Artist Setegn Atenaw & Wubet Mekonnen Best Wedding!!

0
2741
Photo By Matt Andrea

የአርቲስት ሰጠኝ አጠናው እና የሙሽሪት ዉቢት መኮነን ዕለተ ሰርግ

እለቱ ቅዳሜ Feb፣ 23, 2013 ምሽቱ  የሁለት ጥንድ ሙሽሮች መሞሸሪያ፣ የ3 ጉልቻ የትዳር ማጠናከሪያ፣ ለዘላለም በፍቅር አንቺ ትብስ እኔ ትብስ እየተባባሉ ቀሪዉን ህይወታቸውን አብረው ጥንድ ሆነው ለመኖር ወዳጅ ዘመድ ጔደኛ ተጠርቶ ሙሽራዬ የሚዘፈንበት መልካም የሰርግ የደስታ ምሽት ነበር። የዚህም ታላቅ የተቀደሰ ዕለት ባለቤቶች ሙሽሮች ከነበሩት የወንድ ሙሽራው በማሲንቆ አጨዋወቱ እድሜውን በሙሉ የኢትዬጵያን የባህል የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች የሆነው በማሲንቆ አጨዋወቱ ይበል የተባለለት የብዙዎቹን የዘፈን ካሴት ያጀበ ገና ድሮ ማሲንቆውን ይዞ በጐጃሙ የባህል ግሽ አባይ ኪነት ውስጥ ሙያውን  አሣይቶ የሙዚቃ ቡድኑን መሸጋገሪያ አድርጎ በአዲስ አበባ አንጋፋውና ታላቁ በብሄራዊ ቲያትር ቤት በባህል የሙዚቃ ክፍል ውስጥ ችሎታውን በማሳየት በጊዜው በኮከብ ተጫዋችነት ዝናውን ያስመዘገበው በኢትዬጵያ ውስጥና እንዲሁም ወደ አሜሪካን እና ካናዳ  ለሚኖሩ ከትንሽ እስከ ትልቅ በደስታቸው ጊዜ ሁሉ እየተገኘ ሠርጋቸውን፣ ክርስትናቸውን ግራጅዬሽናቸውን ያደመቀ የዘፈነላቸው በድምፁ እያዜመ የዳረ የማሲንቆው ንጉስ እያሉ አብሮ አደጐቹና የስራ ባልደረቦቹ የሚያሞግሱት አርቲስት ሰጠኝ አጠናው እና የሙሽሪት ዉቢት መኮነን ዕለተ ሰርግ ነበር።

በአዳራሹ ከህፃን እስከ አዛውንት ብዛት ያላቸው የሰርጉ ታዳሚዎች እና የሙዚቃ ቤተሰቦች  በዋሽንወግተን አካባቢ ኑሮአቸውን ያደረጉ ብዛት ያላቸው አርቲስቶች፣ ዘፋኞች፣ ተወዛዋዦች፣ ቲያትረኞች፣ ኮሜዲያኖች እና በኢትዮጵያ የዚህን ጥበብ ሙያ የሚሳተፉ ታላላቅ አርቲስቶች አንጋፋውን አርቲስት መሀሙድ አህሙድን፣ አርቲስት ቀለመወርቅ  ደበበን፣ አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆንና ሌሎችንም ታዋቂ ድምፃዊያን ያካተተው አዳራሽ ተጨናንቆ ይታይ ነበር።

ከዚያም ታዳሚውና መላው አርቲስት የሙሽሮቹን መምጣት ይጠባበቅ ነበር አስከትሎም  የሙሽሮቹን የሰጠኝ አጣናውንና የውቢት መኮነን ወደ አዳራሹ እየገቡ መሆኑን ሲበሰር ከመካከል አንጋፋው አርቲስት መሀሙድ አህመድ ከወንበሩ ተነስቶ ወደ መድረኩ በመቅረብ ማይክራፎኑን ይዞ ሙሽራዬ የወይን አበባዬ! ሙሽራው የወይን አበባው! እያለ ሲያዜም ታዳሚው አንዴ መሀሙድን አንዴ በቶክሲዶና በቬሎ ተሸልመው ወደ አዳራሹ የሚገቡትን ሙሽሮች እያዩ ሲደሰቱ ሁሉም ታዳሚውና የጥበብ ሰዎች በሙሉ ከወንበራቸው ተነስተው በእልልታና በሆታ የጋሽ መሀሙድን ሙሽራዬ እየተቀበሉ እያስተጋቡ አዳራሹ በመረዋ ድምፅና በጭብጨባ ተናወጠ። ሙሽሮች ከገቡ በኌላ ከመቀመጣቸው በፊትም እንደገና ታላቁ አንጋፋው ድምፃዊ መሀሙድ አህመድ ሞቅ ደመቀ ባለ ሽብሸባ (ይትባረክ እንዳብርሃም) እያለ ዘመረላቸው እኛም በአዳራሹ ውስጥ ያለን ድምፃዊያን ተቀበልነው። በምሽቱ ከነበሩት የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አባቶች ለምርቃት የመጡት ሁሉም አሸበሸቡና የአብራሃምና የሣራ ሰርግ እንዲሆን ተመኝተው ባረኳቸው።

ከዚያማ መድረኩ አልበቃ አለ! ከነበሩት ዘፋኝ ጓደኞቹ  ብዛት ሰአትና ቦታ አልበቃ ብሎ ነበር የመዝፈኛ ማይክራፎኑ ከአንዱ ወደአንዱ ሲቀባበል ሁሉም እንኳን ደስ ያለህ የመልካም ጋብቻ ምኞቱን ሲገልፅ አመሸ። እንዲያው በጥቅሉ በቦታዉ ለነበረ ምነው የአርቲስት  ቤተሰብ ወይም አርትቲስት ብሆን! የሚል ምኞትን ያሳደረ ምሽት ነበር።

“ሌላውስ ሌላ ነው ምን ጊዜም አታጭው

ከያኔ ጠጅ ነው አዘንብለሽ  ጠጭው”

በማለት በአርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ በተገጠመው ግጥምና በሙሽራው በሰጠኝ አጠናው  በተጫወተው ግጥም እንሰነባበት።

እኛም የባውዛ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች በቦታው ተገኝተን እንኳን ደስ አለህ በማለት መልካም ምኞታችንን ገልፀናል።

መልካም የትዳር ዘመን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here