Artist Kelemework Debebe Recieving award @ the Ethiopian Expo Sep 15 2012

0
379

 

“ቅኔንም ቢዘርፉ ድጓም ቢያስመርቁ

ሳይንስ ቢያጠኑ በእውቀት ቢራቀቁ

ምን ቢመራመሩ የአለም ቋንቋ ቢያውቁ

የባህልን መሰረት

የባህልን ምንነት

የባህልን ጥቅም

አውቀው ካልተረዱ

በአእምሮ ወንፊት አንጓለው ካልለዩት ፍሬውን ከእንክርዳዱ

እውቀት ፋይዳም የለው ለዘር ለትውልዱ።”

አርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ

የቲያትርና ሙዚቃ መነሻ የሀገራችን የቤተክህነት ትምህርት እንደሆነ የሚያወሱት አርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ የዛሬ የባውዛ የኪነጥበብ እንግዳችን ናቸው። ተሰፍሮ ከማያልቀው እውቀታቸው፣ የስራ ላይ ገጠመኛቸውንና ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በተመለከተ በትንሹ ቆንጥረን ለአንባቢያን ለማካፈል ወደናል።

ባውዛ – አርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ በመጀመሪያ የባውዛ የኪነጥበብ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በጣም እናመሰግናለን። እስኪ በመጀመሪያ ስለግል ታሪክዎ ከትውልድዎ ጀምረው ስለአስተዳደግዎና ስለትምህርትዎ ቢገልጹልን።

 

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – የተወለድኩት ጥር 11 1933 ነው። ቤተሰቦቼ አባቴን ጨምሮ ካህናት ስለነበሩ እኔም ካህን እንድሆን ጥረት ያደርጉ ነበር። ያደኩት እና የተወለድኩት በወሎ ክፍለ ሀገር ላስታ ቅዱስ ላሊበላ ነው። በመጀመሪያ በቤተክርስቲያን ትምህርት ፊደል ከቆጠርኩ በኋላ ግሸን ማርያም አቡነ ሚካኤል ከሚባሉ አባት የድቁና ማእረግ አግኝቼ ከዚያ በድቁና እያገለገልኩ የዜማ የቅኔ ጾመድጓ ትምህርቴን አካባቢው ባለው ቤተክርስቲያን መምህራን ባሉበት ትምህርቴን ቀጠልኩ። በዛ ጊዜ ቅኔ በአካባቢያችን የሚከበር ትምህርት ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ቅኔ ካላወቀ ካህንም ቢሆን የሚያነበውን መተርጎም አይችልም። በዛ ላይ ውድድር ነበር።ስለዚህ  አንድ የዜማ መምህራችን ነበሩና እሳቸውን ተከትለን ወደ ቤተልሄም ጎንደር ሄድን ስንማር ቆየን። ከዛ አዲስ አበባ እንሂድ በሚል የወጣትነት ስሜት ተነሳስተን ወደ ሰባት የምንሆን ጓደኛሞች ወደ አዲስ አበባ መጣን። ኡራኤል ቤተክርስቲያን መሪ ጌታ አድማሴ የሚባሉ ታላቅ የቅኔ መምህር ነበሩ ጎጃሜ ናቸው። እና እሳቸው ጋር ቅኔ እየተማርን በድቁና ማገልገል ጀመርኩ።

ባውዛ – አርቲስት ቀለመወርቅ ወደ ኪነጥበብ አለም እንዴት ገቡ? ከገቡ በኋላስ ያሳዩት እድገትና የነበረዎት አስተዋጽኦ ምን ነበር?

