Artist Behailu Menegesha Passed Away March 3, 2013.

0
1240


Artist Behailu Menegesha Passed Away March 3,2013.
Our deepest Condolences go out to his family and friends,
ፍትሃተ ፀሎቱ Thursday march 7,2013
9:00AM ጀምሮ በ DEBRE MIHERERT ST MICHAIL
ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH
3010 Earl Place NE Washington DC ይካሄዳል።
Reed more about our exclusive interview with  Late Artist Behailu Menegesha .
በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 8 1948 ዓ.ም ነው ተወለደው። ውልደቱ 6 ኪሎ ቢሆንም እድገቱ ሙሉ በሙሉ ጉለሌ ሩፋኤል አካባቢ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ መድኃኔዓለም ት/ቤት ነው ያጠናቀቀው። ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ
አርቲስት አለም ፀሐይ ወዳጆ ጓደኛው ስለነበረች ወደ ሃገር ፍቅር ቲያትር ወስዳ ከነ ተስፋዬ አበበና መላኩ አሻግሬ ጋር አስተዋውቃዋለች።” የቲያትር ሙያ ላይ እንዳተኩር ያደረገችኝ እሷ ናት”ይለናል።
 በኋላም ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን 22ሺ ብር መድቦ አማተር ተዋንያን መልምሎ ሲያሰለጥን ከነ አለምፀሃይ ወዳጆ ፣ አለሙ ገብረአብ ፣ አስራት አንለይ ፣ ሲራክ ታደሰ ፣ ተክሌ ደስታ ፣ ትሩፋት ገ/ኢየሱስ ፣ አልማዝ ሰይፉ ፣ ተዘራ ውብሽት ፣ መሰለች ከበደና በሃይሉ መንገሻ ሆነው ስልጠናውን ይጀምራል ። በመሃሉ ባገኘው ዕድል ለሁለት ዓመት ወደ
ታንዛንያ ዳሬሰላም ሄዶ ወታደራዊ ሳይንስና ማኔጀርነት ይማራል። በኋላም ሃገሩ ተመልሶ ቲያትር ቤትም እየሰራ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ይጀምራል በወቅቱ ” ትግል ይቅደም ትምህርት ይቅደም” የሚባል የፖለቲካ ትግል ስለ ነበር አቋርጦ ወደ ራሺያ ይሄድና በሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት ቀጥሎም በሞስኮ የቲያትር
ኪነ ጥበብ አካዳሚ አምስት አመት ተኩል ትምህርቱን ተከታትሎ በቴአትር አዘጋጅነት “ዳሬክተር የማስተር ኦፍ አርት” ማስትሬት ዲግሪውን አግኝትቷል። በሞያው ለበካታ ዓመታት በሃላፊነት በቤሄራዊ ትያትር ፣ በሃገር ፍቅር ቲያትር ፣ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሰርቷል። ከዚህ በተጨማሪ በአዘጋጅነት ፣ በተዋናይነት በርካታ
ቲያትሮችን ፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን በመስራት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ አድርጓል። አርቲስት በሃይሉ መንገሻ። ለአርቲስት በሃይሉ መንገሻ እዚህ ሃገር ከመጣ በኋላ የመስማት ችግር ስላጋጠመው አንዳንድ ጥያቄዎችን በፅሁፍ አቅርበንለት እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥቶን ነበር።
ባውዛ፡ አሜሪካ አመጣጥህ ለምን እና እንዴት ነበር?
