Interview with Ethiopian American soldier after he is back from afghanistan!

0
2542
ኢትዮጵያዊው የአሜሪካ ወታደር ከአፍጋኒስታን መልስ

ባውዛ፦ ራስህ ለአንባቢያን ብታስተዋውቅልኝ?

ብሩክ፦ ስሜ ብሩክ አስፋው ይባላል። ደብረ ዘይት ነው ተወልጄ ያደኩት።

ባውዛ፦ አየር ሃይል አካባቢ እያዬህ ነው ያደግከው ማለት ነው? ሳቅ

ብሩክ፦ አዎ እንዲሁም አባቴም እናቴም አየር ሃይል ውስጥ ይሰሩ ነበር።

ባውዛ፦ የቤተሰቦችህን ፈለግ ተከትለህ ነው ወታደር የሆንከው?

ብሩክ፦ የነሱ ተፅኖ ይኖረው ይሆናል ብዬ አላስብም ነገር ግን የእነሱ ወታደር ቤት ውስጥ መስራት እነሱን እያየሁ ማደጌ ወደ ኋላ እንዳልፈራ አድርጐኛል። ነገር ግን ወታደር እሆናለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም ነበር።

ባውዛ፦ ወደ US army እንዴት ገባህ?

ብሩክ፦ እዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ በሜሪላንድ ዩንቨርሲቲ ተመዝግቤ ትምህርት ጀምሬ ነበር። እንደ አውት ኦፍ ስቴት ተማሪ ነበር ቲዩሽን የምከፍለው የትምህርት ወጭዬ ከፍተኛ በመሆኑ እና ትምህርቴን ለማቆም በመገደዴ ትምህርቴን የምቀጥልባቸው ሁኔታዎች እያፈላለኩ ነበር። እና ይህ አንዱ ምክንያት ነው ወደ አርሚ ለመቀላቀሌ።

ባውዛ፦ US army ውስጥ ለምን ያክል ጊዜ አገለገልክ?

ብሩክ፦ ወደ 2 አመት ተኩል አካባቢ።

ባውዛ፦ ግዳጅ ላይ ተመድበህ ነበር?

ብሩክ፦ እኔ ያለሁት Maryland National Guard ነው እንደ ተጠባባቂ ጦር ነው የሚወሰደው። ሆኖም ግን active duty ላይ በ አፍጋኒስታን ከ 9 ወር በላይ ቆይቼ አሁን መምጣቴ ነው።

ባውዛ፦ አርሚ ውስጥ ከመግባትህ በፊት የምታስበው እና ከገባህ በኋላ ልዩነቱ እንዴት ነው?

ብሩክ፦ ለብዙ ነገሮች የነበረኝ ግምት ተለውጧል። በጣም ከባድ ይመስለኝ ነበር፣ ልምዱን በጣም ፈርቸ ነበር። ነገር ግን በጣም ከባድ የሚባል አልነበረም። ህይወትህን የሚለውጡ የተለያዩ አጋጣሚዎች አሉ ከነበርኩበት ብርጌድ በአፍጋኒስታን የሞቱብን ሰዎች ነበሩ፣ በጣም ያሳዝናል።

ባውዛ፦ አፍጋኒስታን በምን ክፍል ነበር ያገለገልከው?

ብሩክ፦ የእኛ ሰፖርት(Support) ነው የሚባለው አንድ ቤዝ ይዘን ተቀምጠን ነበር።

ባውዛ፦ በ US army ውስጥ ምታውቃቸው እንዳንተ ትውልደ ኢትዬጵያውያን የሆኑ ወታደሮች ነበሩ?

ብሩክ፦ አዎ አሉ ብዙ ጊዜ ያጋጥመኛል እንዲያውም። እንዴት ወደ army መግባት እና ማገልገል እንደምችል እኔን እና ሌላ ጓደኛዬን መንገዱን ያሳዩኝ ሙሉጌታ የሚባል ልጅ ነው እርሱ ቀድሞ ተመዝግቦ ስለነበረ። እዛ አፍጋኒስታን እያለሁ ደግሞ ሌላ ወታደር ያልሆነ ተስፋዬ የሚባል ልጅ አግኝቻለሁ። በኮንትራክተር በኩል ነው የነበረው።

ባውዛ፦ army ውስጥ በማገልገልህ ያገኘኸው የህይወት ተሞክሮ እና ያዳበርካቸው ችሎታዎች አሉ?