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – በዚያን ጊዜ እሪ ስለ እብነ ገብረመስቀል የሚባሉ አገር ፍቅር የሚሰሩ ታዋቂ ድምጻዊ ድጓና ጾመድጓውን ዜማውን እየቀመሩ በተለይ በጾም ጊዜ በሬድዮ ያስተላልፉ ነበር። የዛኔ ከእሳቸው ጋር ሀገር ፍቅር ስሄድ በማይበት ጊዜ ዜማው ውዝዋዜው ቤተክህነት ነክ ነበረና ወደ ኪነጥበብ ተሳብኩኝ። ያ ጊዜ የሀገር ፍቅር አስተዳዳሪ የነበሩት ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ይባሉ ነበረ እና እሳቸው ፊት ቀርቤ ተፈተንኩ ፈተናው የወረብና የምስማከ ዜማ ነበር ድምጼ ጥሩ ነበር እሳቸውም ደስ አላቸውና ቀጠሩኝ። ለተወሰነ ጊዜ የኪነጥበብ ስራ መሪ ከነበሩት አቶ ማቲዎስ በቀለ ጋር ሳገለግል ቆየሁ። የዛኔ ሀገር ፍቅር ሶስት ቡድን ነበረ። እኔ አቶ ኢዩኤል ዮሀንስ የማባሉ ሰው ቡድን ጋር ደረሰኝ። ከዚያ በዜማ፣ በሽለላ እና በፉከራ ሳገለግል ድምጼም ጥሩ ነበር፤ ልጅነቱም አለ እና እየሰመረልኝ እነሱም እየወደዱኝ ሄዱ። ሙያውንም በጣም እያፈቀርኩት ሄድኩ ድራማ፣ አጫጭር ታሪኮች፣ ግጥሞች፣ ቲያትሮችን እና ዜማዎችን መጻፍ ጀመርኩ ሙያውን እየወደድኩት ሄድኩ ። የበለጠ እንድወደው ያደረገኝ ወደ ውጪ የነበረው ጉዞ ነው።

ባውዛ – በዚያን ዘመን በኪነጥበብ ሙያ ለተሰማሩ ሰዎች የነበረው አመለካከት ምን ይመስል ነበር?

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – አገራችን ለኪነጥበብ ሰው ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው። አዝማሪ ነበር የሚባለው። ከበሬታ አለነበረም። ውጪ ግን ለባለሙያዎቹ ያለው ከበሬታ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ አየሁኝ። ይሄ በዚህ ሙያ ላይ የበለጠ እንዳተኩር አደረገኝ። ቤተሰብ የሚፈልገው ሌላ ትምህርት ተምሬ “ጥሩ” ደረጃ ላይ እንድደርስ ነው፤ እኔ ደግሞ ህሊናዬ ወደ አዘዘኝ ሄድኩ።ድራማውንም ሙዚቃውንም ህዝቡ እየወደደልኝ ሲሄድ እኔም ቀጠልኩ።

ባውዛ – በኪነጥበብ ሙያዎ ያበረከቱት ድርሻ ምን ይመስል ነበር?

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – በ1970 ዓ.ም. የወሎ ክፍለ አገር “እኛ ባህላችንን ማሳደግ ስለምንፈልግ ሰዎች ላኩልን ባህላችንን የሚያደራጁ” የሚል ጥያቄ ለባህል ሚኒስቴር አቀረቡ ይህ እንግዲህ በደርግ ጊዜ ነው። ባህል ሚኒስቴር እኔን ጨምሮ 6 ሰዎች ላከ። እዛ የላሊበላ የኪነት ቡድን አቋቋምኩ እና ወሎ ባህል አምባ የሚባል ቲያትር ቤት አስፋፋን። ነገሩም ሰመረ የኪነት ቡድኑም ታዋቂነት አገኝ ። እስከ 1975 ዓ.ም. እዛ ሳገለግል ቆየሁ። ከዛ ወደ አዲስ አበባ ተመልስኩ። አዲስ አበባ በተመለስኩ በሁለተኛው ወር የጎንደር ክፍለሀገርም ተመሳሳይ ጥያቄ እኔን በስም ጠቅሰው አቀረቡ። እኔም ስራውን ስለወደድኩት እና ከቲያትር ቤት ይልቅ ገጠር በመሄድ ብዙ እማራለሁ ብዬ ስላሰብኩ አላቅማማሁም ወደ ጎንደር ሄድኩ። ጎንደር በአስተዳደር ስራ አልገባሁም ለ9 ወር ከወረዳው የመጡትን የኪነጥበብ አባላት በድራማ፣ በውዝዋዜና በሙዚቃ በማሰልጠን የፋሲለደስ የኪነት ቡድን የሚባለውን አስመረቅን።ከዛ በክፍለ አገርና በአዲስ አበባ የኪነት ቡድን ሽኩቻ ስለነበረ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ።

ባውዛ – አርቲስት ቀለመ ወርቅ የወሎን እና የጎንደርን የኪነጥበብ ቡድን አሰልጥነዋል። የዛ ስልጠና ውጤት ናቸው የሚሏቸው የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ቢጠቅሱልን