በኃይሉ ፡ ባለቤቴ ወ/ሮ አለም እሸት ከዱ ቀደም ብላ ወደ አሜሪካ መጥታ ስለነበር እኔም ወደዚህ መጣሁ። በሶስተኛው ቀን ነው ወደ ሃኪም ቤት የገባሁት። ወዲያው ሁለቱም ኩላሊትህ ስራ አቁመዋል ተብዬ ዲያልየሲስ “ደሜ ከሰውነቴ ወጥቶ ተጣርቶ መመለስ እንደሚያስፈልገኝ” ተነገረኝ።
ቅድመ ዝግጅት ሰርጀሪ ተደርጌ አስፈላጊዎቹ የላስቲክ ቱቦዎችን ተገጠሙልኝ። ከዚያም ሰነባብተው አንዱ ኩላሊትህ ካንሰር (develope) እያደረገ ነው ብለው በቀዶ ጥገና አወጡት። እንግዲህ ለተለያዩ ሕመሞቼ ከምወስዳቸው ኪኒኖች ውስጥ አንዱ በከፍተኛ ፍጥነት ሁለቱም ጆሮዎቼን አደነቆረኝ። በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ችግር ላይ ወደኩ። ስራመድ ሁሉ መንገዳገድ ጀመርኩ ባለቤቴ ሶስት ወር ያህል ከስራ ቀርታ
በየሃኪም ቤቱ እያሳከመችኝ ለምጠየቀው ጥያቄ መልስ እየሰጠች አስታማ የጆሮዬ ነገር የሞተ ጉዳይ ሆነ። እንግዲህ ካለ ኢንፎሜሽንና ኮሚኒኬሽን መንቀሳቀስ የማትችልበት አገር በመሆኑ ችግር አለው። በአንጻሩ የመስሚያ መሣሪያ ተገጥሞልኝ ትንሽ ትንሽ ይረዳኛል።
ቲቪ ካፕሽን ስላለው እያነበብኩ እከታተላለሁ ቴክኖሎጂው ህይወትን ለማቅለል በብዙ መንገድ ይረዳል። በኋላም ልቤን ከሦስት አርትሪዎች ሁለቱ ጠበው ከሁለቱ ደግሞ አንዱ በጣም ስለጠበበ ቀዶ ህክምና አደረኩ።( እስቴንት) የሚሉት የልቤ አርትሪ ብረት ለቀለበት ገጥመውልኝ አሁን ድህና ነኝ። እግዚአብሔር ይመስገን ጓደኞቼ አብሮ አደጎቼ የባለቤቴ
ዘመዶች ጓደኞች እየተመላለሱ እየጠየቁኝ አስታመውኛል እግዚአብሔር ይስጣቸው። ውለታቸው በደስታ ይከፈል እላለሁ
ባውዛ፡ መተኪያ ኩላሊት አገኝህ እንዴ ?
በኃይሉ ፡ ገና የኩላሊት ትራንስፕላንት እየጠበኩ ነው።ተመዝግቤያለሁ። ከ3-5 ዓመታት ይፈጃል። አገር ቤትም ሰዉ አግኝቼ ነበር ግን የአሜሪካ አሜምባሴ ቪዛ አልሰጥም አለ።
ለሁሉም እግዚአብሔር ቢፈቀደ ጊዜ አገኝ እሆናለሁ ብዬ እየጠበኩ ነው።
ባውዛ፡ ስለ ሥራ ሕይወትህን ጠቅለል አድርገህ ብታጫውተን?