ብሩክ፦ በምናገኘው አድስ ችሎታ አንፃር በህይወትህ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ዲሲፕሊን ትማራለህ። በሰአት መገኜት፣ ጊዜ ባግባቡ መጠቀም እና የተለያዩ ችግሮች ላይ ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻልን ትማራለህ፣ በግሩፕ መስራት ቅፅበታዊ እና ትክክለኛ ውሳኔ መስጠት መቻል ትማራለህ።

ባውዛ፦ ወደፊት US army ለመቀላቀል የሚያስቡ እና የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዬጵያዊያን ወጣቶች ምን ትመክራለህ? በወታደርነት ማገልገል የአገርን ክብር እና የተሰጠህን ሃላፊነት ከመሠጣት በተጨማሪ ምን ጥቅም አለው?

ብሩክ፦ በህይወትህ ላይ የምታከብራቸው ጥቅም ያላቸው ነገሮች ትማራለህ ከዛም በኋላ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ታገኛለህ።

ባውዛ፦ ወጣቶች army እንዲቀላቀሉ ትመክራለህ?

ብሩክ፦ እንግዲህ ውሳኔው የራሳቸው ቢሆን ጥሩ ነው። ምክንያቱም ውትድርና ለሁሉም የሚሆን ሙያ አይደለም የአካል ብቃታቸው ጥሩ መሆን አለበት፣ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትን እና ችግርን መቋቋም የሚችሉ መሆን አለባቸው፣እንዲሁም የውትድርና ስሜቱ ያላቸው ከሆኑ US army ን ቢቀላቀሉ እመክራለሁ።

ባውዛ፦ አሁን ከአርሚ ወጥተሃል ወይስ እረፍት ላይ ነህ?

ብሩክ፦ እኔ እንግዲህ የምሰራው Maryland National Guard ነው። ከአፍጋኒስታን ግዳጅ በኋላ National Guard ውስጥ ነው ያለሁት እንደ reserve army ነው የሚወሰደው። በወር ውስጥ ሁለት ቀን እንዲሁም በዓመት 15 ቀን ሄደን ትሬኒንግ እናደርጋለን። በተጨማሪ አሁን የ Electrical Engineering ተማሪ ነኝ።

ባውዛ፦ በአሁኑ ሰአት በተጨማሪ የእንጨት ጌጣጌጥ እና መገልገያ እቃዎች እንደምትሰራ ሰምቻለሁ ይህንን ስራ የት ነው የለመድከው?

ብሩክ፦ army ውስጥ አይደለም አባቴ ነው ያስተማረኝ አባቴ በጣም ባለሙያ ነው ብዙ ነገሮችን የመስራት ችሎታ ነበረው ከልጅነቴ ጀምሮ የብረጭቆ ወረቀት ይሰጠኝ እና ይህንን አለስልስ ይለኝ ነበር ብረት ስራ ቀለም ቅብ፣ አትክልት መንከባከብ ሁሉንም ነበር የለመድኩት አባቴን በማዬት ነው።

ባውዛ፦ US army join ለማድረግ እና ለማገልገል በተለይ አንተ ያለህበት National Guard ምን ያስፈልጋቸዋል መረጃ እንዴት ያገኛሉ?

ብሩክ፦ National Guard ለመግባት የአሜሪካ ዜጋ መሆን አይጠበቅባቸውም፣ ግሪን ካርድ ካላቸው በቂ ነው ማንኛውም recruiter ጋር ሄደው ማናገር ይችላሉ። ያ recruiter ጤናቸውን አስመርምሮ ሁሉንም ነገር ይጨርስላቸዋል። በተጨማሪም www.nationalguard.com ዌብሳይት ውስጥ ገብተው ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

ባውዛ፦ ስለነበረን አጭር ቆይታ እያመሰገንኩኝ በአጠቃላይ የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ እድሉን ልስጥህ።

ብሩክ፦ በአሁኑ ሰዓት በኢትዬጵያውያን ላይ በሳውዲ አረብያ እየተደረገ ያለው ነገር በጣም ልብ የሚነካ እና አሳዛኝ ነገር ነው። የኢትዬጵያ ኢምባሲ የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግላቸው እጠይቃለሁ። ሌላው በአሁኑ ሰኣት አፍጋኒስታን ውስጥ በግዳጅ ላይ ያለ ዬሃንስ ዘውዴ የሚባል ልጅ ቤተሰቦቹ ቨርጅኒያ ነው የሚኖሩት ለቤተሰቦቹ አይዞህ ለእሱም ደግሞ ብርታቱን ይስጥህ ማለት እፈልጋለሁ።

ባውዛ፦ ጊዜህን ስለሰጠኸን አመሰግናለሁ።

መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here