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – ብዙ ናቸው ባጭሩ ለመጠቆም ያህል በወሎ ላሊበላ ኪነት ውስጥ ማሪቱ ለገሰ፣ ጸሀይ አማረ፣ ጸሀይ ካሳ እና አሁን የማላስታውሳቸው ብዙ ልጆች አሉ። በጎንደር ኪነት ውስጥ ደግሞ አበበ በለው፣ አበበ ብርሃኔ፣ አሰፉ ደባልቄ፣  እነዬ ታከለ፣ ዋሴ ካሳ እና ሌሎችም ናቸው። እንዚህ ህዝብ ለህዝብ በተባለው የባህል ጉዞ በመሳተፍ የላቀ ሚና ተጫውተዋል። ብዙዎቹ ደስ የሚያሰኝ ደረጃ ላይ ነው ያሉት። አንዳንዶቹ እንደነዚነት ሙሀባ የመሰሉት ደግሞ ባጭር የተቀጩ ልጆች አሉ። ብቻ ሁለቱም የኪነት ቡድን ለኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ልጆች ያፈራ ነው።

ባውዛ – ሀገር ፍቅር የነበረዎን ቆይታ እንዴት ያስታውሱታል?

 

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – ለኔ ያደኩበት ዩኒቨርስቲዬ ሀገር ፍቅር ነው። እዛ የማልረሳቸው ያስተማሩኝ ታላቅ ሰው አቶ እዩኤል ዮሀንስ ናቸው። የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ እድገት ሲወሳ በተለይ የባህሉን እድገት በማምጣት እንደ አቶ እዩኤል ትልቅ ሚና የተጫወተ የለም። አንደኛ ደራሲ ናቸው፤ ሙዚቃውን ይቀምራሉ፣ ሙዚቃውን ይጫወታሉ፣ ከዛ ደግሞ መድረክ ላይ ወጥተው ይወዛወዛሉ። እና ከሳቸው ብዙ ተምሬያለሁ። የዛኔ እንዳሁኑ ኪነጥበብ አላደገም ነበር። ህዝቡ ሙዚቃውን የማየት ፍላጎትና ጉጉት አለው። እሁድ እሁድ ነበር አገር ፍቅር ዝግጅት የሚታየው። ከአዲስ አበባ ወጣ ስንል ደግሞ ቲያትር ቤት ስላልነበረ እኛው እራሳችን አዳራሽ ተከራይተን፤ ከየጠጅ ቤቱ ወንበር ሰብስበን ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈን ነበር የምናሳየው። ያሁን ጊዜ የኪነጥበብ ባለሙያ የታደለ ነው የተምቻቸ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። የዛኔ ግን ትኬት ቆራጭ እኛ ነን፤ አስተናባሪ እኛ ነን፤ ከዛ ደግሞ ገብተን ቲያትርና ሙዚቃውን እንጫወታለን። ይህ ሁሉ ሲሆን ልጅነትም ስላለ እንወደዋለን እንጂ ሰልችተንና ተመረን አናውቅም። በደሞዝ ደረጃ ስታየው በዚያን ጊዜ የነበረው ትልቁ ደሞዝ 30 ብር ነው። የተቀረው ከዛ በታች ነው ያለው።ግን ይሄ ሁሉ ሳያስመርረን በሙያው ፍቅር ተግባብተን ሀገር ፍቅርን ለብዙ ጊዜ አገልግለናል።

ባውዛ – በዚያን ጊዜ የነበረውን የኪነጥበብ ስራ ከአሁኑ ጋር እንዴት ያነጻጽሩታል?