በኃይሉ ፡በመሠረቱ ስራዬ የቲያትር አዘጋጅ በመሆኑ ከዚሁ ከሙያው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሥራ ላይ ነው ብዙ አመት ያገለገልኩት። በብሄራዊ የቴያትር ክፍል ሃላፊ የፕላንና ፕሮግራም የህዝብ ግንኙነትህ ኃላፊ የትያትር ቤቱ ዋና አዘጋጅና አርቲስቲክ ዳሬክተር በመሆን አገልግያለሁ። ከ984 በኋላ የክልል 4 ባህልና ስፖርት ቢሮ የሥነ ጥበባት ማስተባበሪያ ቡድን መሪ በመሆን ቴያትርን ሙዚቃን ሥነ ጽሁፍን ስዕልና
ቅርጻቅርጽን በሚመለከት በሃላፊነት ከባለሞያዎች ጋር በመሆን በማደራጀት የሙያ ፈቃድ በመስጠት በመገምገምና የተለያዩ ስልጠናዎች ጭምር በመስጠት አግለግያለሁ። በቴአትርቤቶች መድረክ ላይ የሚቀርቡትን የቴአትር ቤቶቻችንን የጥበብ ውጤቶች መገምገም ደረጃቸውን እንዲጠበቁ በመቆጣጠር በመደገፍ በማበረታት በመምራትና ሙያዊ አገልግሎት መስጠት ሌላውን የስራ ድርሻዬ ነበር። በ 1990 የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት (city hall) የቴአትርና ባህል አዳራሽ ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን በኋላም የባህልና የማስታወቂያ ቢሮ የቴያትርና የሲኒማ ከፍተኛ ኤክስፐርትነት ተመድቤ ፈቃድ በመስጠት በማሰልጠን በተለይ እያበበ የመጣውን የቪዲዮ
ሲኒማ እየገመገምን በሪፍሌክተር በቴአተር ቤቶቻችን አዳራሽ እንዲታዩ በመፍቀድ ዘርፉ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። በአዘጋጅነት የሎሬት ፀጋዬ ገ.መድኅንን « ጴጥሮስ ያችን ሰዓት » በሃገር ፍቅር ቴአትር “የፊታውራሪ መኮንን ዶሪ“ “የእጮኛው ሚዜ” በብሔራዊ ቴአትር ያስታጥቃቸው ይሁንን “አንቺን አሉ” በብሔራዊ ቴአትር የማክሲም ጎርኪን በረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ
የተተረጎመውን “ቅኝት” በብሔራዊ ቴአትር የሻምበል ታምራት ገበየሁን ”ውጫሌ 7” በብሔራዊ ቴአትር የዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳን “ፍቅር በአሜሪካ” በብሔራዊ ቴአትር የሻምበል ፈቃድ ዮሐንስ “እቡይ ደቀመዝሙር” የተስፋዬ አበበን “የደም ቀለበት” በቴአትርና ባህል አዳራሽ የሰራዊት ፍቅሬን “የከርቼሌው ዘፋኝ” የአሰፋው አፅማት “የምሽት ፍቅረኞች“ ቴአትሮችን በቲአትር ባህል አድራሽ
መድረክ አቅርቤያለሁ። በተዋንያንነት በሃገር ፍቅር ቲአትር የብርሃኑ ዘሪሁን ” የአርባ ቀኑ መዘዝ” የተስፋዬ አበበ ሙዚቃዊ ድራማ በሃገር ፍቅር ቲያትር የፀጋዬ.ገ/መድን”ሀሁ በስድስት ወር” ሁለተኛው የገፀ ባህርይ ምድብ በመሆን የተስፋዬ ሣህሉን ፣ አለሙ ገ/አብ፣ ጠለላ ከበደን ፣ አለምፀሐይ ወዳጆ ፣ አውላቸው ደጀኔን ፣ ሲራክን ታደሰ ፣ ወጋየሁ ንጋቱን ፣ ተክሌ ደስታ ጀምበሬ ጥላሁን ፣ አስራት አንለይ፣ ጌታቸው ይበልጣል ፣ በኃይሉ መንገሻ ፣ በመሆን
