቤት ውስጥ ማሲንቆ ስጫዎት የጊሽአባይ ባለስልጣኖች አዩኝና
“እኛ ጋ ና” አሉኝ፡፡ በወቅቱ እኔ ማታ ማታ ቡና ቤት እዘፍናለሁ ቀን ቀን ቢስክሌት መንዳት ነበር ስራዬ፡፡
የጎጃም ክፍለሃገር አስተዳዳሪ መጥቶ ለአንድ ቀን ተጋበዝኩ:: በድምጽ ሳቀነቅን ታየሁኝ፡፡ በኋላ ባለስልጣናቱ ጠየቁ
“ይሄ ልጅ ከየት መጣ” ብለው፡፡
በዝግጅቱ ላይ እንድታደም የወሰዱኝ ባለስልጣናት ስለእኔ ሁኔታ ተናገሩ፡፡
“በቃ ይሄን ልጅ ያዙት አሳድጉት” የሚባል መመሪያ ተሰጠ:: በዛ አጋጣሚ የጊሽአባይ ኪነት አባል ሆንኩኝ፡፡ ጊሽአባይ በተቆረቆረ በሰባተኛ ዓመቱ ነበር የተቀላቀልኩት::
በኪነት ቡድኑ ውስጥ እያለሁም የጎጃምን ሰባቱን አውራጃ ዞሪያለሁ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በድምጽ ነው ለጊሻአባይ ኪነት የታጨኸው?
አዎ፡፡ በወቅቱ ግን ከአሳዬ ዘገየ ጋር ሆኜ የማሲንቆ ህጎችን..እከታተል ነበር፡፡
ነገር ግን ማስንቆም እንዴት መጫዎት እንዳለብኝ የበሰለ ነገር ያገኘሁት ከጊሽአባይ ኪነት ነው:: ሁለት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ጊሽአባይ ኪነትን ከዳሁ - ጠፋሁ፡፡
ወደ  ቤተሰቦቼ ተመልሼ ከአንድ ወር በኋላ ግን ወደአዲስ አበባ ሄድኩ፡፡
አዲስ አበባ መርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ሄጄ ጓደኞቼን አገኘኋቸው… ከዛ በሙዚቃ ስራ ቀጠልኩ፡፡
በማስንቆ መሳሪያ ተጫዎችነት ስንት ዓመት ስራህ
ይሄ አደጋ እስከተከሰተብኝ ድረስ ከ25 ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡
ስለሰጠኸን ቃለመጠይቅ እናመሰግናለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here