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – የአሁኑ ጊዜ አርቲስት እድለኛ ነው መሰረቱ ያ መሆኑን ይወቅ አይወቅ አላውቅም ግን ትንሽ ነገር ሰርቶ ብዙ የሚያገኝ ነው። ደግሞ ድሮ የሚቀርበውንና አሁን የሚቀርበውን የኪነጥበብ ዝግጅት ከድሮው ጋር ስታወዳድረው ያሁኑ ሆን ተብሎ ለገንዘብ የተዘጋጀ ይመስላል። ያው የኢኮኖሚም ጉዳይ ስላለ፤ ውድድርም ስላለ። የዛኔ ኪነጥበቡ ላይ እርምት ነበረ በግጥሙ ላይ ገቢር ተገብሮ እንዳይኖር፣ ቅርብና ሩቅ ስህተት እንዳይኖር በግጥሙ ላይ፣ ዜማው አንዱ ካንዱ እንዳይመሳሰል በጣም ጥንቃቄ ይደረግበት ነበር። ስለዚህ ህዝቡ ያንን ዜማ ባጭር ጊዜ ውስጥ አያወጣውም ነበር። አሁን ጥሩ ዘፋኞች ጥሩ ገጣሚዎች አሉ አይካድም ይሄ አድጓል ሙዚቃው። ግን በእኔ አመለካከት ግጥሙ አላደገም ያንዳንዶቹ ግጥም እርስ በርሱ ይጋጫል። ሁለተኛ ደግሞ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ዜማ አላየሁም። 3 ወር 4 ወር ከቆየ በኋላ መልሶ ይደበዝዛል። እንግዲህ አንድኛ መብዛቱ ለውጥ ስላለ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ ዜማው አንዱ ካንዱ የሚወራረስ ከሆን ይህ ብዙ የህዝቡን ህሊና ላይዘው ይችላል። የዛን ጊዜ እነ ብሄራዊ ቲያትር፣ እነ ክቡር ዘበኛ በኋላ ነው የመጡት እና ሀገር ፍቅር ብቸኛ በመሆኑ ቋሚ የሆነ ስራ ነው ይሰራ የነበረው።

ባውዛ – ከኢትዮጵያ እንዴት እንደወጡ፣ እዚህ አሜሪካ ሲኖሩ እዚህ ላለው ወጣት የኢትዮጵያን ባህል እንዲጠብቅ እዚህ እርስዎ የሚያድርጉት አስተዋጽኦ ካለ ቢገልጹልኝ።

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – አዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ የዚያን ጊዜ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ካሳ ገብሬ እሳቸውም ጎንደርና ላሊበላ የሰራሁትን ስራ አይተው በኮንስትራክሽን ስር አንድ የኪንጥበብ ቡድን ማቋቋም ስለምንፈልግ ይህ ሰው ይመደብልን ብለው ጠየቁ በዛ ጡያቄ መሰረት እዛ መስራት ጀመርኩ። ከዛ በጣም ሰፊ ጥናት ተጠንቶ በጀት ተመድቦ ስራ ሊጀመር ሲል ለውጥ መጣ። የዛኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከነበረው ከታምራት ላይኔ አንድ ደብዳቤ ደረሰኝ። የዛኔ 52 አመቴ ቢሆንም ጡረታ ጊዜዎ ካለፈ 12 አመት ስለሆነው ከዛሬ ጀምሮ ከስራ ጡረታ እንዲወጡ የሚል ነበር ደብዳቤው። እና ሻጥር እንዳለበት ገባኝ። ጡረታ ሚኒስቴር ሄጄ ጡረታ መብቴን ለማስከበር በምጥርበት ጊዜ የ12 አመት እላፊ አለብህና ማግኘት አትችልም አሉኝ።የዛኔ ጡረታ የሚወጣው በ55 አመት ነበር።  የለም ብዬ ከባህል ሚኒስቴር ገና ጡረታ ለመውጣት 3 አመት እንደሚቀረኝ አጽፌ አመጣሁ። ቢሆንም ጡረታ ሚኒስቴር ሊወስንልኝ ስላልቻለ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ሰውየው ይህንን መረጃ አምጥቷልና ምን እናድርግ ብለው 3 ደብዳቤ ጻፉልኝ ግን ምንም መልስ አልመጣም። ባንዴ ህይወቴ ቆመ። ቤተሰቦቼ ችግር ላይ ወደቀ።አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እኔን በበጎ አይን እንደማያዩኝ ሰማሁ። ከዛ ጎንደር በነበርኩበት ጊዜ የማውቃቸው አቶ ተስፋሁን ረዳ የሚባሉ ቤተ እስራኤላዊ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በእሳቸው አማካኝነት እድል ገጥሞኝ እየሩሳሌም ሄድኩ። ያው የኪኒጥበብ ሙያ ዛር፣ ልክፍት ነውና እዛም ቡድን አሰባስቤ መስራት ጀመርኩ። እስራኤል ስራ ለመስራት አስቸጋሪ ነው እና አንድ ገዳም ተጠግቼ ገዳሙ የስራ ፈቃድ አውጥቶልኝ ነበር የምሰራው። ከዛ ወደ አሜሪካ የምሄድበት መንገድ አጋጠመኝ ተነስቼ ወደ አሜሪካ መጣሁ። አሁን ቋሚ አድራሻዬን በቤተክርስቲያን አካባቢ አድርጌ ቤተክርስቲያን ውስጥ እያገለገልኩ እገኛለሁ። በኪነጥበብ ሙያ እዚህ አንዳንድ ስራዎች ለመስራት ተሞክሯል ቲያትሮች፣ ሙዚቃዎች ግን እዚህ አገር አስቸጋሪ ነው። ሙያተኛው ቁጭ ብሎ ቲያትርም ሆነ ሙዚቃ ለማጥናት ጊዜ የለውም። ግን ሞክረናል አሁንም እንሞክራለን። በተለይ የወደፊት አላማዬ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ለመስራት ነው። የአሁን ጊዜ መዝሙሮች የዘፈን ይዘት እየያዙ ነው ያሉት ስለዚህ ያ የሚሻሻልበትና ትክክለኛ ያሬዳዊ ዜማዎች የሚሰሩበትን መንገድ ማድረግ ነው እቅዴ።