በኋላ በወጣት ተዋንያን የተገነባውን ቲአትር ይዘን ጅማ ፣ መቱ ፣ አሰላ ፣ ድሬዳዋና ሐረር ፣ አሳይተናችው የፀጋዬ ገ/መድኅን “አቦጊዳ ቀንሶ” በብሔራዊ ቴአትር የፀጋዬ ገ/መድኅን አፅም ብየገፁና የመቅደላ ሰንበት ብሔራዊ ቴአተር። በቴሌቪዥን የተስፋዬ አበበን “አባ ውቃውና ጋዜጠኛው” የተሰኘውን ከ1966ጀምሮ የተለያየ የቲቪ ድራማዎችን
በፊልም (the adventure of tom sawyer and hunky berry fin) የአማሪካዊው ክላሲክ ደራሲ የማርክ ትዌይን በሞስኮ - የሲኒማ ኩባንያ የቀረበው ላይ ፣ የእንግሊዝ ኩባንያ ያቀረበው ላይ ቢቢሲ (channel 4 &carnival films) ያቀረቡትን ( the big battalions ) የተሰኘው ፊልም ላይ ጎንደር ሲሳይ
የተባለ ገፀባህርይ እና የተለያዩ ፊልሞች ላይ ትንሽ ባህርያትን ተውኛለሁ። በትይንተ ጥበባት ክብደትን የተለያዩ ባለ አንድ ገቢር ድራማዎችና በዝግጅትም ሰርቼአለሁ። በሙያዬ በተለየና በትውነናና በዝግጅት በተከታታይ የሦስትና የአራት ወር ስልጠናዎች ከምልመላ ጀምሮ በመምህርነት ለማገልገል ወጣትና ተተኪ ባለሙያዎችን አፍርቼአለሁ። የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈፃሚ አባል በመሆን በአገር ውስጥ በውጭ ሃገር የገንዘብ አሰባሰብን በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ የኪነጥበብ አቅርቦትን የተለያዩ ክፍላት ሃገራት በመዞር የስፖርት ውድድሮችን በማዘጋጀት የኦሎምፒክ አላማን በመግለጽ ስፖርተኞች ሲሄዱ መሸኘት። ሲመለሱ ለየት ያለ የድል አድራጊ አቀባበል በማዘጋጀት
ከቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ እስከ ስታዲየም ያለውን ዝግጅት በመምራት ሰርቼያለሁ። በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመካከለኛውና የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን አገራችን አዘጋጅ በነበረችበት ጊዜ የአብይ ኮሚቴ አባል በመሆን ከውጭ ከሚመጡ ስፖርተኞች የእግር ኳሱ ኃላፊዎች ደጋፊዎችን ጋዜጠኞችን መቀበል መስተንግዶና አሸኛኘቱ የህትመት ሥራዎች ፖስተር ፍላየር ባጅ ስቲከር የመሳሰሉትን የመሳሰሉት ዝግግቶች ላይ ተሳትፊያለሁ ቡድናችንም ለድል በቅቷል። በግል የተለያዩ የቴአትር ክለብ የሚያዘጋጃቸውን ቴአትር በመገምገም የቴአትር ድርሰት (ስክሪፕት በመገምገም ፣ በማሰተካከልና በማስተማር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ።
ባውዛ፡ የወጣቶችን ሥራ በቴአትሩ ዘርፍ እንዴት ታየዋለህ?
በኃይሉ ፡ በአሁኑ ጊዜ እንቅስቃሴ ቢደረግም ትልቁ ችግር የአዳራሽ ችግር ነው። ያሉት አዳራሾች የቴአትር ቤት ደረጃ ያላቸው ሁለት ናቸው። ቀደም ብሎ ሃገር ፍቅር ቴአትር ከዚያም በ 1948 ዓ.ም ብሔራዊ ቴአትር ናቸው። በዚያን ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪ 700 ሺ ነበር። በኋላም ሲቲ ሆል ቴአትር ባህል አዳራሽ ለፊልምና ለወቅታዊ ኮንሰርቶች ነው የተሰራው። በችግርና በግድ ነው ቴአትር ቤት የሆነው። ራስ ቴአትርም እንዲሁ አሁን የአዲስ አበባ ህዝብ ከ4 ሚሊዮን በላይ ቢሆንም ያሉት ቴአትር ቤቶች ያው የነበሩት ቴአትር ቤቶች ናቸው። ባለሃብቱም ሆቴልና አልቤርጎ ነው የሚገነባው። ስለዚህ መድረክ አዳራሽ ሳይኖር የወጣቱን ሥራ ለማቅረብ
ለማወዳደር አይቻልም። ስራቸውን ወደ ፕሮፌሽናል መድረክ ለማምጣት የአዳራሽ ኪራይ ውድነት የቅዳሜና እሁድ ፕሮግራም በቴአትር ቤቱ መደበኛ ባለሙያዎች መያዝ ፦ ለወጣቱ ፕሮዳክሽን የአዘቦት ቀን ከ ፡00 ሰዓት በኋላ መስጠት ደግሞም እነዚህ ቴአተር ቤቶች ፒያሳና ዝቅ ሲል ብሔራዊ ቴአትር ነው። ዛሬ ገርጂ ረጲ አስኮ ፡ አቃቂ ፡ ካራ ነው ብዙ ሰዎች የሚኖሩት። ከልምምድ በኋላ ማታ ወደ ቤታቸው መግቢያ ትራንስፖርት አያገኙም። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር አርት የተመረቁ በተለያዩ የግል ድርጅቶች ስልጠናዎች ያገኙ ባለሙያዎች ጥረት ያደርጋሉ። ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ሁሉ አልፈው ጥሩና ሊታይ የሚበቃ ውጤታማ ሥራ
የሚያቀርቡ ወጣቶች እያበቡ ናቸው። ለኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረጉ ነው። በተለይ አሁን በቴአትር ቤት አንጋፋዎቹ ፀሐፊ ፣ ተውኔቶች አዘጋጆችና ተዋንያን በሌሉበት ወቅት ትራዲሽኑን እየተቀበሉ እየሄዱ ነው። በታሪክ እንደምታውቁት ቀደም ሲል ቴአትር ከሙዚቃ ጉርሻ ጋር ነበር የሚቀርበው። ከነ ሎሬት ፀጋዬ በኋላ በ “ሀሁ በስድስት ወር”ተአምር ታየ። በዚያው ቀጠለ። በርግጥ የስክሪፕት ( የቴአትር ጽሁፍ) ድርቀት አለ። በቋንቋም በሴራም በገፀ ባህሪ አሳሳልም ብዙ ጠንካራ ባይሆኑም ተመልካቹን እያረኩ ነው። ከሩቅ ቦታ በፀሐይና በዝናብ ወደ ቴአትር ቤት አድራሽ ባለበት አካባቢ እየተመላለሱ ካለ ውሎ
አበል አንድ ምግብ ለሁለት ለሦስት እየበሉ በክፍላት ሃገር ቴአትር እያቀረቡ ይገኛል። ወጣቶች እንግዲህ መድረክ ሳይኖራቸው ተቀጣሪ ሳይሆን የጥበቡ ፍላጎትና ዝንባሌ ይዞአቸው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አንዳንዶቹም ትልቅ ቦታ እየደረሱ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
ባውዛ፡ የኢትዮጵያን የቲያትር ዕድገት እንዴት ታየዋለህ?