ባውዛ – አሁን ደግሞ እስቲ ስለ ቤተሰብዎ ይግለጹልኝ።

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – ከዚህ ደረጃ እንድደርስ ያደረገችኝ ባለቤቴ እህት አፈራሁ መኮንን ናት። በትዳር 43 አመት ቆይተናል። ባለቤቴ የኪነጥበቡን ሙያ እንድገፋበት እቤት በምሄድ ጊዜ የምትሰጠኝ ምክርና አስተያየት፤ ስበሳጭ እያረጋጋች፤ በደስታ እንድኖር ያደረገችኝ ባለቤቴ ነች። ሰው በቤቱ ውስጥ ብስጭት ካለው እቅድና አላማ ቢኖረው እንኳን ሊያሳካው አይችልም። እና 6 ልጆች አፍርተን አሁን እዚህ አገር በደስታ እንኖራለን።

ባውዛ – ስለልጆችዎ ትንሽ ቢገልጹልን

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – መጀመሪያ በተከታታይ 2 ወንድ ወለድንና እንዴት ነው ሴት ሳናገኝማ አናቆምም ተባብለን ሶስተኛ ስንወልድ አሁንም ወንድ ሆነ ከዛ በአራተኛው ሴት አገኘን። የመጀመሪያው ያሬድ፣ ሁለተኛው ፋሲካ፣ ሶስተኛው በትረ፣ አራተኛዋ ሴቷ ህብረ ትባላለች በኪነጥበቡ አኳያ አንዳንድ አስተዋጽኦ እያደረገች ነው የአባቴን ሙያ እቀጥላለሁ እያለች። አምስተኛዋ አቦነሽ ትባላለች እኔም ወደእዚህ በመምጣቴ የሚደግፋት አጥታ ነው እንጂ አሉ ከሚባሉት ድምጻውያን አንዷ መሆን የምትችል ነች። አሁን በናይት ክለብ ውስጥ አንዳንዴም ወደ ውጭ በኩንትራት እየሄደች ትሰራለች። የመጨረሻው መስፍን ይባላል። እሱ ዲቪ ደርሶት እዚህ አገር ነው ያለው።

ባውዛ – ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለው የሚያደንቋቸው ሰዎች

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – አስቸጋሪ ነው ለመጥቀስ። ግን እንደ እዩኤል ዮሀንስ፣ አውላቸው ደጀኔ፣ አሰፋ አባተን አድንቃለሁ።

ባውዛ – በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ

አርቲስት ቀለመ ወርቅ ደበበ – እዚህ አገር ብዙ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አሉ። ያው የስራቸው ሁኔታ እንደሚያስቸግራቸው አውቃለሁ። ግን እንደው ተሰብስበን በአመት ሁለት ጊዜ ጥሩ ነገር እያዘጋጀን ሙያችንን ማገልገልና ባህላችንን ማሳየት የምንችልበት መንገድ ቢፈጠር አንድ የባህል አዳራሽ ቢኖረን ደስ ይለኛል። አንዴ ከጀመርነው በራሱ ሂደት እያደገ ይሄዳል።

ባውዛ – አርቲስት ቀለመ ወርቅ ላደረጉልን ትብብር ከልብ እናመሰግናለን። በቀጣይ እትማችን አርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ ከአዘጋጁት መጽሄት ለአንባቢያን ቁም ነገር ያካፍላሉ ያልናቸውን ይዘን እንቀርባለን።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here