በኃይሉ ፡ ዮፍታሄ ንጉስ ናቸው የዘመናዊ ቲያትር አባት። አቶ ተስፋዬ ገሠሠ በጥናት ጽሁፍ እንዳቀረበው ታዲያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብዙ ልፋትና ድካም ተደርጎለት ብዙ የወቅቱ ወጣቶች እድሜአቸውን ጨርሰውበት በዚያን ዘመን የነ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ፣ ደራሲ መንግስቱ ለማና ዘመነኞቻቸው መፈጠር የወቅቱ ወጣቶች እንደ ተስፋዬ ገሰሰ ደበበ እሸቱ ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ አባተ መኮንን ፣ ተፈሪ ብዟየሁ ና ሃይማኖት አለሙ ወደ ውጪም ሄደው ሙያቸውን በከፍተኛ ትምህርት ተክነው ወደ አገር ቤት መድረክ መጥተው መሥራት መጀመር ሙያው እንዲያብብ እንዲበለጽግ አድርጎታል። በተጨም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወጣቶች በቴአትር አርስት
በመጀመሪያ ዲግሪ ማስመረቁ ለእድገቱ ከፍተኛ አስተዋጾ ነበረው። በኋላም በኢህአዲግ የስልጣን መጀመሪያ አመታት ጉድ መፍላት ጀመረ። ጨርሶ ከመድረክ ጋር የማይተዋወቁ በፀሓፊ ተውኔትና በአዘጋጅነት ምንም አስተዋጾና አቅርቦት ያላደረጉ ግለሰቦች የሃላፊነት ቦታ መረከብ ጀመሩ።ከእኛ የተሻለ ሰውም ማየት አንሻም አሉ። በተለይ የቴአትር ድርሰት መረጣ ወደ ቴአትር ቤት በተዛወረ ጊዜ የዘርፉ ሙያ እውቀቱ የሌላቸው “በእከክልኝ ልከክልህ” በትውውቅ በጓደኛና በዘመድ መሰራት ተጀመረ።ደግሞ የትውውቅና ስራ አይን ይጋርዳል። እነዚያ በተመልካች ተጨናንቀው የነበሩ አዳራሾች ወደ ኦናነት የተለወጡበት ጊዜ ነበር። ሃላፊዎች ከነሱ
የተሻለ ሥራ የሚሰሩትን ያገሏቸዋል። ታዲያ ጥበቡ ይጫጫል የህዝብንም አደራ መወጣት አይቻልም። ጥበብ ቦታውን ያውቃል በአንጻሩም አንዳንድ የግል ጋዜጠኞች ደግሞ ምንም ያልሰሩትን ጀማሪ አርቲስቶች ክበው አየር ላይ ያነሳፍፏቸዋል። ጋራ ያሳክሏቸዋል። ለጥበቡ ውድቀት ይሄ አንድ አስተዋጾ አለው። ማን ነክቶኝ ማንስ ሂስ ሰጥቶኝ ብለው ቡራ ከረዮ ይላሉ። ታዲያ በምን መንገድ ጥበብ እንዴት አድርጎ ሊያድግ ይችላል? አሁንም በኪነ ጥበብና በሥነ ጥበብ አገልግሎት ውስጥ ጥበቡን የሚያውቅና ሊመራ የሚችል ሰው ቢመደብ መልካም ነው። ማን ፕሮፌሽናል ማን አማተር እንደሆነ ያውቃል። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ፣
ተስፋዬ ገሠሠ ፣ ተፈሪ ብዙአየሁ ፣ ተስፋዬ ለማ ፣ አባተ መኩሪያ ፣ ኢዩኤል ዮሐንስ ፣ ጌታቸው አብዲ ፣ ኃይማኖት አለሙ ፣ አማን ኢብራሂም ፣ ደበበ እሸቱና አለምፀሐይ ወዳጆ የመሰሉ ሰዎች የመሩት የቴአትር ጥበብ ነበር። አሁን የት አለ? ሰው አለ ግን ሙያና ሙያተኛ አልተገናኙም። ተስፋ ሰጭው እንደ ጌትነት እንየው ከቴአትር ቤት ውጪም እንደ አያልነህ ሙላት እንደ እነ ሰራዊት ፍቅሬ ፣ አለልኝ መኳንት ያሉ ባለሙያዎች ጥበቡን ለማሳደግ እየታገሉ ይገኛሉ። ሕዝብ ተመልካች ማበረታታት አለበት። ጥበብ አንዴ ይነሳል አንዴ ይወድቃል። አረረም መረረም የሚመዝናት ሂስ ነው። የሂስ ባለሞያዎች አለመኖር
ደግሞ አንዱ ትልቁ ችግር ነው።
ባውዛ፡ የትዳር ህይወትህና ልጆችህ በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ብታጫውተን?
በኃይሉ ፡ በ1979 ጥር ላይ ነው ከባለቤቴ ወ/ሮ አለምሸት ከዱ ጋር የተጋባነው። ። አለምሸት ባለቤቴ ፣ እህቴና እናቴ ናት። አሁንም በታመምኩበት ጊዜ አስታማሚዬ ናት። እሷ ናት ያለችኝ ማን አለኝ? ምግቤ ለየት ያለው ነው ኩላሊት ከሌለብህ ቲማቲም ፣ ድንች ፣ ሙዝ ፣ ብዙ ምግቦችን በፍራፍሬም የበለፀጉ አትበላም። አሜሪካ ደግሞ ቲማቲም አትበላም ማለት የአበሻው ወጥ ፣ ፓስታው ፣ ፍሬንች ፍራይድ ፣ፒዛ፣ ሳንድዊች ሁሉ ሲያምርህ ይቀራል። ደግሞ ለስኳር የምከላከላቸው ምግቦች አሉ። አሁን በተጨማሪ ለልቤ የምከለከለው አለ። ስለዚህ ይህን ሁሉ አስተካክላ ሰርታ ትመግበኛለች። እኔ ሥራ የለኝም እሷ ናት ሰርታ የምታስተዳድረኝ።
በጣም ጥሩ ሰው ናት። እግዚአብሔር ልፋቷን ይቁጠርላት እንጂ እኔ ምን አደርጋለሁ። ልጅ አንድ ነው ያለኝ። ምኒሊክ በኃይሉ ይባላል። አሁን በዚህ ኦገስት ወደ ኦሃዮ ክሊቭላንድ ዩኒቨርሲቲ ይገባል። ለአምስት ዓመት ስኮላር ሺፕ አግኝቷል። ምህንድስና አጠናለሁ ነው ያለኝ። ከናቱ ጋር በመሆን አስታማሚዬ ነው። ኢትዮጵያ ቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት ከመማሩም ይልቅ ታዛዤ በመሆኑ ነው ምርቃቴ መሰለኝ ስኮላርሺፕ ያስገኘው ጎበዝ ተማሪ ነው። መጨረሻውን ያሳምርለት እላለሁ።
ባውዛ፡ የተደሰትክበትና ያዘንክበት ጊዜ የሉህም?
በኃይሉ ፡ቴአትር አዘጋጅቼ ሳስመርቅና የተለያዩ ብዙ የተደሰትኩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም እንደ ሠርጌ ቀንና ልጅ እንደወለድኩበት ቀን የተደሰትኩበት ጊዜ የለኝም። ያዘንኩበትና ልብ የተሰበረበት ጊዜ አቶችም አሉ። በሃገር ጉዳይ በፖለቲካው ሂደት ጉዳይ ግን ከሁሉም በላይ አሁን ድረስ ሳስታውሰው የሚያሳቅቅ ነው። ሌላው ታናናሽ ወንድሞቼ የኢንጂነር ታምሩ መንገሻና የኢንጂነር ይልማ መንገሻ ድንገተኛ ሞት ነው። ለራሳቸው ለቤተሰባቸው ለሃገራቸው ትልቅ ቁም ነገር የሚሰሩ ወጣቶች ነበሩ።
ባውዛ፡ እዚህ ከመጣህ በሙያህ ምን አደረግክ?
በኃይሉ ፡ ያው ታማሚ በመሆኔ የህመሜ አይነት ደግሞ የማይመች በመሆኑ ምንም ትርጉም ያለው ነገር መሥራት አልቻልኩም። ግን አብሮ አደጌና የጥበብ ጓደኛዬ አለም ፀሐይ ወዳጆ የጣዪቱ ኢንተርቴይንመንት ሥራ አስኪያጅ በሷ ፕሮግራሞች ላይ እንድሳተፍ አመቻችታልኝ የአንጋፋ የሥነ -ፅሁፍ ግጥሞችን በማቅረብና በአንዳንድ የኪነ-ጥበብ ሰዎች የህይወት ታሪክ ዙሪያ በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ መድረክ አግኝቻለሁ።
ባውዛ፡ ከአንተ የህይወት ልምድ ህብረተሰቡ ምን ሊማር ይችላል?
በኃይሉ ፡ አንዱ ትልቅ ነገር ሰው ከጣረ ከደከመ አላማ ይዞ ከታገለ ከፈለገበት ግብ የማይደርስበት ምንም ምክንያት የለም። እኔም በኪነ-ጥበብ ከወጣትነት ጀምሬ በልምድ ፣ በትምህርትና በሥራ እዚህ ደረጃ ላይ ደረሼ ነበር። ግን መጨረሻ በበሽታ ተለከፍኩ። ከኔ ልምድ በተለየ በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው ኩላሊት ሳይኖረው
መስማት ተስኖት የልብ ችግር እያለው እግዚአብሔርን እያመሰገነ በተመቻቸበት መድረክ ላይ የአቅሙን ያህል መንቀሳቀስ መሞከሩ ትልቅ ነገር ይመስለኛል። ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው።
ባውዛ አመሰግናለሁ
በኃይሉ ፡ እኔም አመሰግናለሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here